“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለፊፋ የመክሰስ ሃሳባችንን ትተነዋል” አቶ በረከት ደረጀ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኢንተርሚዲየሪዎች ማኅበር ም/ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኢንተርሚዲየሪዎች ማኅበር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያደረገው ውይይት በሠላም በመጠናቀቁ ወደ ፊፋ ሊሄድ የነበረውን ሃሳብ መሠረዙ አስታወቀ፡፡
ም/ል ፕሬዝዳንቱ “ፌዴሬሽኑ የዛሬ ዓመት የኢንተርሚዲየሪ ሕጋዊ ሰርተፊኬት ከመስጠት ውጪ ሌላ ማብራሪያና ድጋፍ አላደረገም፡፡ ሙያው አዲስ ከመሆኑ አንፃርና ብዙ ችግር ያለበት በመሆኑ ማህበሩ ድጋፍ ሊደረግለት ሲገባ ፌዴሬሽኑ ዝምታን መርጧል፡፡

ማህበራችን ግን ከአንዴም ሁለቴ ደብዳቤ ፅፎ ለውይይት ቀጠሮ ብንፈልግም በተለያየ መልኩ ምላሽ ሊሰጠን ባለመቻሉ ቅሬታ ተፈጥሮብን ቆይቷል” ሲሉ ሁኔታውን ገልፀዋል፡፡
“የዝውውር ሂደቱ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እንደሚከወን በተለምዶ እንጂ ጤናማና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለ አካሄድ በታቃራኒ የቆመ መሆኑን ማህበሩ ዳግም ይህን ለማስተካከል ከፌዴሬሽኑ ጋር ለመነጋገር ፈልገን 2 ወር ሙሉ አጥጋቢ ምላሽ ማጣታችን አስከፍቶናል” ያሉት አቶ በረከት “ከሰሞኑ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር ገንቢ የሆነ ውይይት አድርገናል፡፡ በደንብ ካላስተናገዱን ላይሰንሱን ወደሰጠን ፊፋ እንሄዳለን የሚለውን የመጨረሻ ደብዳቤ ፈጣን ምላሽ አግኝቶ ተወያይተናል፡፡ በዚህም ካቀረብናቸው 8 አጀንዳዎች አብዛኞቹ ምላሽ አግኝተው በስምምነት በመፈፀማችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለፊፋ የመክሰስ ሃሳባችንን ትተነዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ም/ል ፕሬዝዳንቱ የውይይቱ ሂደቶችን ለሀትሪክ ሲገልፁ “የኤጀንት ክፍያ ያልከፈሉ ተጨዋቾች ያደረጉት ዝውውር እንዲታገድ ተስማምተናል፤ በሕገ ወጥ መንገድ የሚመጡ የውጭ ሀገር ተጨዋቾችን በማስቆም ሁለታችንም ከኢሚግሬሽን ጋር ለመስራት ስምምነት አድርገናል፡፡ የትኛውም ግብዣ በማህበራችንና በፌዴሬሽኑ ማረጋገጫ ሳያገኝ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡና ቪዛ እንዳይሰጥ ለማድረግ ተስማምተናል፤ ላይሰንስ ያላቸው ሆነው ሕገ ወጥ ስራ የሚሰሩትን ለማስቆም ተስማምተናል፡፡ ብዙ ዘገየ ያልናቸው የኤጀንት መታወቂያዎች በቀናቶች ውስጥ እንዲሰጠንና ቅድሚያ የማህበራችን አባላት እንዲያገኙ ከተቻለም ህጋዊነቱን ለመጠበቅ መታወቂያው በኛ በኩል የሚሰጥ እንዲሆን ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡

የኢንተርሚዲየሪዎችን መተዳደሪያ ደንብ በጋራ ለማየትና ለማፅደቅ ተስማምተናል፡፡ ከተጨዋቾች ማህበርና ከፌደሬሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ሶስቱም አካላት ለተጨዋቾች ሙሉ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የጋራ ስራ ለመስራት በመስማማት ውይይቱ በስኬት ተጠናቋል፡፡ በቀጣይም ለማህበራችን ቢሮ ፈልጎ ለመስጠት ፌዴሬሽኑ ያቀረብነውን ጥያቄ ተቀብሏል” በማለት ከፌዴሬሽኑ አመራሮች የተደረገውን ውይይት የተሳካ ብለውታል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ በረከት ደረጀ ለሀትሪክ እንደገለፁት ፌዴሬሽኑ ሀገር ውስጥም ባሉ ይሁን ሌሎች ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ለመስጠት ፌዴሬሽኑ ፍቃደኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ማህበሩ የተጨዋቾችን መብት ለማስከበር ይጥራል፡፡ ሕገወጥ ኤጀንቶች ከውጪ ተጨዋቾች እያመጡ ገንዘባቸውን ተቀብለው ዞር እንደሚሉ እንሰማለን፡፡ የኛ ሀገር ተጨዋች ወደ ውጪ የመሄድ ዕድል ሲያገኝ ሕጉ ምን ይላል? ቅደም ተከተሎቹ ምን ይመስላሉ? በሚል የምንችለውን ድጋፍ ለተጨዋቾች ለማድረግ ተዘጋጅተናል” ሲሉ የማህበሩን አቋም ለሀትሪክ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኢንተርሚዲየሪዎች ማህበር ተቋቁሞ ሕጋዊ ሠርተፊኬት ካገኘ አራት ወራቶች ያስቆጠረ ሲሆን በስሩ ወደ 32 የሚጠጉ አባላትን የያዘ ማህበር መሆኑ ይታወቃል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport