“መልክህ አላማረኝም ብለው የተነሱ ደጋፊዎች ቢኖሩም ሁሉንም
በውጤት ለማሳመን ጠንክሬ እየሰራሁ ነው”አሰልጣኝ ስዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

በዮሴፍ ከፈለኝ 

መቐለ 70 እንደርታ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ባለመካፈሉ ብቸኛው የሀገራችን ተወካይ ፋሲል ከነማ ሆኗል፤ በመጀመሪያው ግጥሚያ በቱኒዚያው ሞንስቲር 2ለ0 የተረታው የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ፋሲል ከነማ ውጤቱን ቀልብሶ ወደ 2ኛ ዙር የማለፍ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር በነበረው አጠር ያለ ቆይታ “የተሸነፍንበት ውጤት የመቀየር አቅም አለን ይህም የሙሉ ቡድኔ እምነት ነው” ሲል ተናግሯል፤ አሰልጣኙ ከዚህ ጨዋታ ውጪ ስለ ፕሪሚየር ሊጉ፣ ከፋሲል ከነማ ቦርድና ደጋፊ ጋር ስላለው ግንኙነት በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ጦርነትና ኮቪድ 19 እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ቱኒዚያ የነበረው ጉዞ መንገላታት ነበረው እንዴ?

ስዩም፡- አካሄዳችንን ስናየው ከአዲስ አበባ ካይሮ ከካይሮ ወደ ቱኒዚያ ነው የበረርነው፡፡ ከአዲስ አበባ ካይሮ ስንጓዝ የተጠቀምነው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ነው፤ ከካይሮ ወደ ቱኒዚያ ደግሞ በግብፅ አየር መንገድ ነው የሄድነው፤ ካይሮ ከገባን በኋላ ወደ ቱኒዚያ ለመጓዝ ወደ 7 እና 8 ሰዓት መጠበቅ ነበረብንና ወንበር ላይ አረፍ እያልን ጋደም እያልን ቆይተን ነው የሄድነው፤ ስንመለስም ተመሳሳይ ነው አስቸጋሪ መንገድ እንደሆነ መናገር ይቻላል ነገር ግን ቱኒዚያ ስንገባ ክለቡ ያደረግልን አቀባበል ምርጥ ነበር፤ ስታንዳርዱን በጠበቀ ሆቴል ነው ያስቀመጠን… የምግብ አቅርቦቱ በጣም ደስ የሚል ነበር የተቀመጥንበት ሆቴል የሀገሪቱ የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን የሜዳ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድኖችን የሀገሪቱ ትላልቅ ክለቦች የሚቀመጡበት በመሆኑ መስተንግዶው ለስፖርተኛ የሚሆን ነው በዚህ ደስ ብሎናል፡፡

ሀትሪክ፡- ሰበብ ማድረግ ባይቻልም ግን የጉዞው መንገላታት ለውጤቱ መበላሸት አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ይቻላል?

ስዩም፡- በፍፁም… የማገገሚያ ቀናትም ስለነበረን ምንም የሚገናኝ ነገር የለውም፡፡ ችግር ፈጥሯል ብዬም አላምንም

ሀትሪክ፡- ለመልሱ ጨዋታ ልምምዱን በደንብ እየሰራችሁ ነው?

ስዩም፡-አዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት በየቀኑ ልምምዳኝን ቀጥለናል፡፡ የቱኒዚያው ሞንስቲር ክለብ የአገሪቱ የሱፐር ካፕ ፍፃሜን ከኤስፔራንስ ጋር ያደረገው ጨዋታን አግኝተን ከተጨዋቾቼ ጋር አይተናል በዚህ ጨዋታ ተጋጣሚያችን ሞንስቲር ነው 2ለ0 አሸንፎ ዋንጫ የወሰደው…. በዘንድሮ የውድድር አመት ጀምረው ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ፤ የኛን ቡድን ስታይ በኮቪድ 19 ምክንያት 7 ወር የተገለሉ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው የሄዱ ተጨዋቾች ያሉበት ቡድን ነው በኛ በኩልም ከቀሪዎቹ ተጨዋቾች ጋር ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ እንደ ቡድን ለመጫወት የሄድነው ግን በተለይ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ጋር የተዘጋጀነው ለ4 ቀናት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ተጨዋቾቼ ከጠበኳቸው በላይ ነው አሪፍ ሆነው ያገኘኋቸው… ጥሩ ተንቀሳቅሰናል ብዙ ቀን እንዳረፉ ሆነው አልነበረም… አዲስ የተቀላቀሉንም ጥሩ ነበሩ፤ በመጀመሪያው ግማሽ የነበረን የሜዳ ቁጥጥር በጎል አለመታጀቡ እንደ ድክመት ይታይ እንጂ ጥሩ ነበርን፡፡ ከዚህ ውጪ የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች የመጀመሪያው 15 ደቂቃ ላይ ነው የሚያስቸግሩት ተጠንቀቁ ተባብለን ተነጋግን ገና በተጀመረ 3ኛው ደቂቃ ላይ ግብ መቆጠሩን እንደ ድክመት አይተነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- የተባለውን ያህል ጥሩ ነበራችሁ?

ስዩም፡- የመጀመሪያው 45 ደቂቃ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል የጎል እድሎችን ፈጥረናል ጥሩ ነበርን በጎል አለመታጀቡ ቅር ያሰኛል 2ኛው 45 ደቂቃ ግን የተለየ ነው ዋነኛ ግብ ያደረግነው ማሸነፍ ካልተቻለ አቻ በጣም ከከፋ በጠባብ ግብ መሸነፍ ማለትም ሊገለበጥ የሚችል መሆን አለበት ተባብለን ስለነበር ተጨዋቾቼ 2ኛው 45 ደቂቃ ላይ ሲገቡ ራሳቸውን መቆጠብና ማፈግፈግ ወደ ኋላ ማለት ጀመሩ እንጂ እንደመጀመሪያው 45 ደቂቃ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ሊቀየር ይችል ነበር ብዬ አስባለው ሁለተኛው ግብ ከቆመ ኳስ ነው የተቆጠረብን፡፡

ሀትሪክ፡- አሁንስ ምን ይጠበቃል? የሚገለበጥ ውጤት ነው… ውስጥህ እንዲህ ያምናል?

ስዩም፡- አሁንማ ቡድኑን አይተነዋል በውስጣችን ድፍረቱ አለ የእነርሱ ኮሜንታተር በአርብኛ ሲናገር ከጠበቁት በላይ ማግኘታቸውን ነው የተናገረው በመልሱ ጨዋታ የማጥቃት አጨዋወት ይዘን በመግባት ውጤታማ ለመሆን ስንዘጋጅ ነበር የቆየነው እናም ውጤቱ የመገልበጡ ነገር አያጠያይቅም እዚያ በሄደው ልዑካን ጭምር ሜዳው ላይ ያሳየነው አቋም ከጠበቅነው የተሻለ በመሆኑ ሁሉም የቡድኑ አባላት እዚህ ማሸነፍ እንደምንችል እምነቱ አለን እኔም ውጤቱ እንዲገለበጥ ለማድረግ በውስጤ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡

ሀትሪክ፡ ሙሉ ቡድኑ ጤነኛ ነው የተጎዳ የለም?

ስዩም፡-ሁሉም ለጨዋታ ተዘጋጅቷል ቱኒዚያ ላይ የጡንቻ መሸማቀቅ ገጥሞት የነበረው አምሳሉ ጥላሁን አልተሰለፈም አሁን ግን ለውጥ አለው ቀጣዮቹ 2 ቀናት ያለውን ሁኔታ አይተን እንወስናለን /ቃለ ምልልሱ ሀሙስ ቀን የተደረገ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በቱኒዚያ ቆይታህ የታዘብከውና ከኛ ጋር ያለው ልዩነት ምንድነው?

ስዩም፡- ሲነሳ አደረጃጀት ይለየናል ሲበዛ ፕሮፌሽናሎች ናቸው ለምሣሌ እኛ ከዚህ ካይሮ ከካይሮ ሞኒስቲር ተጓዝን ጉዞው ድካም ይፈጥራል እነርሱ ግን ከሞኒስቲር ከተማ የቀጥታ በረራ አድርገው ለመምጣት አስበዋል ይሄ ትልቅ አቅማቸውንና ፕሮፌሽናል ደረጃቸውንም ያሳያል፡፡ ከዚያ ውጪ የቱኒዚያ ሊግ ፕሮፌሽናል ናቸው ከሚባሉ ሊጎች አንዱ ነው፤ ክለቡ የተሰየመው በከተማው ሞነስቲር ስም ነው የራሱ ሜዳ አለው ሳሩ የተፈጥሮ ነው ምቾቱ ግን እንደ አበበ በቂላና ሀዋሳ የሰው ሠራሽ አይነት ሜዳ ነው ምቹ ሜዳ ነው እያንዳንዱ ክለብ የተመሳሳይ ሜዳ ባለቤት ነው በትንሹ በዚህ መንገድ ከኛ የተሻሉ ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ቦርድ ሙሉ ድጋፍ አለኝ ብለህ ታምናለህ?

ስዩም፡-አዎ ስራዬን በቅርብ የሚያውቁ የቦርድ አባሎች ማኔጅመንቱና የቴክኒካል ስታፍ ሁሉም እኔነቴን ያውቃሉ በርግጥ በፌስቡክና በሌሎች ድረ ገጾች ላይ በተለይ በኮቪድ 19 ጊዜ ብዙ መንገጫገጮች ብዙ ውዝግቦችም ንትርኮች ነበሩ፤ ሰው የራሱ ስሜትና ፍላጎት ሊኖረው ይችላል ያንን ምንም ማድረግ አልችልም፤ ውሌን በተመለከተ የፈረምኩት ፊርማ ዘንድሮ ይጠናቀቃል ከ100 ፐርሰንት በላይ በቦርዱ በማናጀመንቱና በቴክኒካል ስታፍ ሙሉ ድጋፍ አለኝ፡፡ በእቅዴ መሠረት ከቻልን በኮንፌዴሬሽን ካፕ ይህን ዙር አልፈን የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት እፈልጋለው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን በበላይነት ለመጨረስ አቅደን ነው የተነሣነው ይሄን ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከደጋፊው ጋር ያለው ግንኙነትስ ምን ይመስላል? ልዩነት ካለ ለውጤት ማጣት በር ሊከፍት አይችልም?

ስዩም፡- ከደጋፊው ጋር በተያያዘ አንድ ነገር አስረግጬ ልናገር እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጡኝም ደጋፊዎች አሉ በውስን አካል ለፋሲል ካለ ቀናነት ከማሰብ ይሁን ከራስ ስሜት ጋር የተያያዘ ይሁን የተወሰነ የማያቸውና የምሰማው ኔጌቲቭ ነገሮች አሉ፤ እነኚህን ሁሉ ላይና ልጨርስ አልችልም፡፡ ማሳመን ያለብኝ በስራዬና በውጤት ብቻ ነው ስራዬ እንዲናገር ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ መልክህ አላማረኝም ብለው የተነሱ ደጋፊዎች ቢኖሩም ሁሉንም በውጤት ለማሳመን ጠንክሬ እየሰራው ነው፤ አላስፈላጊ ትችቶች ላይ ካተኮርኩ ስራዬን ላበላሽ ስለሆነ አቅሜን ስራዬ እንዲገልፅ በማሰብ ከባልደረቦቼና ተጨዋቾቼ ጋር ስራዬን ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ጨዋታው በዝግ መሆኑ ጉዳት የለውም?

ስዩም፡- እዚያም የተጫወትነው በዝግ ነው የተወሰነ ሰው ነው ትሪቩን የገባው 100 ላይሞላ ይችላል ያ ለሁላችንም በመሆኑ ተፅዕኖ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ሁላችንም ይህን ትተን ስራችን ላይ ነው ያተኮርነው.. ምናልባት በቀጥታ ስርጭት ሊተላለፍ ይችላል፤ በእኛ በኩል ግን አሸንፈን በማለፍ ይህን ክብር መውሰድ ለኛ ትልቅ ደስታና ድፍረት መሆኑን ስለምናውቅ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ ደጋፊ ቢኖር እንመርጥ ነበር ያው በሽታው ለሁሉም ስለሆነ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡

ሀትሪክ፡- ጦርነቱ በረድ ያለበት ጊዜ ላይ በመሆኑና ሀገር እንደመወከላችሁ ውጤቱ ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የለውም ማለት ይቻላል?

ስዩም፡-በርግጥ ስፖርትና ፖለቲካ ባይገናኝ ደስ ይለኛል ነገር ግን እንደ ሀገር በተለይ በኳሱ ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ድል ማግኘት ለእግር ኳሱ መነቃቃት ትልቅ ዕገዛ ይኖረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሠላሙ እየበዛ መሄዱ ለምንጀምረው ፕሪሚየር ሊግ ራሱን የቻለ ድምቀትም ይኖረዋል ከሁሉ ደግሞ የፋሲል ደጋፊና መላው ህብረተሰብ ደስተኛ ለማድረግ ብንችልና ቢሳካልን ደስ ይለናል በሊጉ ላይም ውጤቱ የተሻለ ጥንካሬ ይፈጥራለን ብለን ስለምናስብም በየቀኑ ውጤቱ የሚሰጠውን ትርጉም እንደተነጋገርንበት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ጦርነቱና ኮቪድ 19 እንደ ቡድን ፋሲል ከነማ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አልነበረውም?

ስዩም፡-በጦርነቱ ዙሪያ በቀጥታ እኛ ላይ የመጣ ችግር የለም፤ ነገር ግን ጦርነት በራሱ ትልቅ ስሜትን የሚጎዳ ነገር ሊከሰት ስለሚችል ጥሩ ስሜት አልፈጠረብንም፤ ሠላም ከሌለና በሀገር ደረጃ ሠላም ከጠፋ ለእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ኑሮ አስቸጋሪ ይሆናል፤ ሠላሙ እንዲጨምር የሁላችን ፍላጎትና ፀሎት ነው፤ እግዚአብሔርም ወደ ሠላሙ የሚወስደን ይመስለኛል፤ በተጨማሪ ደግሞ ኮቪድ 19 በአገር ደረጃ ትልቅ ዓለምን ያናወጠ ብዙ ነገርን የቀየረ መጥፎ በሽታ ነው የቡድናችን አባላት እንዲጠነቀቁ ሁሌም የምናገራቸው ነው ቱኒዚያም ተመርምረናል ዝግጅት ላይም ምርመራው ነበር እዚህም ተመርምረን ሁሉም ኔጌቲቭ ነው መባሉ አስደስቶኛል፡፡ በሽታው እስኪጠፋ ድረስ ምርመራው ይቀጥላል የኛም ጥንቃቄ እንደዛው ነው፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱም ሙሉ በሙሉ ተወግደው የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡ ጨረስኩ.. የምታመሰግነው ካለ?

ስዩም፡-ለክለቡ ቦርድ አባላት ለማኔጅመንቱ ለቴክኒካል ስታፎቼ ለተጨዋቾቼ ምስጋና አቀርባለው ስራዬ ጤነኛ ሆኖ እንድሄድ በፍላጎትና በደስታ አብረውኝ ስለሰሩና ለተሻለ ነገር መነሳሳታቸው ለእኔ ኩራት ነው እንደሀገር ይህን ጨዋታ አሸንፈን የተሻለ ደረጃ እንድንጓዝ ደጋፊውን ማርካት እንድንችልና የታሪክ ተጋሪ እንድንሆን በርታትን እንሰራለን ደጋፊውም ይህን ስሜታችንን እንዲረዳ እፈልጋሁ.. በቅርቡ በሚጀመረው ፕሪሚየር ላይ ላይ ያቀድነውን ሻምፒዮን የመሆን ክብር የምንጎናፅፈው ሁሉም በየሙያው የሚያደርገውን አውቆ ሲንቀሳቀስ ስለሆነ የፋሲል ከነማ አንድነት እንዲጠናከር አደራ እላለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport