የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የምስል እና የስያሜ መብት ስፖንሰር ሺፕ ስምምነትን በስካይ ላይት ሆቴል ዛሬ ፈፅሟል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ለቀጣዮቹ ዓመታት በጣምራ አብረውት ከሚሰሩ ሁለት ተቋማት ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነነትን በዛሬው ዕለት ከሰዓት በስካይ ላይት ሆቴል ፈፅሟል። በስፖንሰርሺፕ ስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ፣ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሀ በላይነህ የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ክፍሌ ሰይፈን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ጋዜጠኞች በስፍራው በመገኘት ስነ ስርዓቱን ታድመዋል።
አምስት አመታትን ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካገኘበት የዲኤስቲቪ ቆይታው ወደ ሀገር ውስጥ ጣቢያ ፊቱን ያዞረው አክሲዮን ማህበሩ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከኦቢ ኤን ጋር አብሮ በመስራት የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ ለማሰራጨት የተስማማ ሲሆን ስርጭቱም በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች ለተመልካቾች ተደራሽ እንደሚሆን በመድረኩ ተጠቁሟል። ሀያ ክለቦች በሚካፈሉበት የዘንድሮው የሊግ ውድድር ከሚከናወኑ 380 ጨዋታዎች ተቋሙ 250 ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ ዕቅድ መያዙን ነገር ግን በቀጣይ እየታየ የሚጨመር ነገር ሊኖረው እንደሚችል ሲገለፅ ለጊዜው ግን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚከናወኑ ጨዋታዎች ሽፋን ሲያገኙ በሀዋሳ የሚኖሩት ጨዋታዎች ግን በአክሲዮን ማህበሩ የፌስቡክ ገፅ ላይ ይተላለፋሉም ተብሏል።
በሌላ በኩል ከቤትኪንግ አቋማሪ ድርጅት በኋላም ፕሪምየር ሊጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስያሜ መብቱ እንደተገዛ ዛሬ በነበረው ሌላ ስምምነት ተጠቁሟል። በዚህም መሠረት ፕሪምየር ሊጉ ላይ የሚካፈሉ ሁሉም ክለቦች በግራ መለያቸው ላይ የንግድ ባንክን አርማ የሚለጥፉ ሲሆን ሊጉም CBE የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተብሏል። ጨዋታዎቹን ከOBN ውጪ መቅዳትም ሆነ መቅረፅ እንደማይቻል የጣቢያው ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍስሃ በላይነህ የገለፁ ሲሆን ጨዋታዎቹ በተለያዮ የሚዲያ ፕላት ፎርሞች ማለት ( ቲክቶክ፣ፌስቡክ እና ዮቲዮብ ላይ ጣቢያው እንደሚያስተላፉ ከጠቆሙ በኋላ በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ተስጥቷቸዋል።
- ማሰታውቂያ -



