“ዲ.ኤስ.ቲቪ ፕሪምየር ሊጋችንን ሊያስተላልፍ መሆኑ ብዙ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች እንዲኖረን ያደርጋል” ኤልያስ ማሞ /ድሬዳዋ ከተማ/


በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሁን ላይ ለድሬዳዋ ከተማ ለመጫወት ቢችልም ከዛ በፊት በነበረው የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ላሳደገው ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ለብሔራዊ ቡድናችንም ጥሩ ብቃቱን በማሳየት ለመጫወት ችሏል፤ ይሄ ተጨዋች ኤልያስ ማሞ ሲባል ከእዚህ ተጨዋች ጋር ከኳስ ጋር በተገናኙ ጥያቄዎች ዙሪያ አጠር ያለ ቆይታን አድርገናል፡፡


ሀትሪክ፡- ኮቪድ ወደ አገራችን ገባና ከኳሱ ራቅክ፤ ያለፉት ወራቶች እንዴት ታለፉ?
ኤልያስ፡- ከእዚህ በፊት በእንደዚህ አይነት መልኩ ለበርካታ ወራቶች ያለ ኳስ የቆየሁበት ጊዜ ፈፅሞ አልነበረምና በጣም ከባድ ጊዜያትን ነው ያሳለፍኩት፤ ቤት ሆኜ ስፖርትን ብቻ እሰራ ነበር፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ሰፈር ውስጥ ያለ ኳስ ዝም ብሎ አንድ አንድ እንቅስቃሴዎችንም የማደርግበት ሁኔታ ስለነበር ያን በአሰልቺነቱም የምጠቅሰው ነው፡፡

 

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ለቅ/ጊዮርጊስ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለኢትዮጵያ ቡናና አሁን ደግሞ ለድሬዳዋ ከተማ እየተጫወትክ ይገኛል፤ በእነዚህ ቡድኖች ቆይታህ ጥሩ ጊዜን አሳለፍክ? ደስተኛስ ነበርክ?
ኤልያስ፡- አዎን፤ በእግር ኳስ ህይወቴ አሁንም ድረስ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በተጫወትኩባቸው ቡድኖቼ ውስጥም ጥሩ ጊዜን ነው ለማሳለፍ የቻልኩት፤ በተለይ ደግሞ በቅ/ጊዮርጊስ ቡድን የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ከስር በማደግ በወጣትነት እድሜዬ በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ ታዋቂ እና ትላልቅ ተጨዋቾች ጋር የመጫወት አጋጣሚዎችን ያገኘሁበት ምርጥ ወቅት ስለነበር ያንን ፈፅሞ የማልረሳው ነው፡፡

 

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ታሪክ ብቸኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ተሸልመሃል፤ ስለዛ ክብርህ ወደኋላ መለስ ብለህ ምን የምትለን ነገር ይኖርሃል?
ኤልያስ፡- በኢትዮጵያ ደረጃ ከእኔ በፊት እንደዚህ አይነት ሽልማትን ያገኘ ተጨዋች ይኑር አይኑር ባላውቅም ሀገራችን ላይ በተካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ /ሴካፋ/ ዋንጫ ላይ ያኔ ይህን ሽልማት ሳገኝ የተሰማኝ የደስታ መጠን በጣም ከፍተኛ ነበር፤ እስከዛሬ በሀገራችን ከሚገኙት ተጨዋቾች ደግሞ ይህን ሽልማት ያገኘ ብቸኛው ተጨዋች ለመሆን መቻሌም ደስታዬን እጥፍ ድርብም ነው ሊያደርግልኝ የቻለው፡፡

 

ሀትሪክ፡- በጊዜው በነበረው የሴካፋው የውድድር ተሳትፎአችን የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማቱን አገኛለው ብለህ ጠብቀህ ነበር?
ኤልያስ፡- በፍፁም፤ ያኔ ሽልማቱን ስቀበል እንደውም ያልጠበቅኩት ስለነበር በጣም ደንግጬ እንደነበርም ነው የማስታውሰው፡፡

 

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን በምትፈልገው ደረጃ ተጫውተህ አልፈሃል?
ኤልያስ፡- በእዛ ደረጃ ብዙም አልተጫወትኩም፤ ይህን ለማለት ያስቻለኝም አሁን ላይ የሚታየው የኳሳችን ሁኔታ እንደበፊቱ ስላልሆነና በጣም አስቸጋሪም ስለሆነ እንደዚሁም ደግሞ ሁሉም ውጤት ላይ ብቻ በማተኮር ለኳሱ በቂ ትኩረት እየተሰጠው ባለመሆኑና የመዘናጋት ነገርም ስላለ እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው በበቂ ሁኔታ ኳሱን እንዳልጫወት ያደረገኝ፡፡

 

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ስለ ቀጣይ ጊዜ እቅድህ ምን ትላለህ?
ኤልያስ፡- በእግር ኳሱ መሄድና መድረስ ያለብኝ ቦታ አሁንም ድረስ ለመጓዝ ጠንክሬ እየሰራው ነው፤ የእዚህ ዓመት ላይም በፊት ከነበረኝ ብቃት በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘትም ከፍተኛ ፍላጎቴ ነውና ለዛ ራሴን ከወዲሁ እያዘጋጀሁትም ነው የምገኘው፡፡

 

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ ምን አይነት የውድድር ዘመንን ያሳልፋል?
ኤልያስ፡- ባሳለፍነው ዓመት ተሳትፎአችን የተለያዩ ችግሮች ነበሩብን፤ ክፍተቶቻችንም ሰፊ ነበሩ፤ ዘንድሮን ስናይ ደግሞ ቡድናችን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ለበርካታ ወራቶች ከሜዳ ከመራቃችን አንፃርና ቡድናችንንም የተቀላቀሉት ተጨዋቾች አዳዲስ ስለሆኑም ከባድ የውድድር ጊዜን የምናሳልፍ ነው የሚመስለኝ፡፡

 

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እየቻለ ያልተሳካለት ተጨዋች የምትለው ማንን ነው?
ኤልያስ፡- ብዙ አሉ፤ ለእንደዚህ አይነት ተጨዋቾች ብዙ ትኩረት ስለማይሰጥ ወደፊትም ብዙ ተጨዋቾችም በየክለቡ ውስጥም ይኖራሉ፤ በተለይ ደግሞ የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ተስፋ ቡድኑ ላይ የነበሩት ተጨዋቾች በትልቅ ቡድን ደረጃ መጫወትና የተሻለም ደረጃ ላይ መድረስ እየቻሉ ያ ሳይሳካላቸው በመቅረቱና በታችኛው ሊግ ደረጃም እንዲጫወቱ በመደረጉ ያ በጣሙን ይቆጨኛል፡፡

 

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዳግም መመረጥ አልናፈቀህም?
ኤልያስ፡- ናፍቆኛል፤ ለእዛም ስል በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎዬ ላይ ይህን የመመረጥ እድል በድጋሚ ለማግኘት እንደ ግልም ሆነ እንደ ቡድን ለክለቤ ድሬዳዋ ከተማ ጥሩ ለመንቀሳቀስ እየተዘጋጀው የሚገኘው፡፡

 

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ በዲ.ኤስ.ቲቪ ይተላለፋል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ኤልያስ፡- ይሄ ለአገራችን እግር ኳስ ጥሩ ነገርን ነው ይዞልን የሚመጣው፤ ከእዚህ በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ወይንም ደግሞ ጨዋታዎቹን በስፖርት ፕሮግራም ላይ ስንመለከት ቀረፃዎቹ ጥሩ እና ልክ አልነበሩም፤ ተጨዋቾቻችን ወደ ባህር ማዶ ተጉዘው የፕሮፌሽናል ተጨዋችነትን እድል ለማግኘት ፊልሞቹን እንደ መረጃ ቢያቀርቡ እንኳን እነሱነታቸውን በደንብ ለመግለፅ አዳጋችም ነው ሲሆንባቸው የነበረውና አሁን ላይ ግን ልክ በአንድ ወቅት ሀገራችን ላይ ተካሂዶ እንደነበረው የሴካፋ ውድድር ዲ.ኤስቲቪ የፕሪምየር ሊጋችንን ሊያስተላልፍ መሆኑ ብዙ ተጨዋቾቻችን በኤጀንቶቻቸው አማካኝነት ወደ ውጪ በመውጣት የሚጫወቱበትን እድል ስለሚፈጥርላቸው ይሄ ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው፡፡

 

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
ኤልያስ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎዬ ጥሩ ብቃቴን ይዤ በመቅረብ የእኔን ችሎታ ለመመልከት የሚመጡ ጓደኞቼን ለማስደሰት በሚገባ እየተዘጋጀው ነው፤ ከዛ ውጪ በኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደርስም ውዷ ባለቤቴ ከእኔ ጎን ሁሌም ባለመጥፋት የምታደርግልኝ እገዛ በቃላት ብቻ የሚገለፅ ባለመሆኑ እሷን ከቤተሰቦቼ ቀጥዬ አመሰግናታለሁ፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website