ኢትዮጵያ ቡና ከተጋጣሚው ሳይሆን ከራሱ አሰልጣኝ ዘላለም ጸጋዬ ጋር ሙግት ከገጠመ ቆይቷል.. ነሀሴ 30/2014 ውሉ ለሚጠናቀቀውና ዋና አሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ “እውነተኛ ረዳት አሰልጣኜ” የሚለውን የአሰልጣኝ ዘላለም ውልን ላለማደስ ወስኖ ከዋና አሰልጣኙ ጋር እየተከራከሩ ነው…. ከዳዊት እስጢፋኖስ ዝውውር ጀምሮ በአንዳንድ ተጨዋቾች ኮንትራት ዙሪያ የክለቡ ስራ አስኪያጅና ቦርድ ጣልቃ ሲገባ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ያሳየው መለሳለስ ለዚህ እንዳበቃው ሂደቱን የሚመለከቱ ወገኖች ይናገራሉ።
በዚህ መሠረት ምክትል አሰልጣኙ ወደ ቢሾፍቱ ከተጓዘው የክለቡ ስኳድ ጋር እንዳይሄድ ክለቡ መወሰኑን የቡድን መሪው ለዋና አሰልጣኙ በመግለጹ ከሐምሌ 28/2013 ጀምሮ ከቡድኑ የተገለለው ምክትል አሰልጣኙ ዘላለም ጸጋዬ ዛሬ ከቀትር በኋላ ለኢትዮጵያ ቡና ደብዳቤ አስገብቷል። ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ አሰልጣኙ በውሌ መሠረት ወደ ስራዬ እንድመለስ እየጠየኩ ይህ ካልሆነ የታገድኩበትና ከቡድኑ የተለየሁበት ምክንያት በአምስት ቀናት ውስጥ በደብዳቤ እንዲገለጽልኝ እጠይቃለሁ በማለት ጠይቆ እውነታውን ለፌዴሬሽኑ በግልባጭ አሳውቋል።
በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን በሻምፒየንስ ሊግ የሚወክለው ፋሲል ከነማ ዛሬ ከኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ እየተዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት በቀጣይ ቀናቶች ከኡጋንዳው.. ጋር ከሜዳው ውጪ የኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ የሚጠብቀው ኢትዮጵያ ቡና ግን በዚህ መሠል ፍትጊያ ላይ መሆኑ በውጤት ዘንድ ትልቅ ክፍተት እንዳያመጣ ተሰግቷል።
በቀጣይ ክለቡ የሚሰጠው ምላሽና የአሰልጣኙ አቋም ምን ይሆናል የሚለው የሚጠበቅ ሆኗል።