“በጅማ አባጅፋር ላይ የተቀዳጀነው ድል ቢያስደስተንም ወደምንፈልገው አቋማችን ግን ገና አልመጣንም”ኤልያስ ማሞ /ድሬዳዋ ከተማ/

የድሬዳዋ ከተማው ስኬታማ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ኤልያስ ማሞ በቤትኪንጉ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ቡድናቸው ጅማ አባጅፋርን በአስቻለው ግርማ እና በጁኒየስ ናንጄቦ ግቦች 2-0 የድል ውጤትን ከማግኘት አንፃር ማሸነፋቸው ቢያስደስተውም ከእንቅስቃሴ አንፃር ግን ቡድናቸው ወደ ሚፈለግበት ደረጃ እና አቋም ገና እንዳልመጣ ከሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ ጋር ባደረገው ቆይታ ሀሳቡን ገልጿል።

የድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከጅማ አባጅፋር ጋር ባደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን በመቆጣጠርም ሆነ የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል ከተጋጣሚው አንፃር ተሽሎ እና ለድል ከበቃባቸውም ግቦች መካከልም አንዱን አስቆጥሮ በግብ ቢመራም የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ ላይ ደግሞ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ከተጫወተ በኋላ መልሶ ደግሞ ቀደም ሲል ወደነበረው አጨዋወቱ በመመለስ ሌላኛዋን የድል ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን በአሸናፊነት ሊወጣ ችሏል።

ሀትሪክ ድረ ገፅ የድሬዳዋ ከተማውን አማካይ ከጨዋታው በኋላ ቡድናቸው በጅማ አባጅፋር ላይ ስለ ተቀዳጀው ድል፣ ስለ ግጥሚያው ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን ቆይታቸው እና ስለ ራሱም ጥያቄዎችን አንስተንለት ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ አጠር አድርጎ ሰጥቷል።

ከጅማ አባጅፋር ጋር ስላደረጉት ጨዋታ እና ስለተጎናፀፉት ድል?

“ጨዋታው ጥሩ እና ጠንካራ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ ከእነሱ በተሻለ መልኩ ተጫውተናል። የግብ እድሎችንም ፈጥረን አንዷን ልንጠቀምበት ችለናል። የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ደግሞ ቡድናችን ባለፉት ሁለት ግጥሚያዎቹ ከሽንፈት ከመምጣቱ አኳያ የመሪነቱን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት ከመፈለግ አኳያ ወደ ኋላ ስላፈገፈግን በምንፈልገው መልኩ ለመጫወት አልቻልንም። ከዛም መልሰን እንቅስቃሴያችንን ስለቀየርን በመልሶ ማጥቃት ጨዋታ ሌላኛዋን የድል ግብ አስቆጠርን። ባገኘነው የድል ውጤትም በጣም ተደሰትን”።

የድሬዳዋ ከተማ ጠንካራ እና ደካማ ጎን?

“በሊጉ ተሳትፎአችን በጠንካራ ጎንነቱ የተመለከትኩት ነገር ቢኖር ተሸነፍንም አሸነፍንም ወደፊት አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ያለን መሆኑ ነው፤ በተቃራኒ ቡድን የግብ ክልልም በተደጋጋሚም መድረሳችንም በጥሩ ጎንነቱ የሚነሳም ነው፤ እንደዛም ሆኖ ግን የምናገኛቸውን የግብ አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን ደግሞ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛልና ይሄን የቡድናችንን ክፍተት ወይንም ድክመት በፍጥነት ልናርመው ይገባል”።

ድሬዳዋ ከተማን ከአምናው አንፃር ስትመዝነው?

“የአሁኑ ቡድናችን ከተጨዋቾች ስብስቡ አንስቶ ጥሩ እና በብዙ መልኩ ከአምናው ከፍተኛ ለውጥ ያለው ነው። ጥሩ እንቅስቃሴን በማድረጉም በኩል ተሻሽለናል”።

የድሬዳዋ ከተማ ክለብን በምን መልኩ ለመጥቀም እንደተዘጋጀ እና ዘንድሮ ስለሚያመጡት ውጤት?

“በድሬዳዋ ከተማ ክለብ ውስጥ ያለኝ ቆይታ ጥሩ እና የወደድኩት ነው። ከዛም በመነሳት ዘንድሮ በሚኖረኝ የቡድኑ ተሳትፎ ከአምናው በተሻለ ብቃቴን አሳይቼ ክለቤን ለመጥቀም ተዘጋጅቻለው። ቡድናችንን በተመለከተም በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ለውጤታማነት በመጫወት ጠንካራ ተፎካካሪም እንሆናለን”።

ስለ ቀጣዮ ጨዋታቸው?

“እኛ ለሁሉም ግጥሚያ ነው ትኩረት ሰጥተን ወደ ሜዳ የምንገባው። አጥቅቶ የሚጫወት ቡድኝ ስላለንም አላማችን እያንዳንዱን ጨዋታም አሸንፎ ለመውጣት ነው”።

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team