ራሱ የመሠረተውን ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እያንደረደው የሚገኘው አሰልጣኝ።
ከአመት አመት አዳዲስ ተጫዋቾችን እያሳየን በከፍተኛ ሊጉ ሜዳ ላይ አስደናቂ ቡድን ሲገነባ አስተውያለሁ። እግር ኳስን በትልቅ ደረጃ መጫወት ባይችልም ተወልዶ ላደገበት ጋም ጨንቻ እና አካባቢው ግን ተጫውቶ አሳልፏል ነገር ግን ወደ ስልጠናው የገባው ቶሎ ስለነበር ታዳጊዎችን ሰብስቦ ማሰልጠን ከጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጋሞ ጨንቻ እግር ኳስ ክለብን በራሱ ተነሳሽነት ከመሠረተ በኋላ ቡድኑ በፍጥነት ውድድሮችን እየተሻገረ ለከፍተኛ ሊጉ እንዲበቃ አድርጓል።
አርባምንጭ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ክለቦች ጥሩ የሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾችን ሲወስዱበት በፍጥነት በሌሎች እየተካ ሲጓዝ የምንመለከተው ወጣቱ አሰልጣኝ ማቲዮስ ለማ ዘንድሮ ራሱ ያቋቋመውን ጋሞ ጨንቻን እየመራ ያለፉትን አመታት አስቆጪ ጊዜያቶች ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን በማሳደግ ለመካስ ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።
ጋሞ ጨንቻን ለስድስት አመት አርባምንጭ ከተማን ለአራት አመት በረዳት እና ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በዋና አሰልጣኝነት የመራው የካፍ ሲ ላይሰንስ ባለቤቱ እና የስፖርት ሳይንስ ተማሪ የሆነው ማቲዮስ በሁለተኛው ዙር ውድድር ትላንት አቃቂ ቃሊቲን 5ለ1 በመርታት ዙሩን በድል መጀመር የቻለ ሲሆን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ክለቡ ጋሞ ጨንቻን በ10 ጨዋታዎች በሰበሰበው 24 ነጥቦች ከተከታዩ የካ ክፍለ ከተማ በሁለት ነጥብ በልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ እንዲገኝ አስችሎታል።
- ማሰታውቂያ -
የጋሞ ዞን አስተዳደር እና የክለቡ አመራሮች ከፍተኛ ዕገዛን እያደረጉለት መጓዙን የቀጠለው ክለቡ ዘንድሮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሊጉ ክለቡ ካደገ ከፍተኛ ሽልማትን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ሰምቻለሁ።


