በህዳሴ ዋንጫ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ቡና 3 ለ 1 ተሸንፏል።
ከጨዋታዉ በኋላ ሀሳቡን በነበረው የድህረ ጨዋታ ቆይታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑሰገድ ከዕለቱ ጨዋታ በበለጠ የደመወዝ ክፍያ ስርዓት ደንቡን በተመለከተ ሀሳቡን እና ስጋቱን አጋርቷል።
አስቀድሞ የአዲስ አበባ ስታድየም በደጋፊዎች ታጅቦ ጨዋታ ማስተናገድ መጀመሩን እንዳስደሰተው የተናገረው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የአዲስ አበባ ስታድየምም ሆነ የአዲስ አበባ ህዝብ እግር ኳስ ናፍቆት ነበር ብሏል።
ጨዋታውን በተመለከተም ቡድኑ ዝግጅቱን ዘግይቶ መጀመሩን ያነሳው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የመጀመሪያ ፌዝ ላይ ነው ያለነው ፤ በዚህ ሁኔታ ላይ የኔ ቡድን እንዲህ ነበር ብዬ ለመገምገም አልችልም ሲል ተናግሯል።
- ማሰታውቂያ -
በመቀጠልም ቡድኑ አዲስ ነው ያለው የ2016 ዓ.ም የሊጉ ሻምፒዮን አሰልጣኝ በሊጉ የደመወዝ ክፍያ ስርዓት ደንብ አከባበር ላይ ቅሬታውን ተናግሯል።
“ቡድኑ አዲስ ነው። በአዲሱ የደመወዝ ጣሪያ ምክንያት ቡድናችን ፈርሷል። ምናልባትም ህጉን ከሚያከብር አንድ ከተጠራ አንድ ነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ቁመናችን ፕሪምየር ሊግ በሚፈልገው ልክ አይደለም። አብዛኛው እንዳያቹት ከ20 ዓመት በታች እና ከከፍተኛ ሊግ ነው።”
“አዲስ ቡድን ነው። ከ75% እና ከ80% በላይ ፈርሷል ቡድናችን ማለት ነው እና እንግዲህ ቆንጆ ውድድር እንዲኖር እዚህ ላይ ለአወዳዳሪዎችም አደራ ማለት የምፈልገው አሁን የምናያቸው ነገሮች ያሰጉኛል። በሚቀጥለው ዓመት 22 ቡድን ይሆናል ብዬ ነው እኔ የምጠብቀው አሁን ከአጀማመሩ 20 የሆነበት ምክንያት ህግ ተጥሶ ነው። በቀጣይ ደግሞ 22 ይሆናል ብዬ ነው የማስበው።”
አሁን ያለው እኛ ማስፈረም አቅቶናል ሌላው እንዴት እንደሚያስፈርም ግልፅ አይደለም ያለው አሰልጣኝ በፀሎት የውድድር መድረኩ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እኩል መሆን አለበት ብሏል።
አሰልጣኙ አክሎም በተለይም በመንግሥት በኩል የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ከማሰብ አንስቶ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በማድነቅ የፕሪሚየር ሊጉን ደረጃ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።
ሊጉ ለሁሉም እኩል መሆን አለበት ፤ የውድድሩ ደረጃም ከፍ ማለት አለበት ያለው አሰልጣኝ በፀሎት ይህ እንዲሆን ደግሞ አወዳዳሪው አካል ሁሉንም በእኩል ማየት አለበት ህግም መከበር አለበት ሲል ተናግሯል።


