አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ ያደረገው ውሳኔ ፀጥ ተብሏል ለምን ?
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በ2017 የውድድር ዘመን 16 ክለቦች በሚወዳደሩበት ፕሪምየር ሊግ ላይ አዲስ ህግን ማውጣቱ ይታወሳል። ይህም ህግ አንድ ክለብ በአንድ አመት ውስጥ መጠቀም ያለበት 56 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው በማለት ህግን በማውጣት ከተለያዩ ተቋማትም የተዋቀረ ኮሚቴን በማቋቋምም ጭምር ህጉን ተፈፃሚ ለማድረግ የሚከታተሉ እና በሚጥሱትም ክለቦች እና ተጫዋቾች ላይ ጠንካራ ውሳኔዎች ለማሳለፍ በሚል ወደ ትግበራ መገባቱ ይታወሳል።
ይህም ኮሚቴ አራት ክለቦችን መርምሬያለሁ ብሎን በመጨረሻም በሲዳማ ቡና ፣ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና መቻል የተቀመጠውን የፋይናንስ መመሪያ ጥሰው ተገኝተዋል በሚልም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የፋይናንስ አስተዳደር አጣሪ ኮሚቴ ነኝ ያለው አካል ከባድ ውሳኔዎችን ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው አራቱ ክለቦች ብቻ በአራቱ ክለቦች ውስጥ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ላይ የገንዘብ እንዲሁም ተጫዋቾች ዕላፊ ወስዳችኋል ብር መልሱ በማለት አልፎም ደግሞ የማገድ ውሳኔዎችንም ጭምር ሲወሰን መመልከታችን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ይህ ኮሚቴ ከውሳኔዎቹ በኋላ ለሚዲያ አካላት ጥሪን በማስተላለፍ አራቱን ክለቦች ቀጥቻለሁ ፣ ተጫዋቾችም ላይ ውሳኔዎች አሳልፌያለሁ የቀሩት አስራ ሁለቱ ክለቦችን ግን እየመረመርኝ ነው ብሎን በይፋ ቢያሳውቀንም ይህ ውሳኔ ግን አስራ ሁለቱን ክለቦች የረሳ መስሎ ጉዳዩም ቀስ በቀስ ለመረሳት እስኪመስል ድረስ አንድ አመትን ሊደፍን ተቃርቧል።
አራቱ ክለቦች ላይ የእንጀራ እናት በሚመስል መልኩ ውሳኔን አሳልፎ አስራ ሁለቱን ክለቦችን ግን ልጆቼ ብሎ እንደዋዛ የተረሳ የሚመስለው ይህ ጉዳይ ቅጣት የተላለፈባቸው ክለቦች ገንዘብ ተቀጥተው ፣ ገንዘብ ወሰዱ የተባሉ ተጫዋቾች የወሰዱትን መልሰው ፣ በየወሩም ከደመወዛቸው እየተቆረጠባቸው አመት ሊሞላው በተቃረበበት በዚህ ወቅት አጣሪ ኮሚቴው ግን የቀሩትን አስራ ሁለቱን ክለቦች ዝም ብሎ ይገኛል።
- ማሰታውቂያ -
ለምን ዝምታ ተመረጠ ? አራቱ ክለቦች ላይ አጣዳፊ ውሳኔ ተወስኖ አስራ ሁለቱስ ለምን ዝም ተባሉ ? የተለየስ አዲስ ነገር ተፈጥሮ ወይንስ የማናውቀው ጉዳይ ኖሮ ነው ?


