የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር ባሳለፍነው ቅዳሜ ያካሄደውን 6ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ በዛሬው መግለጫ ሰጥቷል።
በሊግ አክስዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ስራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋዜጣዊ መግለጫውን በጋራ ሰጥተዋል።
በጉባኤው ላይ ተለይተው ሰባት አጀንዳዎች የተነሱ ሲሆን በነሱ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉ ተግልጿል።
አክስዮን ማህበሩ በ2016 ዓመተ ምህረት ከ265,552,342.50 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱን በመጥቀስ ለክለቦች 195,533,491.87 ማከፋፈሉ ተመላክቷል።
- ማሰታውቂያ -
በተጨማሪም ለመንግስት ከ34 ሚልየን ብር በላይ ግብር በመክፈል በሀገሪቱ ከሚገኙ 500 በላይ ተቋማት ጋር ምስጉን ግብር ከፋይ ተቋም በሚል መሸለማቸውን አንስተዋል።
በጉባኤው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የክለቦች የፋይናንስ ስርዓት አንዱ መሆኑም ተጠቅሷል። ይህንን አስመልክቶም የተወሰኑ ክለቦች የውድድር ዘመኑ ሻምፒዮን እና ወራጅ ቡድን መኖር የለባቸውይ በሚል መጠየቃቸውን መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ገልፀዋል።
ለዚህም ክለቦቹ እንደ ምክንያት ያነሱት እኛ ደንቡን አክብረን እየሰራን በመሆኑ እና ሌሎች ክለቦች ደግሞ ያንን አልተገበሩም በዚህም ተጎድተናል በሚል መሆኑ ተጠቅሷል።
የቦርድ ሰብሳቢው እንዳሉት ከሆነም አንዳንድ ክለቦች የመረጃ አሰጣጥ ላይ ክፍተት ነበረብን በሚል ተጫዋቾችን ያስፈረሙበት የገንዘብ መጠን ሁኔታን አንስተዋል።
ምንም እንኳን ደንቡ ሲወጣ በርካታ ክለቦች በደስታ ተቀብለው ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ቢናገሩም የአምናው ውድድር በተጠናቀቀ ማግስት ሶስት እና አራት ደንቡን መጣስ የጀመሩ ክለቦች ነበሩ ብለዋል።
በዚህም የክለቦችን ኃላፊዎቹ ጠርተን አናግረን ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል ነገር ግን ደንቡን ከመጣስ ወደ ኋላ አላሉም ሲሉ ተናግረዋል። ደንቡን የጣሱት የክለብ አመራሮች ለክለባቸው ሳይሆን ለግል ኪሳቸው በማሰብ ያደረጉት ነውም ብለዋል።
ይህንን ጉዳይ ለማጣራት ከፌዴራል ፖሊስ እና ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ጭምር ተወካዮች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም በተጫዋቾች ደረጃ 25 የሚደርሱ ተጫዋቾች ላይ ማጣራት በመደረግ ላይ መሆኑን ያነሱት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በተጫዋቾችም ሆነ በክለቦች ላይ ህጋዊ መስመሩን ተከትለን ቅጣት እናስተላልፋለን ፤ የስልክ ቅጂ ማስረጃዎች ሁሉ አሉን ደንቡን ጥሶ ከጥፋት የሚያመልጥ አይኖርም በሚል በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
ከክፍያ ጋር በተያያዘ የበርካታ ክለቦች አሰልጣኞች እና አመራሮች የተጨመላለቀ አሰራር ውስጥ ናቸው ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ምሳሌ በመጥቀስ ጭምር ያነሱት መቶ አለቃ ፈቀዳ ማሞ ከአንድ ተጫዋች በአመት እስከ አራት መቶ ሺህ ብር ድረስ ኮሚሽን የሚቀበሉ ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።
ከስታድየም ጋር በተያያዘ በአሁን ሰዓት ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው ስታድየም የድሬዳዋ ስታድየም ብቻ መሆኑ የጠቀሱም ሲሆን ሊጉን ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ንግግሮች በመደረግ ላይ ናቸው ብለዋል።
በተለይም ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ በተፈጠሩት ከስፖርታዊ መርህ ያፈነገጡ ተግባራት ምክንያት በአዲስ አበባ ላይ የእግርኳስ ጨዋታ ማድረግ ከባድ ነው በማለት የከተማ መስተዳድሩ ውሳኔ አሳልፏሉ ሲሉ ተናግረዋል።።
የቦርድ ሰብሳቢው አክለውም አስቀድሞ እነዚህ ሁኔታዎች ከመፈጠራቸው በፊት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በስታድየሙ አጠቃቀም ከስምምነት ተደርሶ ነበር ብለዋል። አሁን ላይ ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ወድድሩን በምን መልኩ ወደ መዲናዋ መመለስ ይቻላል በሚለው ላይ ንግግሮችን በማድረግ ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከቀጥታ ስርጭት መብት ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት መጨረሻ ውሉ የሚጠናቀቀው ሱፐርስፖርት በዓመቱ 72 ጨዋታዎችን ብቻ አስተላልፋለሁ ማለቱን በመግለፅ ቀሪ ጨዋታቸውን ከፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት በተሻገር ለማስተላለፍ በሚያስችል ሁኔታ ላይ ከሱፐርስፖርት ጋር በመነጋገር ላይ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል።
በያዝነው የ2017 ዓመት አክስዮን ማህበሩ በዋነኝነት በቀጣይነት የሊጉ የስያሜ እና የብሮድካስት መብት ሽያጭ ላይ በትኩረት የሚሰራበት ዋነኛ ተግባሩ መሆኑ በመግለጫው ተገልጿል።


