የአቻ ውጤቶች ጥገኛ ፣ የጎል ረሀብ ያጠቃው ፣ 155 ተጫዋቾች ጎል ቢያስቆጥሩም ሀትሪክ ሰሪ ተጫዋችን የናፈቅንበት ፣ በአወዛጋቢ ዳኝነት የታጀበውን እና በፀሀያማ ሰዓት ጨዋታዎች የተደረጉ ጨዋታዎች እንዲሁም አስገራሚ ተጫዋቾችን ያስመለከንን የሊጉን አንደኛ ዙር ከሌሎች ሀሳቦች ጋር በቀጣይ ሁለተኛው ዙር መኖር ስለሚገባቸው መፍትሄዎች ይህንን ፅሁፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ከ2017 ሐምሌ አጋማሽ ወር አንስቶ የተከፈተውን የዝውውር መስኮት ተንተርሶ በሊጉ የሚሳተፉ ሀያ ክለቦች 921 ሚሊዮን ብር በማውጣት 484 ተጫዋቾችን በዝውውር ካስፈረሙ በኋላ ጥቅምት 8 ሲል የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2018 የውድድር ዘመን ከሦስት ወራት በላይ ያስቆጠሩ የውድድር ጊዜያትን አሳልፎ የካቲት 2/2018 ከተደረገው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ በኋላ 190 ጨዋታዎች የተደረጉበት የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን አንደኛውን ዙር ማገባደዱም ይታወሳል። ከአምስት አመታት በኋላ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከናፈቀው ሊግ ጋር በተገናኘበት እና እንደተለመደው የሀዋሳ እና አዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳዎች ባሰናዷቸው የሊጉ የመጀመሪያው ዙር መርሀግብሮች ከመልካም ጎኑ ይልቅ በብዙ እፀፆች ታጅቦ መገባደድ የቻለ ነበር።ከዕረፍት መልስ ባሉ ደቂቃዎች በይበልጥ ጎል በተቆጠረበት እና 155 ተጫዋቾች ጎል አስቆጥረው ሀትሪክ የሰራ ተጫዋችን ያላስመለከተንን የዙሩን ውድድር በተከታይ መልክ ተመልክተነዋል።
በጠራራ ፀሀይ የተደረጉ ጨዋታዎች እና የክለቦች ቅሬታ
ሊጉን ከአመታት በኋላ ያሰናዳው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከናፈቀው ውድድር ጋር ዳግም የመገናኘች ዕድሉን አግኝቶ ለመዲናይቱ የእግር ኳስ ወዳዶች ደረስኩላችሁ ቢልም የሰዓት ጉዳይ ግን ክለቦችን አሳስቦናል የሚል ድምፅን ሲያሰሙ ተደምጧል። ምንአልባት አንጋፋው ስታዲየም የአመሻሽ ጨዋታዎች ለማስተናገድ ፓውዛ አለመኖሩ የሰባት ሰዓት ጨዋታዎችን እንዲደረጉ ያስገደደ ቢሆንም የክለቦች ጠጠር ያለ ቅሬታን ግን አወዳዳሪው አካል በአፅንኦት ሊመለከተው የሚገባ ጉዳይ መሆን ያለበት ይመስላል። ምን አልባት ሊጉን ፀሐያማ በሆነ እና ተመልካቾች ራሳቸውን በስራ በሚወጥሩበት ሰዓት ላይ መደረጉ ከዚህ በፊት በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም መመልከት የቻልን ሲሆን በጥቅሉ ግን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች አመቻችቶ የሰዓት ማሻሻያ ሊደረግበት ግድ ይላል።
- ማሰታውቂያ -
የጎል ያለህ ብሎ አፍ ያወጣው ሊጋችን
ሀያ ክለቦችን በያዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ክለቦች በተጋጣሚያቸው ላይ ጎል የሚያስቆጥሩት በአማካይ 1.6.8 ሲሆን ይህም ማለት አንድ ተጫዋች በተጋጣሚ ቡድን ላይ ከሁለት መዝለል ያልቻለ ጎልን ከመረብ ያሳርፋል ማለት ነው። ከሦስት ወራት በላይ በሦስት የተለያዩ ሜዳዎች ላይ 190 የሊግ ጨዋታዎች መደረግ የቻሉ ሲሆን 80 ያህሉ በአቻ ውጤቶች መጠናቀቅ ችለዋል። እንደ አጥቂ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በይበልጥ ከቆሙ ኳሶች እንዲሁም በግል ጥረቶቻቸው ባስቆጠሯቸው በዕኩሌታ 8 ጎሎች አማካኝነት የሊጉን የጎል አስቆጣሪነት ደረጃን መምራት ቢችሉም ፕሪምየር ሊጉ ካለው ከፍ ያለ የጨዋታ ቁጥር አንፃር ግን የተቆጠሩት ጎሎች በእጅጉ ደካማ እንደሆኑ ከላይ የጠቀስነው የአቻ ውጤቶች ቁጥር ማየት የምንችል ሲሆን በይበልጥ ደግሞ አብዛኞቹ ጨዋታዎች 0ለ0 መቋጨታቸው ልብ ይለዋል። በተለይ ለዚህም እንደምክንያት የሚቆጠረው ክለቦች በይበልጥ በመከላከል ያመዘነውን አቀራረብ ይዘው መግባታቸው እንዲሁም አማካዮች ለአጥቂዎች በበቂ ሁኔታ ኳሶችን የማቀበል ውስንነቶች ተደማምረው ሊጉ አፍ አውጥቶ በዙሩ የአቻ ያለህ እንዲል አስገድዶታል።
የሊጉ ክለቦች ቁጥራዊ መረጃዎች
የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ካስተናገደው የመጀመሪያው ዙር 190 ጨዋታዎች ውስጥ 80 ያህሉ ጨዋታዎች በአቻ ውጤቶች መጠናቀቅ የቻሉ ሲሆን ባህርዳር ከተማ በ12 ቀዳሚው ሲሆን አዳማ እና ወላይታ ድቻ በዕኩል ቁጥር 10 አቻዎችን በመውጣት ይከተላሉ። በሊጉ 322 ጎሎች መቆጠር የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 22 ጎሎችን አስቆጥሮ በተቃራኒው ግን 24 ጎል በማስተናገድ ቀዳሚው ሲሆን መቐለ ፣ ወልዋሎ እና አርባምንጭ 22 ወላይታ ድቻ 21 ፣ አትዮጵያ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና በበኩላቸው 20 ጎሎችን በማስተናገድ ተከታትለው መቀመጥ ችለዋል። በሊጉ ሲዳማ ቡና እና መቻል 24 ጎሎችን በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ ሲያስቆጥሩ ሀዋሳ ከተማ እና ንግድ ባንክ 22 ነገሌ አርሲ በበኩሉ 21 ጎሎች ያስቆጠሩ ቢሆንም መሪው ሲዳማ ቡና 14 ተከታዩ ሀዋሳ 12 እና ሦስተኛ ላይ የሚገኘው ነገሌ አርሲ 9 ከዕዳ ነፃ የሆነ ንፁህ ጎሎችን ይዘው ይገኛሉ። በሊጉ የ19ኝ ሳምንት ቆይታ አንድ ብቻ ጨዋታ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ 9 ጨዋታዎችን በመሸነፍ ቀዳሚው ክለብ መሆን ሲችል ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ በበኩላቸው በ8 ሽንፈቶች ይከተላሉ። በሊጉ ከተደረጉ 190 ያህል ጨዋታዎች 110 ያህሉ በመሸናነፍ መቋጨት የቻሉ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ እና ነገሌ አርሲ ዕኩል አስር ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ ሲዳማ ቡና 9 ፋሲል እና መቻል በበኩላቸው 8 ጨዋታዎች ያሸነፉ ክለቦች ሆነዋል።
አፍጥጦ የወጣው የዳኝነት ችግር እና መፍትሄው
ዘንድሮ ትኩረትን ከሳቡ ጉዳዮች ዋነኛው ከዳኝነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው። ሀያ ክለቦች እየተካፈሉ ባለበት እና አራት ክለቦች ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን በሚወርዱበት ውድድር ላይ ክለቦች በድግግሞሽ በዳኛ ላይ ቅሬታን ሲያሰሙ ከጨዋታ ጨዋታ መመልከት እንደተለመደ አንደኛው ዙር ተገባዷል። በ190 የሊግ ጨዋታዎች ዳኞች 863 ቢጫ ካርዶችን ሲመዙ 44 ቀይ ካርዶች በመስጠትም ተጫዋቾችን እና የቡድን አበላትን ከሜዳ አስወግደዋል። ከተሰጡት ካርዶች መካከል በአማካይ 20% ያህሉን ዳኞች በራሳቸው ያልተገባ ዕይታ የሰጧቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ተጫዋቾች በጥፋታቸው ያገኟቸው ናቸው። በሌላ በኩል ሜዳ ላይ አንድ ተጫዋች በሌላኛው የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ አደገኛ እና የተጫዋቹን ህይወት የሚያበላሹ ጥፋቶችን እየተሰሩ ዳኞች በዝምታ ያለፉባቸውም ወቅቶች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ጉዳዮች በተጨማሪ ረዳት ዳኞች ከጨዋታ ውጪ ያልሆኑ ኳሶችን በእጅ ባንዲራቸው በማመልከት ያልተገቡ ውሳኔዎችን ሲወስኑ በጥቅሉም የመሐል ዳኞች የገቡ ግልፅ ጎሎችን ያለምንም ምክንያት ሲሽሩ በእጅ የተቆጠረ ጎልን ደግሞ ሲያፀድቁ ያስተዋልንበትን ሳምንታት አሳልፈንበታል። ዳኞች በዘመነው የእግር ኳስ አለም የአጋዥ መሳሪያዎች በራሳቸው ብርቱ ጥረት ጨዋታዎችን መምራታቸው የሚያስመዘግናቸው ቢሆንም ቀጣዩ የሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ግን ለዋንጫ እና ላለመውረድ የሚደረጉ ፉክክሮች እንደመብዛታቸው ከፍ ያለ ትኩረትን በመሻቱ የዳኞች ኮሚቴ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ይጠበቃል። በመጀመሪያው ዙር ግን በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ፣ፌድራል ዳኛ መለሠ ንጉሴ እንዲሁም በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ፌድራል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ አየለ በአንፃራዊነት በተቻላቸው መጠን በሊጉ ላይ ጥንቃቄን መርጠው በመዳኘነት የተለየ አቀራረብ የነበራቸው ዳኞች እንደነበሩ መታዘብ ችያለሁ።
አዳዲስ ተጫዋቾችን የተዋወቅንበት እና ነባሮቹ የደመቁበት
ሊጉ ምንም እንኳን በየአመቱ አዳዲስ ፊቶችን በማስተዋወቁ የሚታማ መሆን ባይችልም የያዝነው አመት ግን በተለይ ዕድሜያቸው ለጋ የሆነ ወጣት እና ተስፈኛ ተጫዋቾችን አይተንበታል። ዘንድሮ በሊጉ ክስተት በሆነው አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ ውስጥ እየፈካ የሚጓዘው የመስመር አጥቂው ከቤ ብዙነህ በልዩነት ሁሉም የሚስማማበት ኮከብ ሲሆን እዚሁ ክለብ ላይ እንደ ርሆቦት ሰለሎ እና ዘሩባቤል ሞላ አይነቶቹ ከባለ ልምዶቹ ዳዊት ተፈራ ጋር በጥምረት ለቡድናቸው የተለዩ ነበሩ። የሀዋሳዎቹ ብሩክ ያሬድ ፣ ናትናኤል ሻጋሞ እና የአብስራ ደግፌ ፣ የጊዮርጊሶቹ ሀብታሙ ጉልላት ፣ ብሩክ ታረቀኝ እና የአብስራ ጎሳዬ ፣ የፋሲል ከነማው ዳግም አወቀ ፣ የመድኑ ዳዊት አውላቸው ፣ የሸገሩ አሚር አብዶ እና አቤኔዘር ህስቄል ፣ የንግድ ባንኩ በዛብህ ካቲሶ ፣ የኤሌክትሪኩ ሀሰን ሁሴን ፣ የባህርዳሩ ማንያዘዋል ካሳ ሊጉን ያደመቁ አዳዲስ ፊቶች መሆን ሲችሉ ባለ ልምዶቹም እንደ አዲስ መወለዳቸውን አስመስክረዋል። የንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ፣ የሽረው አይደክሜው ሽመክት ጉግሳ ፣ የሲዳማዎቹ መስፍን ታፈሠ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና ያሬድ ባዬ ፣ የባህርዳሮቹ በረከት ጥጋቡ እና ሔኖክ ይበልጣል ፣ የመቐለው ፍፁም አለሙ ፣ የመቻሎቹ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ አለምብርሀን ይግዛው እና ፈቱዲን ጀማል ፣ የድሬዳዋው አህመድ ረሺድ እና ከጉዳት የተመለሰው መሀመድ ኑስናስር ፣ የሀዋሳዎቹ ሽመልስ በቀለ ፣ ጌታነህ ከበደ ወደ መጨረሻም ቢሆን ተባረክ ሄፋሞ ፣ የሸገሮቹ ሔኖክ አዱኛ እና ፍቅሩ አለማየሁ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ የሀዋሳው ሰይድ ሀብታሙ ፣ የነገሌው እንድሪሱ አብዱላሂ ፣ የፋሲሉ ሞይስ ፓዎቴ እና የአዳማው አላዛር ማርቆስ በሊጉ ዳግም ያንፀባረቁ ኮከቦች ሲሆኑ ከሴካፋው ከ17 አመት ብሔራዊ ቡድናችን በድንገት ወደ ሊጉ የመጡት የሸገሮቹ ዳዊት ካሳው እና ቢኒያም አብርሀ እንዲሁም የንግድ ባንኩ ሁዘይፋ ሻፊን ጨምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድምቀት መሆን የቻሉ ወጣቶች ነበሩ።
ካለፈው አመት አንፃር የክለቦች አቋም
እጅግ ከፍ ያለ የጨዋታ ቁጥር ባለበት የያዝነው የውድድር ዘመን እንደ ነገሌ አርሲ አይነት አዲስ ግን ጠንካራ ክለብን ያስመለከተን ሲሆን ካለፈው አመት ስህተታቸው መማር ያልቻሉ ክለቦችንም በተቃራኒው ያስተዋልንበት ነበር። መውረድ ኖሮ ቢሆን ኖሮ በሊጉ የማንመለከታቸው ወልዋሎ እና መቐለ በቆሙበት የቀሩ ሲመስሉ አርባምንጭ ከተማም በወራጅ ቅርቃር ተሰንቅሮ ቀጣዩ ዙር ለመጠበቅ የተገደደ ክለብ ሆኗል። ከጠንካራነቱ ላልቶ ላለመውረድ በመጫወት ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ሻምፒዮን ሆኖ በአመቱ በተቃራኒው ወደ ታች ቁልቁል እየተመለከተ የሚገኘው እና ከወትሮ አቋሙ ወረድ ያለው ባህርዳር ከተማ በሁለተኛው ዙር ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ክለቦች ናቸው። በብዙ ነገር ተለውጠው የመጡት ሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ እንዲሁም መቻል ከነማ በይበልጥ ከፍ ባለ የዋንጫ ተሳትፎ ውስጥ የሚጠበቁ ክለቦች መሆናቸውን ባጠናቀቁት የዙር ተሳትፎአቸው መታዘብ ችለናል። ከላይ እነኚህን ቡድኖች ጠቀስን እንጂ እንደ የወጥነት ችግር የሚታይባቸው እንደ አዳማ ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሀድያ ሆሳዕና ፣ ድሬዳዋ ፣ ሽረ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ንግድ ባነክ እና ሸገር ከተማ በደንብ መሻሻል የሚጠበቅባቸው ክለቦች ናቸው። በአጠቃላይ ግን በሊጉ ከመሪው ሲዳማ ቡና ሀያኛ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ድረስ በሂሳባዊ የመውረድ ስጋት ያለባቸው ሲሆን ከዚህም መነሻነት ቡድኖች ቀዳዳቸውን ደፍነው በብርቱ እንደሚፎካከሩ ይጠበቃል።
37 የውጪ ተጫዋቾች ምን ሰሩ ?
በፕሪምየር ሊጉ 37 ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን የተመለከትን ሲሆን 13 ደግሞ ግብ ጠባቂዎች ናቸው። በንፅፅር የተጫዋቾቹ ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም እንደ ቁጥሩ መጠን ለቡድኖቻቸው ግልጋሎታቸው እምብዛም ሆኖ እናገኘዋለን። በግብ ጠባቂዎች ቦታ እንደ ካሜሮናዊው የፋሲል የግብ ዘብ ሞይስ ፓዎቴ ፣ የነገሌው ጋናዊው እድሪሱ አብዱላሂ እና ሌላኛው ጋናዊ አንድሬ አዩ በምድረገነት ሽረ ፣ የባህርዳሩ ሴኔጋላዊ ፔፕ ሰይዶ ከአዳማው አላዛር ፣ ከሀዋሳ ሰይድ ሀብታሙ እና ከሸገሩ ባህሩ ነጋሽ ጋር በሊጉ ጥቂት ግቦችን ያስተናገዱ ጥሩ ሳምንታት ያሳለፉ ሲሆን በአጥቂ ቦታ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ናይጄሪያዊ አጥቂ አቡበከር አዳሙ እና ለማዳው ዩጋንዳዊ ሳይመን ፒተር በንግድ ባንክ በኩል 6 እና 5 ጎሎችን በማግባቱ ጥሩ ቆይታን ሲኖራቸው የነገሌው ካሜራናዊ ተከላካይ ዴዜሪ ፓስካል እና የፋሲሉ ዩጋንዳዊ ዋሳዋ ጂኦፎሪ ከሀገራችን ተጫዋቾች ጋር በቅንጅት የተሻለውን ጊዜ ሲያሳለፍ የተቀሩት ግን ምንም ሲፈይዱ ለመመልከት አልታደልንም።
እንደ ትዝብት ጠቅለል ባለ መልኩ ከላይ ውስን ሀሳቦች እናንሳ እንጂ ሌሎች ደካማም ይሁን ጠንካራ ጎኖችን ማስተዋል የቻል ሲሆን ሊጉ በብዙ ነገሮች በአዳዲስ የዝውውር ጉዳዮችን ካጠናቀቀ በኋላ ለሀገር ውስጥ ስርጭት መብቱን ሽጦ በOBN በጥራት በመጀመሪያው ዙር የተላለፈው ጨዋታ በአዳማ እና ሀዋሳ ከተሞች ላይ ሁለተኛው ዙር የካቲት 14/2018 በይፋ ሲጀመር በሁለቱም ከተሞች ጨዋታዎችን ማስተላለፋቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።


