ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 14ኛ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 23 ጎሎች በ21 ተጫዋች ተቆጥረዋል። የጎሎቹ አገባብ አንድ በፍፁም ቅጣት ምት ቀሪዎቹ በጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው። በሳምንቱ 19 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አንድ ተጫዋች በሁለተኛ ቢጫ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰኞ የካቲት 13 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋቾች ደረጃ ባለ ውሳኔ ካሉት ሚሊዮን ሰለሞን(አዳማ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት 1 ጨዋታ እንዲታገድ እንዱሁም ሱራፌል ዳንኤል(አርባምንጭ ከተማ) የተለያዩ አምስት ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ የተመለከተ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድና የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ ባለ ውሳኔ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው የ14 ኛ ሳምንት እግርኳስ ጨዋታ የአዳማ ከተማ ቡድን አምስት ተጫዋች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል እንዲሁም የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ስለቀረበ ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ወስኗል።
- ማሰታውቂያ -
ወልቂጤ ከተማ ክለቡ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው የ14ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ የክለቡ ተጫዋቾች 15 ደቂቃ ወደሜዳ ዘግይተው ስለመግባታቸው ሪፖርት የቀረበበት በመሆኑ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 25000 /ሃያ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል እንዲሁም የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት መብት ያለው ድርጅት የካሳ ክፍያ አክስዮን ማህበሩን ከጠየቀ ክፍያውን ሙሉ በሙሉ ክለቡ እንዲሸፍን ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ኮሚቴው ለለገጣፎ ለገዳዲ እግርኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ እና የቡድን መሪውን ለማነጋገር ጥሪ አስተላልፏል።