የዲ ኤስ ቲቪው የስፖንሰር ሺፕ ዋጋ 22.5 ሚሊዮን ዶላር ወይስ 68 ሚሊዮን ዶላር

የዲ ኤስ ቲቪው የስፖንሰር ሺፕ ዋጋ 22.5 ሚሊዮን ዶላር ወይስ 68 ሚሊዮን ዶላር

“22.5 ሚሊዮን ዶላር እንጂ 68 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚለው ስህተት ነው”

“ፌዴሬሽኑ የአክሲዮኑ አባል ባለመሆኑ ክፍያው አይመለከተውም ሀብታም አይደል ከዚህ ውል ምን ይጠብቃል?

አቶ ክፍሌ ሰይፈ/የፕሪሚየር ሊጉ ዋና ስራ አስኪያጅ/


በዮሴፍ ከፈለኝ

የደቡብ አፍሪካው ግዙፍ የሚዲያ ተቋም ዲ ኤስ ቲቪ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለቀጣዮቹ 5 አመታት የማስተላለፍ መብት መግዛቱ ይፋ ሆኗል፡፡ ከዚህ ስምምነት ጀርባ ግን የአሸናፊነቱ ዋጋ ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ አካላትም አሉ… ጨረታው ይፋ ሲደረግ ዲ ኤስ ቲቪ በ68 ሚሊዮን ዶላር አሸነፈ ነው የተባለው የሚሉት አካላት አሁን ለ5 አመታት አሸነፈ የተባለው የ22.5 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ስህተት ነው ተቀባይነት የለውም በማለት ይሞግታሉ፡፡ በርግጥ የስፖንሰርሺፑ ዋጋ ስንት ነው? 22.5 ሚሊዮን ዶላር ወይስ 68 ሚሊዮን ዶላር? የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፈ ምላሻቸውን ለሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ሰጥተዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ዲ ኤስ ቲቪ ጨረታውን ያሸነፈው በስንት ሚሊዮን ዶላር ነው?

ክፍሌ ፡- አዎ ልክ ነህ 22.5 ሚሊዮን ዶላር ለ5 አመት ይከፍላሉ፡፡ በውሉ መሠረት ዘንድሮ 4 ሚሊዮን ዶላር፣ በ2014 4.2 ሚሊዮን ዶላር፣ በ2015 4.5 ሚሊዮን ዶላር፣ በ2016 4.75 ሚሊዮን ዶላርና በውሉ የመጨረሻ አመት 2017 ደግሞ 5 ሚሊዮን ዶላር ለሊግ ካምፓኒው ለመክፈል ተስማምቷል፡፡ በዚህም ደስተኞች ነን፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን ባለው ሁኔታ ውሉ ተጠናቋል ማለት ይቻላል? /ቃለ ምልልሱን ያደረግነው ባለፈው ረቡዕ ነው/

ክፍሌ ፡- ማክሰኞ ዕለት ከዲ ኤስ ቲቪ ሰዎች ጋር ተገናኝተን አወራን የነበረንን ጥያቄ ጠይቀናቸው መልስ ሰጡን፡፡ ከዚያ እስከ አርብ ድረስ የውሉን ረቂቅ ያመጡልንና በቀጠርናቸው ሁለት ኢንተርናሽናል ጠበቆች አማካይነት እናስገመግማለን ከእነሱ በኋላ ለሊግ ካምፓኒው ቦርድ ቀርቦ እንመለከተዋለን፡፡ በርግጥ አልቋል ለማለት መፈራረም ይጠበቅብናል፡፡ በቀጣይ ትልቅ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅተን ስምምነቱን ይፋ የምናደርግ ሲሆን ምርጥ ፕሮግራም እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ እውነቱን ንገረኝ… የውል ስምምነቱ 22.5 ሚሊዮን ዶላር… ወይስ 68 ሚሊዮን ዶላር?

ክፍሌ፡- ከላይ ጠይቀኸኝ መልሼዋለሁ፤ 22.5 ሚሊዮን ዶላር ነው እንጂ 68 ሚሊዮን ዶላር የተባለው ስህተት ነው ትክክል የሆነ መረጃ አይደለም፡፡ 68 ሚሊዮን የተባለው የፕሮዳክሽን ወጪ፣ የአየር ሰዓት ወጪ፣ የትሬኒንግ ወጪ.. እነኚህ ሁሉ ተደማምሮ የተቀመጠ ነው፡፡ ለኛ በካሽ የሚገቡ አይደለም፡፡ ለምሣሌ ለአየር ጊዜው በአመት 5 ሚሊዮን ዶላር በ5 አመት ደግሞ 25 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላሉ.. እነኚህ የመሰሉ ወጪዎች ተደምረው 68 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል እንጂ ዋነኛ የስፖንሰርሺፕ ክፍያው 22.5 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የዚህ ስምምነት ህጋዊነት የተረጋገጠ ነው? ምን ጥቅሞችን ያመጣል?

ክፍሌ ፡- ለምሣሌ ካናል ፕሉስ በዓመት 1.3 ሚሊዮን ዶላር በአምስት አመት ሲባዛ እንኳን 7ሚሊዮን ዶላር አይደርስም፤ ከገንዘቡ ጋር ሽልማት እሰጣለሁ ያለው ሃሣብ ተካቶበታል ከዲ ኤስ ቲቪ ጋር በፍፁም አይገናኝም ከዲ ኤሲ ቲቪ ጋር በገባነው ውል መሠረት በቀጣዮቹ 5 አመታት ምርጥ ጋዜጠኞች ይፈራሉ፡፡ ምርጥ የካሜራ ባለሙያዎች ይኖሩናል፡፡ ምርጥ ጨዋታን የሚተነትኑ ባለሙያዎች… ይኖሩናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ አለም ላይ ያለው እድገት ወደኛ ሀገር ጎራ ይላል በውሉ መሰረት 22 .5 ሚሊዮን ዶላር እንወስዳለን ይህ ነው የተነገረው… 68 ሚሊዮን ዶላር ለ5 አመት አጠቃላይ የሚወጣ ነው የስፖንሰሩ ዋጋ ግን አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- እግር ኳሱ ከወጪ ወደ ገቢ ተዛወረ… ለሀገር አስተዋፅኦ አደረግን ብላችሁ በድፍረት መናገር ትችላላችሁ?

ክፍሌ፡- አዎ እንደ ሀገር አስተዋፅኣ እናደርጋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እንደቡና ላኪው እንደ ለሎቹ ለሀገሪቱ ገቢ እናስገኛለን፡፡ የእውቀት ሽግግርም እናደርጋለን፡፡ በዚያ ላይ ገንዘብ እየጨረሱ ነው የሚለውን ትችት እናጠፋለን፡፡ በዚህ ስራ ላይ ከ200-300 ሰዎች ይሳተፋሉ ለነኚህ ሁሉ የስራ እድል ፈጠርን ማለት ነው፡፡ የውጪም ምንዛሪ አስገኝተናል፡፡ ምርጥ ምርጥ ባለሙያዎች ይፈጠራሉ፡፡ ይሄ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ያሳያል፡፡ የጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ማለትኮ ይሄ ነው፤ ስታዲየም ይገነባል ወጣቶችን ተጠቃሚ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ስፖርት ውስጥ ያሉ ሰዎች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ይደረጋል… በቃ ትልቅ ጥቅም ያለው ስምምነት ነው፡፡ ገንዘቡን ተቀብለን ከክለቦቹ ጋር ተከፋፍሎ የመለያየት ነገር ብቻ አይደለም፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ክለቦቹ ገንዘቡን የሚያወጡበት የአፈፃፀም ሰነድ መመሪያ እያዘጋጀን ነው እንደተለመደው ዝም ብሎ አይወጣም፡፡

ሀትሪክ፡- ስምምነቱ እግር ኳሱን ከመንግሥት መዳፍ የማላቀቅ አቅም አለው ማለት ይቻላል?

ክፍሌ፡- አዎ…በአማርኛና በእንግሊዘኛ በዲ.ኤስ.ቲቪ ላይ ትንተና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በደንብ እናፈራለን፡፡ ክለቦቹ ደግሞ ፖሊስ አልመጣም ጨዋታውን እናቋርጣለን የሚሉት ነገር አይሰራም፡፡ የሚመለከተው አካል ጥንቃቄ እንዲያደርግ እናሳውቃለን፡፡ አላስፈላጊ ባህሪያት፣ ረብሻዎች ከአቅም በላይ ባልሆነ ችግር ጨዋታዎችን ማቋረጥ እንደማይቻል ለመንግሥትም እናሣውቃለን፡፡ አትራፊ ውል ከሆነ የፈረምንባቸው ደንቦችና ህጎች መከበር አለባቸው፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ክለቦችና እግር ኳስ ራሣቸውን መቻል አለባቸው ያሉትን የምንፈልገውና ጠንካራ ትግል አድርገን አትራፊ የምንሆንበት መንገድ ይቀየሳል፡፡ ውሉ ለሚዲያ ሲገለፅ ትላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲገኙ አድርገን ነው እስካሁን ባለው ጉዞ ደስተኞች ነን፡፡

ሀትሪክ፡- በሊግ ካምፓኒዎችና በክለቦች መሀል ባለው ገቢ ክፍፍል ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስሙ አልተካተተም… ለምንድነው ይሄ የሆነው?

ክፍሌ፡- ፌዴሬሽኑ ሲጀመር የሊግ ካምፓኒው የአክሲዮን አባል አይደለም ስለዚህ አይካፈልም

ሀትሪክ፡- የሀገሪቱ እግር ኳስ የበላይ ነው የሜዳው ባለቤትም ፌደሬሽኑ ነው ይሄ ከናንተ አቋም ጋር አይጋጭም?

ክፍሌ ፡- ሜዳውማ የመንግሥት ነው መንግሥትም ለመጠቀም እንዲቻል ይፈቅዳል ብለን እናስባለን፡፡ ዘንድሮ በኮቪድ 19 ምክንያት ሁሉም በጋራ የሚጠበቅበትን ያደርጋል እንጂ ከ2014 ጀምሮ የሜዳ ጉዳይ የሊግ ካምፓኒው የራስ ምታት አይደለም ክለቦቹ የራሳቸውን ሜዳ በኪራይም ይሁን በሌላ ውል ራሣቸው ናቸው የሚያዘጋጁትና ለሊግ ካምፓኒው የሚያሳውቁት.. ስፖርት ኮሚሽን ሜዳውን ለፌዴሬሽኑ ይስጥ አይስጥ አላውቅም፡፡

ሀትሪክ፡- የአዲስ አበባ ስታዲየም ሜዳ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ትራኩ ደግሞ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ስር ነው ያለው… ውድድር አታካሂዱም ቢሉም መጫወት እንደማትችሉ ታውቃለህ… ?

ክፍሌ ፡- አላውቅም… በእኛ በኩል ግን ሁሉም ክለብ የየራሱን ሜዳ የማሳወቅ ግዴታ ውስጥ ይገባል እንጂ ሜዳ የካምፓኒው ኃላፊነትና ችግር ሊሆን አይችልም የባለቤትነት ጉዳይ የክለቡ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ፌዴሬሽኑ ግን የአክሲዮኑ አባል ባለመሆኑ ክፍያው አይመለከተውም ሀብታም አይደል ከዚህ ውል ምን ይጠብቃል? ስለሜዳውም ካነሳህ የመንግሥት ነው የመንግሥት ከሆነ ደግሞ ጥቅሙ ለህዝብ እንጂ ለአንድ ድርጅት አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- ፊፋና ካፍ ፌዴሬሽኑን እንጂ እናንተን እኮ አያውቁም?

ክፍሌ፡- እውነት ነው እኛን አያውቁም… ከህጋዊ ተቋምነት አንፃር ካየነው መንግሥት እኛን ያውቃል፡፡ ፌዴሬሽኑም በሚገባ ያውቀናል ከመሬት ተነስተን አልተቋቋምንም ፌዴሬሽኑ ውድድር አካሄዱ ብሎ ስልጣን ሰጥቶን ተዋውለን የተመዘገብን ሕጋዊ አካል መሆናችንን ያውቃል፤ ክለቦቹ ከፈለጉ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ተነጋግረው አበበ በቂላ ስታዲየም ማስመዘግብ ይችላሉ ይሄ ግን የኛ ጉዳይ አይደለም አምናኮ ጅማ አባጅፋር ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተስማምቶና ተዋውሎ የዩኒቨርሲቲውን ሜዳ በስሙ አስመዝግቦ መጥቷል፡፡ ሁሉም ክለቦች ይህን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ታህሳስ 3/2013 ፕሪሚየር ሊጉ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፤ ፕሮግራሙ መቼ ይወጣል? ስታዲየሞቹስ መቼ ይታወቃሉ?

ክፍሌ ፡- የሚጠበቅብን ክፍያ ስላለ እሱን አስተካክለን በቅርብ ጊዜ ፕሮግራም አውጥተን ይፋ እናደርጋለን… ስታዲየሞቹን በተመለከተ መጀመሪያ የት ይካሄድ? ቀጥሎስ? የሚለውም ያኔ ይታወቃል ይህንንም ከዲ.ኤስ.ቲቪ. ጋር የግድ መነጋገር አለብን እነሱም መብት አላቸው ፡፡ በኛ ብቻ አይወሰንም የመጀመሪያ ውል እንደመሆኑ በዲ.ኤስ.ቲቪ በጥሩ መልኩ እንዲታይና የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለመላው አለም እንዲያሳይ እንጠብቃለን፡፡

ሀትሪክ፡- ጨርሻለሁ…የቀረ ነገር አለ?

ክፍሌ፡-እንግዲህ ገና እየሞከርን ነው በጥሩ ሁኔታ ይሄዳል ብለን እናምናለን እስከዛሬ ብር ለሌለው እግር ኳስ ዶላሩን አምጥተናል፤ ቢያንስ ብሩ ባይገባ ወረቀቱ እጃችን ላይ ደርሷል በቀጣይም ጥሩ ሥራዎች ተሰርተው የኳሱ እድገት ይታያል ብለን እናምናለን፡፡ አንድም ብር ያላስገኘውን እግር ኳስ ዶላር አምጥተንለታል ይሄም ያስደስተናል፡፡ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ከጎናችን እንደሚቆሙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 


ማስተካከያ

ባለፈው ቅዳሜ በወጣው ሀትሪክ ጋዜጣ ላይ ከሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በቃለ ምልልሱ ላይ ፌዴሬሽኑ የሊግ ካምፓኒው አባል ባለመሆኑ ክፍያው አይመለከትውም ሀብታም አይደል ከዚህ ውል ምን ይጠብቃል? በሚል የተጠቀሰው
ፌዴሬሽኑ የሊግ ካምፓኒው አባል ባለመሆኑ ክፍያው አይመለከትውም በሚለው ብቻ እንዲስተካከል ዝግጅት ክፍላችንን ጠይቀዋል እኛም ማስተካከያውን አስተላልፈናል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport