በ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ አምስተኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከአምስት ቀናት በኋላ የሚገጥመው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ይፋ ተደርጓል።
በአሰልጣኝ ሆሳም ሀሰን የሚመራው ቡድኑ ድንቅ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ላይ የሚገኘው የሊቨርፑሉ ሞ ሳላህን ፣ የማንችስተር ሲቲው ኦማር ማርሙሽ ፣ የናንቲሱን ሙስጠፋ መሐመድን እንዲሁም የኒሱን መሀመድ አብደልሞነምን ከአውሮፓ ሊጎች አካቷል።
በተጨማሪም በኳታር ሊግ የሚጫወቱት ሀምዲ ፋትሂ እና መሐመድ ትርዝጌትም በሆሳም ሀሰን ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ናቸው።
ከሀያ አራት ተጫዋቾች አስራ ስምንት ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ ባደረገው የፈርኦኖቹ ስብስብ የሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች አል አህሊ እና ዛማሌክ አምስት አምስት ተጫዋቾችን አስመርጠዋል።
- ማሰታውቂያ -
በመጪው አርብ ምሽት በሞሮኮ ካዛብላንካ ላርቢ ዛውሊ ስታድየም ላይ ዋልያውን የሚገጥመው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት ልምምዱን ይጀምራል።



