በቅርብ ዓመታት ላይ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ከተመለከትናቸው ባለ ድንቅ ክህሎት ተጫዋቾች መካከል አንዷ ናት።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከታታይ ዓመታት በድል ከተጓዘች በኋላ ከሁለት የቡድን አጋሮቿ ጋር በመሆን የታንዛኒያውን የያንጋ አፍሪካ የሴቶች ቡድን ያንጋ ፕሪንሰስን ተቀላቅላለች።
ለአምስት ወራት ያህል ከቡድኑ ጋር ልምምዶችን ብቻ እየሰራች ቆይታለች።
በመጨረሻም በቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገችበት መርሐግብር አንድ ግብ አስቆጥራ አንድ ደግሞ አመቻችታ አቀብላለች።
- ማሰታውቂያ -
በተከታታይ ጨዋታዎችም ደንቅ አቅሟን እያሳየች በመቀጠል ከታንዛኒያውያን የእግር ኳስ ወዳጆች በእጅጉ እየተሞገሰች ትገኛለች።
ከቀናት በፊትም ቡድኗን ለዋንጫ በማብቃት በሀገሯ የለመደችውን ዋንጫ ድንበር ተሻግራም አንድ ብላ መቁጠር ጀምራለች።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የዩጋንዳ አቻውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ባለፈበት የአበበ ቢቂላው ጨዋታ ቀዳሚውን ግብም ማስቀጠሯ አይዘነጋም።
አረጋሽ ካልሳ !!!
የሉሲዎቹ እና የያንጋ ፕሪንሰስ ቁልፍ ተጫዋች የሆነችው አረጋሽ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ጋር ቆይታ አድርጋለች። እንደታነቡት ጋበዝናችሁ።
ትውልድ እና ዕድገቷ በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ነው። የእግር ኳስ ሕይወትን በትምህርት ቤት ሳለች የተዋወቀችው አረጋሽ ለወረዳ እንዲሁም ለዞን በመጫወት የክለብ ዕድልን አግኝታለች።
አረጋሽ የክለብ ዕድልን አግኝታ ፕሮፌሽናል ተጫዋች የሆነችበትን አጋጣሚ እንዲህ ታስታውሳለች።
“በዞን ደረጃ አርባምንጭ ፕሮጀክት እጫወት ነበር። ሀዋሳ ላይ የሚደረግ የዞን ውድድር ነበር። በሀዋሳው ውድድር ላይ ደግሞ ለክልል ተመረጥኩኝ። ከዛን በየዓመቱ ኮካ ኮላ የሚያዘጋጀው ወድድር ነበር ፤ ይመስለኛል ካልተሳሳትኩ 2007 ይመስለኛል። ውድድሩ አዳማ ላይ ነበር የተደረገው በወድድሩ እኔም ጓደኞቼም ተሳተፈን ነበር። በዛ ውድድር ላይ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የመጡ መልማዮች ነበሩ። እና እኔንም መረጡኝ ሌሎች ጓደኞቼም ነበሩ።”
ለወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ጥሪ የተደረገላት አረጋሽ ምንም እንኳን የአካዳሚው ቆይታ አራት አመት ቢሆንም በሶስተኛው ዓመት መከላከያን (መቻልን) ተቀላቅላለች።
አረጋሽ ከሁለት አመታት የቀድሞው መከላከያ የአሁኑ መቻል ቆይታዋ በኋላ በርካታ ዋንጫዎችን ያሸነፈችበትን ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተቀላቀለች።
ስለ ንግድ ባንክ ቆይታተዋ ስታነሳ በምስጋና የጀመረችው አረጋሽ የክለቡን አመራሮች ሠ የአሰልጣኞች ስታፍ አባላትን እና የቡድን አጋሮቿ የነበሩ ተጫዋቾች ምስጋናዬ ይድረስቹ ብላለች።
“ከናንተ ጋር ባሳለፍኩት ጊዜ ሁሉ በጣም ደስተኛ ነበርኩኝ።በጣምም ደስተኛም ነኝ።በርካታ ዋንጫዎችን ያሳካሁበት ተከታታይ አራት ዓመታት የሊግ ዋንጫን ያሳካሁበት ቤት ነው። ኮከብ ጎል አግቢ የሆንኩበትም ቤት ነው።”
በ2016 የውድድር ዘመን ከንግድ ባንክ ጋር የሊጉ ሻምፒዮን ከሆነች በኋላ ለቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ማጣሪያ እየተጫወተች ሳለ ነበር ከአሁኑ ክለቧ ጥያቄዎች የቀረቡት።
በወቅቱ አረጋሽ እስከ መስከረም 30/2017 ድረስ የሚቆይ ውል ነበራት። ከያንግ አፍሪካ የመጣው ጥያቄ ውል ማፍረሻ በመክፈልም ጭምር ተጫዋቿን የግላቸው ለማድረግ ነበር።
ነገር ግን በቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ክለቧን ንግድ ባንክ ወክላ የመጫወት ህልም የነበራት አረጋሽ ዝውውሯን አዘግይታ ለንግድ ባንክ ተጫውታለች።
በዚህም ምክንያት ዝውውሯ እንዲዘገይ እና በልምምድ ብቻ ለአምስት ወራት ለመቆየት ተገዳለች።
“ያለ ጨዋታ አምስት ወር ማሳለፍ በጣም ከባድ ነው። እውነት ለመናገር ለአንድ ተጫዋች በልምምድ ብቻ አምስት ወራትን ማሳለፍ በጣም ከባድ ነው።”
“ስመጣ እንደማልጫወት አውቃለሁ። ሴካፋ እያለሁ ነው እነ አርየት በሚፈርሙበት ጊዜ ነው የዝውውር መስኮቱ የተዘጋው።የዝውውር መስኮት ድጋሚ የሚከፈተው ደግሞ ጥር ላይ ነው። እንደዛ እንደሚሆን አውቃለሁኝ። ያ የሆነበት ምክንያት አንድ ፤ እኔ ሀገር ውስጥ ሴካፋ እየተጫወትኩ ከንግድ ባንክ ጋር መስከረም 30 ነው ውሌ የሚያልቀው እስከዛ ደግሞ የሴካፋ ውድድር ነበረ።”
“የሴካፋ ውድድሩን ትቼ ለመምጣተ ስላልፈለኩ ነው። ከንግድ ባንክ ጋር ያለውን ውል ከፍለን እናቋርጥ ወይ አንቺ ምን ትያለሽ ሲሉኝ አይ አይሆንም እኔ ይሄን የሴካፋ ውድድር ረጅም ጊዜ ጠብቄዋለሁ ዓመቱን ሙሉ ደግሞ ለፍቻለሁ ዓመቱን ሙሉ ስጠብቀው ስለነበረ ግዴታ ይሄን ሴካፋ መወዳደር አለብኝ ብያቸው ነው።”
ከያንግ አፍሪካ ጋር የነበረው ንግግር በወቅቱ ቢቆምም ከሴካፋው የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር በኋላ ዳግም ቀጥሎ ዝውውሩ እውን ሆኗል።
በወቅቱ ጥያቄው ሲነሳ እጅግ ደስተኛ እንደነበረች እና ትልቁ ህልሟ የተሳካበት መሆኑንም አረጋሽ ትገልፃለች።
“ብዙ ጊዜ ይህንን ዕድል እጠብቀው ነበረ። እፈልገውም ነበረ እና ከሀገር ወጥቶ መጫወትን ከዚህ ቀደምም ብዙ ጊዜ እናገራለሁ። ወጥቼ እጫወታለሁ ህልም አለኝ ወጥቶ የመጫወት እል ነበር እና ጌታ ይመስገን ያ ተሳክቶልኝ ዛሬ እየተጫወትኩ ስለሆነ እና በጣም ደስ ብሎኛል።”
እንደማትጫወት እያወቀች ብትፈርምም ከባድ ስሜት እንደነበረው ነገር ግን በዛን ወቅት ከቡድኑ ጋርም ሆነ በግሏ ጠንካራ ዝግጅት ማድረጓን ጠቅሳለች።
“እንደማልጫወት አውቃለሁ ባውቅም ስሜቶች አሉ። እግር ኳስ ተጫዋች ስትሆን ስሜቶች አሉ አልዋሽህም።ነገር ግን በዛ ብዙም አልቆየሁም ምክንያቱም ማንም አዕምሮዬን አይጠብቅልኝም። እኔ ራሴው አዕምሮዬን ስለምጠብቅ አዕምሮዬን ለመጠበቅ በጣም ስጥር ነበረ። ልምምዶችን ሰራለሁኝ ከዛ ባሻገር በቀሪው ሰዓት እረፍት አደርጋለሁኝ። በተቻለኝ መጠን አዕምሮዬን ነፃ ለማድረግ እሞክራለሁኝ እና እነደዛ ነበር ሳሳልፍ የነበረው። እግዚአብሔር ይመስገን ብዙ አልከበደኝም። ቻሌንጆች ቢኖሩም ብዙ አልከበደኝም ትንሽ ወደ ጨዋታው ከመጣሁ በኋላ አንደ ሁለት ጨዋታ ላይ ጨዋታ ማኔጅ የማድረግ ፤ ትክክለኛዋ አረጋሽን ማምጣት ትንሽ ከብዶኝ ነበረ። ያ ነገር የተወሰነ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል ከዛ ውጪ ግን የከበደኝ ነገር የለም።”
አረጋሽ በይፋ ውሏን ፈርማ ገና በመጀመሪያ ጨዋታዋ ተፅዕኖዋን ማሳየት ችላለች። ለመጀመሪያ ጊዜ የያንጋ ፕሪንሰሰን ማልያ ለብሳ ባደረገችው ጨዋታ አንድ ግብ ስታስቆጥር አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችታ አቀብላለች።
ምናልባትም በቀጥታ ወደ ጨዋታ አለመግባቷ እና ትንሽ ከበድ ይል የነበረው የአምስት ወራት የልምምድ ብቻ ጊዜ በሌላኛው ጎን እንደጠቀማትም ተናግራልች።
በዚህን ልክ ተፅዕኖ እፈጥራለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር የምትለዋ አረጋሽ ደጋግማ የምታነሳውን ፈጣሪዋን አመስግና በቀጣይ ጨዋታዎችም ይህን ለማስቀጠል እንደምትጥር ገልፃለች።
አረጋሽ ወደ ጨዋታ መመለሻዋ ሲቀርብ በቡድኑ እጅግ አስደናቂ አቋም እያሳየች የነበረችው አርየት ኦዶንግ ጉዳት አስተናገደች።
በወቅቱ ደብሮኝ ነበር ከአረጋሽ አንደበት የተሰማ ነው። “እሷ ስትጎዳ በጣም ደብሮኝ ነበረ። ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው እና ምንም ማድረግ አይቻልም እና በቅርቡ ትመጣለች እና ባሉት ጨዋታዎች በቀሪ ጨዋታዎች ላይ አብረን እንጫወታለን የሚል ዕምነት አለኝ።”
ያንግ አፍሪካ ትልቅ ክለብ ነው በርካታ ደጋፊዎችም አሉት የምትለው አረጋሽ እዛ ከደረሰችበት ጊዜ አንስቶ ከአቀባበል ጀምሮ እስካሁንም ድረስ በጥሩ መልኩ እንደሚቀርቧቸው እና የላቀ ክብርም አላቸው ትላለች።
በታንዛኒያ ቆይታዋ ከተመለከተችው አንፃር የኢትዮጵያ እና የታንዛኒያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እና ተጫዋቾች ላይ ልዩነቱ ምን ይሆን በሚል ለቀረበላት ጥያቄም መልሷ እንዲህ የሚል ነበር።
“ብዙ ልዩነት የለንም። እነሱ ተፈጥሯቸው ላይ በጣም ይሰራሉ። በጣም ጠንካራ ናቸው እና እሱ ላይ በጣም ይሰራሉ። ያላቸው ነገር ላይ በደንብ ነው የሚሰሩት በጣም ነው የሚያሳድጉት ያን ያላቸውን ነገር።”
በቆይታዋ ከታዘበችው መካከልም በክለብ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ለቀጣይ ጨዋታዎች ዝግጅት ይደረጋል ኳሳቸውም እጅግ ፈጣን ነው ስትል ታነሳለች።
“በጣም ፈጣን ኳስ ነው የሚጫወቱት። በጣም ትግል ያለው ፣ ፈጣን የሆነ ፣ በጣም የሚገርም ፈጣን ኳስ ነው። ኳስ እኔጋር ሲመጣ ደብል ማሰብ አለብኝ። ማለት ለማ ወዴት የሚለውን ነገር ቀድሜ ማሰብ አለብኝ። ምክንያቱም በጣም ተጭነው ነው የሚጫወቱት ጥንካሬያቸውም እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። እኛ ሀገር ተቀብለን ዞረን ምናምን ነው እዚህ አይፈቅዱም ይሄንን።”
በተለይም በቅርብ ጊዜያት ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ከሀገር ወጥተው መጫወታቸው የሌሎች ሀገራት ተጫዋቾች በሚገባ በማወቅ ረገድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር እና ከዚህ ቀደም የነበረውን የሌሎች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን አግዝፎ መመልከት ነገር እንደሚቀንስ ተናግራለች።
አክላም ብዙ አቅም ያላቸው ልጆች በውጪ ሊጎች የመጫወት አቅም ያላቸው አሉ ያለች ሲሆን በተለይም በብሔራዊ ቡድን ቆይታዋ ተጫዋቾችም ወጥተው ለመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መገንዘቧን ተናግራለች።
ሉሲዎቹ የዩጋንዳ አቻቸውን ረተው ወደ ቀጣይ ዙር ስላለፉበት ጨዋታ ስታነሳም በተለይም ከካምፓላው ጨዋታ መልስ በተጫዋቾች ዘንድ ከፍተኛ ቁጭት ነበር ብላለች።
“ከጨዋታው በፊት በሁሉም ሰው ውስጥ ቁጭት ነበር። ስናወራም ልምምድ ስንሰራም በቁጭት ነበር። ከጨዋታዉ አንድ ቀን በፊት ስብሰባ አድርገን ነበር እና የሁሉም ተጫዋች ቁጭት ያስታውቅ ነበረ። እናሸንፋለን ፣ እናደርገዋለን ፣ እንቀለብሰዋለን ይሄን ውጤት የሚል ቁጭት ነበር እና ያን ይዘን ነው ወደ ሜዳ የገባነው።”
በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳይቆጠር ከተጠናቀቀ በኋላ የአጋማሽ ሰዓት የመልበሻ ክፍል ንግግራቸውን እንዲህ ገልፃዋለች።
“ሌላ 45 ደቂቃ አለን። እነሱ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ነው ያንን ያደረጉት ፤ እኛ ደግሞ 45 ደቂቃ ስላለን ይቻላል የማይቻል ነገር የለም። ሁላችንም አሰልጣኙም ፤ አምበላችንም ሌሎች ተጫዋቾችም እያወራን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው ከዕረፍት መልስ።”
ቡድኑ በራሷ በአረጋሽ ካልሳ ግብ ወደ ጨዋታው ሲመለስ የዕፀገነት ግርማ የ97ኛ ደቂቃ ግብ ደግሞ ጨዋታው ወደ መለያ ምት እንዲያመራ አድርጓል።
አረጋሽ የጨዋታውን ቀዳሚ ግብ ካስቆጠረች በኋላ ተቀይራ ወጥታ ነበር። በወቅቱ ስለተሰማት ስሜት እንዲህ ነበር የገለፀችው።
“እውነት ለመናገር ምንም አልተሰማኝም። ያ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው። ውሳኔውን አከብራለሁኝ። በሰዓቱ የነበረኝ ስሜት እኛ አሸንፈን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ብቻ ስለሆነ እኔም ልሁን ሌላ ተጫዋች ይጫወት ውጤቱን ነበር የፈለኩት ፤ እና ምንም አይነት ስሜት በሰዓቱ አልነበረኝም እውነት ለመናገር በጣም ደስተኛ ነበርኩኝ እግዚአብሔር ይመስገን።”
የፍፁም ቅጣት ምቱ ወቅት እጅግ አስጨናቂ ነበር የምትለው አረጋሽ የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሽንፈትን በማስታወስ በወቅቱ የነበራትን ስሜት እንዲህ ገልፃዋለች።
“ጌታ ሆይ ያንን ታሪክ እንዳትደግመው እያልኩ በጣም እያለቀስኩኝ ነበር። ራሴንም የሆነ ሰዓት ላይ ነው ያስተዋልኩኝ። በመጨረሻም ጌታም አሳልፎ አልሰጠንም ረዳንና አሸነፍን በጣም ደስ ብሎኛል ያም የደስታ እምባ ነበር።”
የሉሲዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ አረጋሽ የምትጫወትበት ሊግ ሀገር ከሆነው የታንዛኒያው ብሔራዊ ቡድን ጋር ነው።
“ታንዛኒያ ጥሩ ቡድን ነው። ቀላል የሚባል ቡድን አይደለም እውነት ለመናገር። ምክንያቱም አባዛኞቹ ተጫዋቾች አውቃቸዋለሁ እዚህ ሊጉ ላይ የሚጫወቱ ስለሆኑ ከውጪ ከሚመጡት ውጪ አባዛኛውን አውቃቸዋለሁ አብረን ነው ሊጉ ውስጥ የምንጫወተው እና ያ በመሆኑ ደስ ብሎኛል። እኛም ብዙ ስራ ይጠብቀናል ለቀጣዩ ፤ ያን ደግሞ አሪፍ ስራ ሰርተን ለቀጣዩ እንቀርባለን ብዬ አስባለሁኝ።”
ወደ ታንዛንያ ሊግ ስትሄድ ከደጋፊው እና ከታንዛኒያ ስፖርት ሚዲያው የነበረው አቀባበል አስደሳች መሆኑን የጠቀሰችው አረጋሽ አስቀድመው ስለእርሷም ሆነ ስለ ቡድን አጋሮቿ መረጃ ነበራቸው ትላለች።
“ያንግ አፍሪካ እንደምታውቁት ትልቅ ክለብ ነው።በጣም ብዙ ደጋፊ ያለው ነው። የታንዛኒያ ሚዲያም በብዙ በብሔራዊ ቡድንም በሴካፋ የክለብ ወድድርም ያውቁናል። እና ቶሎ ነው ያወቁን በዛ ላይ እኔ ሴካፋ ሻምፒዮን ሆኜ ነው የመጣሁት እና ገና በመጀመሪያ ጨዋታ እንደተጫወትኩ ነው ያወቁኝ። አርየትም ከዛ በፊት እየተጫወተች ስለነበረች ሁሉም ያውቃታል። በጣም ደስ ይላሉ ጥሩ ሚዲያ ነው ያላቸው። አሪፍ ነው ደጋፊዎች የሚሰጡት ነገር አሪፍ ነው። እግር ኳስን ጠንቅቀው ያውቃሉ እና በጣም አሪፍ ነው ደስ ይላሉ።”
አረጋሸ በቀጣይም በሌላ ከፍ ባለ ሊግ የመጫወት እና በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ የሚኖረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ብሔራዊ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እንደምትፈልግ ተናግራለች።
ከመሰነበባትትን በፊት ለአረጋሽ ያቀረብንላት ጥያቄ ነበር። በእግር ኳስ እጅግ የተደሰትሽበት እና እጅግ ያዘንሽበት አጋጣሚ እንዲህ ነበር የመለሰችው።
“2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆንኩበት እና በዛው አመት ከንግድ ባንክ ጋር የሴካፋ ሻምፒዮን የሆንኩበት ለኔ በጣም ልዩ ናቸው። እና ኮከብ ጎል አግቢ ሆኜ የጨረስኩበት ዓመት(2015 የውድድር ዘመን በ23 ጎሎች)ለኔ በጣም ልዩ ናቸው እና መቼም አልረሳቸውም።”
“ያዘንኩበት በክለብ ደረጃ ኡጋንዳ ላይ በሴካፋ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ(2023) የፍፃሜ ጨዋታ ከጄኬቲ ኩዊንስ ጋር ጥሎ ማለፉን በጣም ታግለን 120 ደቂቃ ተጫውተን ነበር ያለፈነው እና በቃ የመጨረሻ ጨዋታ እናሸንፋለን የሚል ሙሉ ዕምነት ነበረን። ተሸነፍን እና በጣም በጣም ነበር ያዘንኩት። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም ከሶስት አመት በፊት በዩጋንዳ ስንሸነፍ በጣም ነበር ያዘንኩት። በወቅቱ ቀጣይ ተጋጣሚ ኬንያ ራሷን ስላገለለች በቀጥታ ነበር የምናልፈው እና ሁሌ ውስጤ አለ ያ ቁጭት።”
አረጋሽ ካዘነችባቸው ጨዋታዎች መካከል በጄኬቴ ኩዊንስ ከንግድ ባንክ ጋር ሆና የደረሰባቸውን ሽንፈት ነበር። ግን ከቀናት በፊት ይህን ህመሟን የሚያስረሳ ድል አግኝታለች።
የማትረሳውን ሽንፈት እንድታስተናግድ ያደረጋትን ክለብ ጄኬቲ ኩዊንስን በሌላ ውድድር አግኝታ ዋንጫ ነጥቃቸዋለች።
በሳምያ ሱፐር ካፕ በሚል ስያሜ በሀገሪቱ አራት ታላላቅ ክለቦች መካከል በተደረገው ውድድር ለፍፃሜ ያንጋ ፕሪንሰስ ከጄኬቲ ኩዊንስ ተገናኝተው ባደረጉት ጨዋታ ያንጋ ፕሪንሰስ 3 ለ 0 አሸንፎ ዋንጫውን ከፍ ሲያደርግ አረጋሽ አንዱን ግብ በስሟ አስመዝግባለች።

“ጨዋታው እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ቆንጆ ጨዋታ ነበር። ከጄኬቲ ኩዊንስ ነበር የተገናኘው እና ጌታ ይመስገን በጨዋታው ጎል አግብቻለሁ። እና ያ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል። ከሀገር ውጪ የመጀመሪያ ዋንጫዬ ነው። እግዚአብሔር ይመስገን በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ ስሜቱ እንዲህ እንዲህ ነው ብዬ ልነገርህ አልችልም።”


