የህዳሴ ዋንጫ የሚል ስያሜን ይዞ በመካሄድ ላይ ባለው 19ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሁለት ቀዳሚ ጨዋታ ዛሬ ተደርጓል።
ከቀን 10:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 1 አሸንፏል።
ከጨዋታው በኋላ በጨዋታው ዙሪያ ሀሳቡን የሰጠው የኢትዮጵያ ቡናው ዋና አሰልጣኝ አብይ ካሳሁን በጨዋታው የነበረውን የቡድኑን እንቅስቃሴ በተመለከተ ተከታዩን ብሏል።
“ጨዋታው እንደ አቋም መለኪያ ጨዋታ ነው። ከሜዳው አለመመቸት አንፃር በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጎሎችን አስቆጠርን እንጂ ብዙም እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም።”
- ማሰታውቂያ -

“በሁለተኛው አጋማሽ ግን መሀል ላይ ብልጫ ተወሰደብን 4-4-2 ነበር የሚጫወቱት ያንን ለማድረግ ቅያሪ አድርገን የተወሰነ አስተካክለናል።ጎል ማግባታችን ጥሩ ነው የራስ መተማመን ያመጣልናል።በአጠቃላይ ጥሩ ነው ራሳችንን አይተንበተናል።”
ከቡድኑ ውህደት ጋር በተያያዘ በካጋሜ ካፕ መሳተፋቸውንም በበጎ መልኩ ያነሳው አሰልጣኝ አብይ አዳዲስ ተጫዋቾች ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳዩ መሆናቸውን በመግለፅ ጥሩ ዝውውር ሲልም ገልጿቸዋል።
በደጋፊዎቻቸው ታጅበው በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ማድረጋቸውንም በተመለከተም ደስተኛ መሆናቸውን አሰልጣኝ አብይ ተናግሯል።
“እውነት ለመናገር በጣም ደስ ይላል። የኛ ደጋፊ የታወቀ ነው እንደውም ዛሬ ከዚህም በላይ ይመጣል ብለን አስበን ነበር። ለኛ በጣም ትልቅ ዕድል ነው። ልጆቻችንም ወጣቶች ስለሆኑ በደጋፊ ታጅበን መጫወታችን በጣም ደስተኛ ነን።”
ኢትዮጵያ ቡና በካጋሜ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አድርጎ ወደ ሲቲ ካፑ የመጣ ሲሆን ሌሎች ክለቦች ግን ከዝግጅት ወደ ውድድሩ መጥተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም አሰልጣኝ አብይ ካሳሁን የክፍለ አህጉራዊው ውድድር ተሳትፎ እንደጠቀማቸው እና የቡድኑን ጥንካሬ እና ድክመት ተመልክቶበት መምጣተን ገልጿል።
“ካጋሜ ካፕ ስንሄድ ድንገተኛ ነው የሄድነው። እኛም ዝግጀታችንን አቋርጠን ነው የሄድነው ፤ ግን የተሻለ አድቫንቴጅ እንወስዳለን እዛ ቶፕ ወድድር ላይ ስለነበርን ፤ ጥሩ ሜዳ ላይም ነበርን ጥሩ የኳስ ፍሰት ያለው ጥሩ ቡድን እንግዲህ ዛሬ በእንቅስቃሴ ደረጃ እውነት ለመናገር ጥሩ ፍሰት አልነበረውም።”
“ነገር ግን ከፊት የምናገኛቸውን አጋጣሚዎች መሳት ነበር እዛ የነበረው ችግራችን ፤ እዚህ እያስቆጠርን ነው።አንድ ቡድን ግብ ማስቆጠር ከጀመረ ጥሩ ነው። በተለይ የኛ ቡድን ይህን ማድረግ ከጀመረ አሪፍ ነው። አማካዮቻችን ወደ ፊት ሄደው ማስቆጠራቸው እነ ኤርሚያስ ፤ አጥቂዎቻችንም ተገማች አለመሆናቸው ጥሩ ነገር ነው። እና የዛሬው ጨዋታ የራስ መተማመን ይሰጣል ለልጆቻችን ሶስት ጎል ማስቆጠራችን።”


