(በይስሀቅ በላይ)
*ኢትዮጵያዊቷ ሊዲያ ታፈሰ ቅዳሜ የሚካሄደውን የናሚቢያና የታንዛኒያን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ትመራለች
ሀገር በቀል ወይም ፕሮፌሽናል ያልሆኑ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአህጉሪቱ ሁለተኛው ውድድር የሆነው የቻን 2020 የአፍሪካ ዋንጫ በካሜሩን አስተናጋጅነት በልዩ ድምቀት ተጀምሮ እየተካሄደ ነው።
ለ21 ቀናት የሚቆየው የቻን 2020 ሻምፒዮና ባለፈው ቅዳሜ በይፋ ሲከፈት የካሜሩንን ባህልና ታሪክ በሚያሳይ አፍሪካዊነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ በቀረበና 30 ደቂቃ በፈጀ ልዩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት የተጀመረ ሲሆን በዕለቱ በተካሄደ የመክፈቻ ጨዋታም አዘጋጅዋ ካሜሩን ዜምባብዌን 1ለ0 በማሸነፍ ሻምፒዮናውን በድል ጀምራለች።

የካሜሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ንጉቴ፣የፊፋው ፕሬዘዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ፣ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ በፊፋ ዕገዳ በተጣለባቸው አህመድ አህመድ ምትክ በጊዜያዊነት ካፍን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ኮንስታንት ኦማሪ እንዲሁም ካፍን ከ30 ዓመት በላይ በፕሬዘዳንትነት የመሩት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ካሜሩኒያዊው ኢሣ ሀያቱ በክብር እንግድነት በተገኙበት ነው ሻምፒዮናው በልዩ ድምቀት የተጀመረው።

የብዙዎችን ቀልብ ከሳበውና ደማቅ ከነበረው የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ሌላ የMTV Award አሸናፊ የነበረው ራፐሩ ስተንሌይ ኢኖው አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ማስክ አድርገው ከኮቪድ በሃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በስታዲየም ለተገኙት ወደ 12ሺ ለሚጠጉ ተመልካቾችና ለክብር እንግዶቹ ለሽልማት ያበቁትን ሙዚቃዎች በማቅረብ ሌላው የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ አድማቂ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት አቅም የለኝም በማለቷ ለካሜሩን በተሰጠው የቻን 2020 ሻምፒዮና ላይ በሻምፒዮናው የምትወከልበት፣ ስምዋ የሚጠራበት ቡድን ባይኖሯትም በአህጉሪቱና በአለም አቀፍ የእግር ኳስ መድረክ ሁሌም ስሞዋን በሚያስጠሩት ሁለት ታላላቅ ዳኞች ተወክላለች፤በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰና በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሠማ።

ሁለቱ ኢንተርናሽናል ዳኞቻችን ካፍ ለቻን 2020 ከ31 ሀገራት ከመረጣቸው 41 ዳኞች ውስጥ በመካተታቸው ሀገራችንን የመወከልና የሀገራችን ባንዲራም በካሜሩን ምድር ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የማድረግ ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል።
ካፍ ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞች የወንዶችን የሻምፒዮና ውድድር እንዲመሩ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ለቻን 2020 የተመረጠች ብቸኛዋ እንስት ዳኛ ስትሆን ሌሎች ሶስት ረዳት ዳኞችም ከካሜሩን፣ከናይጄሪያ፣ከማሊ መመረጣቸውም ይታወቃል።
ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በታሪክ የሚያደርጋትን የቻን ሻምፒዮናን የፊታችን ቅዳሜ በዋና ዳኝነት እንድትመራ ተመድባለች፤
ሊዲያ የፊታችን ቅዳሜ የግሩፕ D ጨዋታ የሆነውን የናሚቢያንና የታንዛኒያን በመሀል ዳኝነት በመመራት ሌላ አዲስ ታሪክ ታፅፋለች።

ኢንተርናሽናል የመሀል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የቻንን የወንዶች ሻምፒዮናን በመሀል ዳኝነት ከመምራቷ በፊት በሣምንቱ መጀመሪያ ከወንዶች ጋር የብቃት ፈተና የወሰደች ሲሆን የብቃት ፈተናውንም ከወንዶች እኩል ሮጣ በብቃት ማጠናቀቋም ተስምቷል።ሊዲያ በብቃት ፈተናው ወቅት የተቀመጠላት የሠዓት ታርጌት የነበረ ሲሆን እሱንም በብቃት በማሟሏታ ለቅዳሜው ጨዋታ እንድትመደብ እንዳደረጋት ከወደ ካሜሩን ከመጡ ታማኝ የመረጃ ምንጮች ማወቅ የተቻለው ።
ከዚሁ ከቻን2020 ጋር በተያያዘ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማም ካፍ ለሻምፒዮናው ከመረጣቸው 19 የመሀል፣20 ረዳትና 8 የቪዲዮ ረዳት ዳኞች ውስጥ አንዱ ሲሆን ሊዲያ በመሀል ዳኝነት በምትመራው ጨዋታ በአራተኛ ዳኛነት መመደቡም ታውቋል።
ሀገራችንና ባንዲራቻንን ወክለው በካሜሩን የሚገኙት ሁለቱ አምባሳደሮቻችን የተሳካ ጊዜን አሳልፈው እንዲመለሱ ምኞታችን ነው።
አስተያየት ይስጡ