የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ካሳለፍነው ቅዳሜ እስከ ማክሰኞ ድረስ መካሄዳቸው ይታወሳል ። በነዚህ ጨዋታዎች ላይ በተፈጠሩት የዲሲፕሊን ጥሰቶች ላይ የሊጉ የውድድር እና ስነስርዓት ኮሚቴ በትላንትናው ዕለት ባደረገው ስብስብ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የቅጣት እና የእገዳ ውሳኔዎችን አስተላልፏል ።
በዚህም መሰረት ሀዋሳ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ በቀይ ካርድ የተሰናበተው ፀጋሰው ድማሙ የአራት ጨዋታ እገዳ እና ሶስት ሺህ ብር ( 3000 ) ፤ ፋሲል ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበቱት ሶስት ተጫዋቾች ማለትም የአርባምንጭ ከተማው አሸናፊ ፊዳ ሶስት ጨዋታ እገዳ እና ሶስት ሺህ ብር ( 3000 ) በተመሳሳይ የፋሲል ከተማዎቹ ያሬድ ባየህ የአንድ ጨዋታ እገዳ ሀብታሙ ተከስተ ደግሞ የአራት ጨዋታ እና የሶስት ሺህ ብር ( 3000 ) ቅጣት ተላልፎባቸዋል ።
እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ አራት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ ክለቡ አምስት ሺህ ብር ( 5000 ) እንዲቀጣ ተወስኖበታል ። ከደጋፊዎች ጋር በተያያዘ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በዕለቱ የመሀል ዳኛ እና አራተኛ ዳኛ ላይ በጨዋታው መሀል እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ አስነዋሪ ስድብ ሰለመሳደባቸው በቀረበው ሪፖርት መሰርት ክለቡ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር ( 7500 ) እንዲከፍል ተወስኖበታል ።
አስተያየት ይስጡ