የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት ነገ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ የዘንድሮው ውድድርን ቀዳሚ 13 ሳምንታት በምታስተናግደው ድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል።
ቀደም ብሎ የኮከብ ተጫዋች ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ እና ኮከብ ወጣት ተጫዋች ዕጩዎች ይፋ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን የኮከብ አሰልጣኝ እና የምስጉን ዋና እና ረዳት ዳኛ ዕጩዎች ደግሞ ዛሬ ይፋ ተደርገዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለሊጉ ክብር ያበቁት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ፤ መቻልን እየመሩ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ለዋንጫ የተፎካከሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እና ኢትዮጵያ ቡናን ከ6ኛ ሳምንት ጀምሮ በመምራት ቡድን የ3ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ያስቻሉት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በዕጩ ዝርዝሩ ተካተዋል።
በዋና ዳኝነት ዕጩዎች አራት ዳኞች የታጩ ሲሆን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ፣ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ፣ አባይነህ ሙላት እና ኃይማኖት አዳነ ለዓመቱ ምስጉን ዋና ዳኝነት ዕጩ ሆነዋል።
- ማሰታውቂያ -
ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት ፣ ሲራጅ ኑርበገን ፣ ወጋየሁ አየለ እና ሙሉነህ በዳዳ ደግሞ በምስጉን ረዳት ዳኝነት ዕጩ ሆነው የቀረቡ ናቸው።