የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ እና የነገሌ አርሲው አጥቂ የክለባቸውን ካምፕ ለቀው ወደ አሜሪካ አመሩ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ከ2010 ጀምሮ ከታዳጊ ቡድን እግር ኳስን የጀመረው እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ደግሞ ከ2014 ጀምሮ እስከ 2017 የውድድር ዘመን ድረስ ቆይታን ማድረግ የቻለው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አላዛር ሳሙኤል ባለፈው ክረምት የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን በሁለት አመት ውል መቀላቀሉ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቀሪ የውል ዘመን ያለው ይህ ተጫዋች ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሳያሳውቅ ከካምፕ በመውጣት ወደ ሲያትል አሜሪካ ማምራቱን ያገኘሁት መረጃ ያመላክታል። ተጫዋቹ በቀጣዮቹ ቀናት የጥገኝነት ጥያቄ ለማቅረብ ማሰቡንም ጭምር ሰምቻለሁ።
ሌላኛው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን የተገኘው እና በክለቡም በዋናው ቡድን በተከታታይ አራት አመታት ቆይታን ማድረግ የቻለው አጥቂው ዳግማዊ አርአያ ባለፈው የክረምቱ የዝውውር መስኮት ለአዲስ አዳጊው ክለብ ነገሌ አርሲ በመፈረም በፕሪምየር ሊጉ ከክለቡ ጋር ቆይታን ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም ክለቡ ሳያውቅ ቀሪ ውል እያለው የክለቡን ሆቴል ለቆ ወደ አሜሪካ ማምራቱን አረጋግጫለሁ።
በዚህ አመት በተመሳሳይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መቐለ 70 እንደርታን ተቀላቅሎ የነበረው አማካዩ አብርሀም ጌታቸው በአጋማሹ ወደ አሜሪካ ማምራቱም ይታወሳል።
አስተያየት ይስጡ