ትልቁ የክለቡ ደመወዝ 221 ሺህ ብር ደርሷል
” “ታፈሰና ዊሊያም መጠጡን ካላቆሙ ነገም ይባረራሉ
ቡና የጀግና እንጂ የሰካራም ቤት አይደለም”መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ
/ የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ፕሬዝዳንት/
ኢትዮጵያ ቡና ከአሰልጣኝ ዘላለም ጸጋዬ፣ ከዳዊት እስጢፋኖስና ከአቤል ከበደ ውጪ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ፈልጓቸው የከለከለው ተጨዋች እንደሌለ አስታወቀ።
ዛሬ አራት ኪሎ ሊካሄድ በነበረው የክለቡ ደጋፊ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ በምልዓተ ጉባኤ አለመሟላት ለሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ የክለቡ ቦርዱ ከደጋፊው ማህበርና በወቅቱ ከነበሩ ደጋፊዎች ጋር በነበረ ውይይት ላይ ስራ አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ክለቡ ስላወጣው ወጪ ዝርዝር የቀረበ ሲሆን በወር በደመወዝ 3 ሚሊየን 828ሺህ ከ075 ሳንቲም ሲከፍል በአመት ደግሞ 45 ሚሊየን 936ሺህ 901 ለተጨዋች እንደሚከፍል አስረድቷል። ክለቡ ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በወር 374ሺህ 400 በአመት ደግሞ 4ሚሊየን 492ሺህ 800 ብር ለምክትሉ ገ/ኪዳን ነጋሽ በወር 8ሺህ ብር ለጸጋዘአብ 14ሺህ ብር በአጠቃላይ ለሁሉም ቡድኑ ከ55 ሚሊየን ብር በአመት ወጪ እንደሚያደርግና ለሀዋሳ ከተማ የክለቡ ቆይታ እስከ 2.5 ሚሊየን ብር እንደሚያወጣ አስታውቋል።
ስራ አስኪያጁ እንደገለጹት “ክለቡ ከአሰልጣኙ ፍላጎት ውጪ ያላስፈረመው ወይም አስገድዶ ያስፈረመው ተጨዋች የለም ከሶስቱ ከዘላለም ዳዊትና አቤል ውጪ በኛ ምክንያት የቀረ የለም ከዚያ ይልቅ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጊዮርጊስ መሀመድ ኑር ጅማ አባጅፋር የፈረሙት እኛን ፈልገውን አሰልጣኙ እንቢ በማለቱ መሆኑ መታወቅ አለበት ጌታነህ ከበደንም ያጣነው አሰልጣኙ ባለመፈለጉ ነው እነ ቡልቻ ሹራ፣ ፉአድ ፈረጃ፣አስቻለሁ ታመነና ሌሎችም በራሳየው ምክንያት የቀሩ ናቸው በማለት በምሳሌነት አስቻለሁ 2 አመት ኮንትራትና ከሁለት አመቱ ደመወዝ 80 በመቶ ይከፈለኝ በማለቱ ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል”በማለት ያለውን እውነት አስቀምጧል። አሁን ባለው መረጃ ትልቁ የክለቡ ደመወዝ 221ሺህ 551 ከ72 ሳንቲም ሲሆን አጥቂው አቡበከር ናስርን ጨምሮ የዚህ ደመወዝ ባለቤቶች አቤል እንዳለ፣አስራት ቱንጆ፣ አማኑኤል ዮሀንስና ሚኪያስ መኮንን መሆናቸው ታውቋል።
እንደ አቶ ገዛኸኝ እምነት “የክለቡ ቦርድና ጽ/ቤት መጠየቅ ያለበት አመራር ላይ ካልቻለ ገቢ አሰባስቦ ስፖንሰር ፈልጎ ካላገኘ ብቻ ነው ባለኝ መረጃ 11 ክለቦች ደመወዝ መክፈል ተቸግረዋል እኛም ያ እንዳይደርስብን የምንችለውን ሰርተናል መወደስ እንጂ መሠደብ የለብንም በፌስቡክ የሚካሄጀው ዘመቻ መቆም አለበት ክለቡን እንጂ ቦርዱን ወይም ግለሰቦችን መደገፍ መቆም አለበት እንደምሳሌ ታፈሰ ሰለሞን የስነምግባር ጉዳይ ላይ ድጋፍ የሚያደርግ ደጋፊ ለቡና የሚጠቅም ነው? ተጨዋቹ ክለቡን መጥቀም ባለበት ሰአት ከሆቴልም እየወጣ ልምምድ እየቀረ ሲቀጣ እሱን ማወደስ ተገቢ ነው? ተጨዋችን እንዴት መደገፍና መቃወም እንዳለባችሁ ማወቅ አለባችሁ ሁሌ መሠጠት ያለበት ቅድሚያ ለቡና ነው” ሲሉ አስረድተዋል። እንደ አቶ ገዛኸኝ አንድም የተጨዋች ምልመላና ድርድር ላይ እንዳልተካፈለና በየፌስቡክ የሚነዛው ወሬና ስድብ እንደማይመለከተው በመግለጽ ለደጋፊው አስረድቷል።
የክለቡ ቦርድ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ በበኩላቸው “በፌስቡክ ላይ የሚያናድዱ ስራህን ጥለህ ሂድ ሂድ የሚያስብሉ ናቸው እኛም ችለን ነው የኖርነው.. አንዳንዱ ደጋፊ ራሱ የሚጽፈውን አያውቅም በቅርቡ እንኳን ቀኑን ሙሉ ሲያስቀኝ የነበረው ስለአቡበከር የተጻፈው ነው ይሄ ቦርድኮ እንዳይጫወት አደረገው እንጂ አቡኪ 10 ቁጥር ቦታ ይጫወት ነበር ብሎ ስስቅ ውያለሁ ክለባችን ስለኳስ በሚያውቁና በማያውቁ ደጋፊዎች የተሞላ ነው ደጋፊዎቻችን ይህን ማስተካከል አለባቸው” በማለት ደጋፊውን መክረዋል።
መቶ አለቃ እንደሚሉት “ስለአሰልጣኝና ተጨዋች እናንተን ጠርቼ ላማክር እችላለሁ ውሳኔው ግን የናንተ አይደለም ይህን በፍጹም አልቀበልም ካሳዬን በተመለከተ ለቡና ሲፈርም ተጨዋች ሲይዝ በፊዚካል ፊትነስ የሚያምን፣ ዲሲፕሊን የሚያስከብር፣ የምልመላ ታርጌቱ ወጣት ላይ እንዲያተኩር ከተስማማ በኋላ ነው። ዳዊትን በተመለከተ ሲወጣ የወሰደውን 800ሺህ ብር ይመልስና ለቡና ስለመፈረሙ እናወራለን በተጨሜሪም ዳዊት ከፈረመ መጠጥ ማቆም አለበት ዛሬም ነገም ጥያቄው ቢመጣ መልሱ ይሄ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በተሰብሳቢው ፈገግታ የጫረው የመቶ አለቃ ፈቃደ አስተያየት “ሳሙኤል ኤቶና ሮናልዲንሆ ጎቾ በባርሴሎና በፔፕ ጋርዲዮላ የተባረሩት መጠጥ አናቆምም ስላሉ ነው እኛ ሀገር ግን እናንተ ሰካራሞች ለምን አልሰበሰባችሁም እያላችሁ ነው ቡድናችን ውስጥ ያሉት በጣም ከባዶቹ ጠጪዎች ሁለት ናቸው ታፈሰና ዊሊያም ነገ መባረራቸው አይቀርም ቡና የጀግና እንጂ የሰካራም ቤት አይደለም መለስተኞቹ ጠጪዎች ደግሞ ብዙ ናቸው ከእነሱ ጋርም እየጠጣችሁ ብር ሲያጥራችሁ የምትበደሩት እናንተ አይደላችሁም? ተጨዋቾቹ ሲሰክሩ ብትመቷቸው ከፋዩ እኔ ነበርኩ ይሄ ቀልድ መቆም አለበት እነሱን ለማስተካከል አሰልጣኙ ካሳዬም የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የቻልነውን እናግዘዋለን። በውላችን መሠረት በ2014 ዋንጫ አመጣለሁ ብሏል ዋንጫውንም እንጠብቃለን ካላመጣ ግን መለያየታችን ነው” ብለዋል።
ምክትል አሰልጣኙ ዘላለም ጸጋዬን በተመለከተ የገለጹት መቶ አለቃ “ምክትል አሰልጣኙ ሙስና ላይ አለበት ሙስና የሰራ ደግሞ መቀጠል የለበትም ይህን አንፈራም በቴፕ ምክትሉ ላይ የተሰጠ አስተያየት ተቀድቶ መጣልን ሰማነው ካሳዬ ግን አላምንም አለ ካላመነ ልንከስ ነው ከከሰስነው ደግሞ ሌላ ውዝግብ ሊነሳ ሆነ ይህን አማራጭ ተውንና አሰልጣኙን አንመልስም ሌላ ያመንክበትን ባለሙያ አምጣ አልነው እስካሁንም አልመጣልንም በሙስና ጉዳይ ላይ ፈጽም አንደራደርም ” ሲሉ ተናግረዋል።

የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታምራት በበኩሉ “ተጨዋችን ደመወዝ የምታስጨምሩብን እናንተ ናችሁ 100ሺህ ብር ተስማምቶ ወጥቶ ለምን እሺ አልክ 150 ሺህ በላቸው ብሎ የሚያስተማምነው ደጋፊያችን ነው ከተጨዋች ጋር ካወራችሁ ኢትዮጵያ ቡናን አስቀድሙ ተጨዋቹ ፊት እየሰጣችሁ አታስጠግቡብን እናንተን ማክበር አለበት በፊት ደጋፊው ያስፈራል ይባላል አሁንስ ምን ያመጣሉ እየተባልን ነው ይሄ መስተካከል አለብን ለምንድነው ሊዮኔል ሜሲ አይሆንም ገዛኸኝ እንዳልፈርም አደረገኝ ብሎ ካወራችሁ ከቡና አትበልጥም በሉት የተጨዋችን ወሬ አትስሙ በኔ እምነት ሰይጣን ኢትዮጵያ ቡናን ስፖንሰር ካደረገ የሰይጣንን ነገር አድርጌ እንደምሄድ አትጠራጠሩ ከካሳዬ አራጌ ጋር ተያይዞ ምንም ጸብ የለም እሱ ማንንም አያኮርፍም ተጨዋችም ብቻውን እንዲነግስ አይሻም እርሱ ቡድኑን የሚያስቀድም ባለሙያ ነው ከ40ሺህ ማሊያ 18 ሺህ ማሊያ ቀርቶናል ክለቡ ዕዳ አለበት ደጋፊያችን ክለቡ ያለበትን ዕዳ ተባብረን ልናስወግድ ይወግዳል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
አመራሮቹ ከሰጡት ማብራሪያ በኋላ ከደጋፊዎቹ ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በተለይ የውይይት መድረኩ ላይ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አለመኖሩን ደጋፊዎቹ ቅሬታ ያቀረቡበት ጉዳይ ሆኗል።
አስተያየት ይስጡ