የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፌዴሬሽኑን ሠራተኞችና አመራሮችን ከኮሚሽነርነት እገደ

ለበርካታ ጊዜያት የጥቅም ግጭት ሲነሳበት ብዙምችን ሲያወዛግብ የነበረው የኮሚሽነርነት ምደባ ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አደረገ፡፡ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት የፍትህና የታማኝነት ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡ አቶ ባህሩ ለሀትሪክ ሲናገሩ “በፌዴሬሽን ደረጃ የማናጅመንት አባላትና ቋሚ ሠራተኞች የጨዋታ ኮሚሽነር ሆነው እንዳይሰሩ አግደናል፡፡ የኮሚቴዎች መሪና አመራር ሆነው ሲሰሩና ኮሚሽነር ሆነው ራሣቸው ሲመሩ የሚመጡ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ሲደመጡ ነበር፤ ይሄ ትክክል ባለመሆኑ ከ2013 ጀምሮ መስራት አይችሉም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አቶ ባህሩ ሲናገሩ “ከዚህ ቀደምም ኮሚሽነር ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸው ተገቢ አልነበረም፡፡ የጥቅም ግጭት ሊያስነሳ የሚችል ሁኔታ ነው የሚፈጥረው፡፡ አንድ ተቋም ላይ ህግ አውጥተህ ሕግ አርቀቅህ ሕግ አስፈፅመህ እንዴት ሆኖ መስራት ይቻላል? ይሄ ተገቢ ባለመሆኑ ርምጃ ወስደናል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡ “እንደ ማኔጅመንት አካል የሚመጡ ችግሮችን እንደመፍታት የጉዳዩ ተጠቃሚ የችግሩ ፈጣሪ ሆኖ መስራት ፌዴሬሽኑ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ተግባር በመሆኑ መቆሙ የግድ ሆኗል፡፡ አንድ የፌዴሬሽን ሰራተኛ የጨዋታ ኮሚሽነር ሆኖ ሲሰራና ሌላው ባለሙያ ኮሚሽነር ሲሆን በዳኞችና በክለቦች ላይ የሚከሰተው ተፅዕኖ አንድ አይሆንም የሚነሣ የጥቅም ግጭትን ለማስወገድ እግር ኳስ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ከተነሣን እንደዚህ አይነት አሰራርን ማስወገድ የግድ በመሆኑ ርምጃውን ለመውሰድ ችለናል” ሲሉ ዋና ፀሐፊው ገልፀዋል፡፡ የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ሌሎች መሰል ችግሮችን በደረጃ ደረጃ ለመፍታት ጠንካራ ስራ እየሰሩ ሲሆን በቀጣይ ተቋሙ ከአሁኑ በተሻለ ተአማኒነት እንዲኖረው ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት በነበሩ ተመሳሳይ የተበላሸ አሰራሮች ሲታማ የነበረ ሲሆነ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አመራሮች፣ የውድድር ኮሚቴ አባላት የዳኞች ኮሚቴ አባላት በተለያዩ ጊዜያት ኮሚሽነር ሆነው እየሰሩ በርካታ ውዝግቦች ሲነሱና የጨዋታ ሕጎች በንፅህና ውሣኔ ሳያገኙ በደሎች ደረሰብን የሚሉ አካላት ብዛት የትየለሌ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አመራር ሆነው የጨዋታ ኮሚሽነር በሆኑት ጨዋታ ላይ የዲሲፕሊን ጥሰት ተገኝቶ የራሳቸውን ችግር እንዴት እርሣቸው ላሉበት ኮሚቴ ይቀርባል ተብሎ በርካቶችን ሲያነጋግር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታም ነው፡፡ አቶ ባህሩ “አሁን የወሰድነው እርምጃ በፌዴሬሽኑ ቋሚ ሠራተኞች እና ኃላፊነት ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ነው በቀጣይ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ሆነው ጨዋታዎችን በኮሚሽነርነት የሚመሩት ላይ አስፈላጊ የተባለውን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፌዴሬሽን ሠራተኞችም ከአንዳንድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመነጋገር ፍትህ የሌለው ውሣኔ ሲወሰን ማየትም ሲታይ የነበረ የክለቦች ቅሬታ ነው፡፡ በ2012 በተቋረጠው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር 17ኛ ሳምንት ድረስ የጣልቃ ገብነት ቅሬታ ብዙም ባይደመጥም መርሁ መከበሩ ግን ለቀጣይ አመታት የክለቦችና የስፖርት ቤተሰቡ ጥያቄ ሁነኛ መፍትሔ እንደሚሆን ይጠበቃል፤ ከዚህ ቀደም በነበሩ አመራሮች ያልተደፈረውን ይህን ውሣኔ የአቶ ባህሩ ጥላሁን ጽ/ቤት መወሰኑ ትልቅ ትርጉም ያለው ርምጃ ተደርጎም ተወስዷል፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሀትሪክ እንዳሉት “ግለሰቦችን ለማጥቃት የተደረገ ርምጃ አይደለም፤ የምናውራው ስለሲስተም ነው፡፡ ሲስተሞች መዘርጋትና መከበር አለባቸው፤ የፌዴሬሽኑ የበላይ አመራሮች ብቻ ሣይሆኑ ሰራተኛም የሆኑ ባለሙያዎች ኮሚሽነር ሆነው መስራት አይችሉም፤ ፌዴሬሽኑ ተአማኒ መሆን ካለበት በሀገር ውስጥ የትኛውም ሊግ ኮሚሽነር መሆን አይቻልም፤ በሌሎች ሚናዎች ላይ ፌዴሬሽኑ ወክሎ ሊመደብ ይችላል በካፍ ደረጃ ያለ ኮሚሽነርነት ግን መቀጠሉ አይቀርም” በማለት ውሣኔው ከ2013 የውድድር አመት ጀምሮ የፀና መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ውሣኔ ተከትሎ ውጫዊና ውስጣዊ ጩኸቶች መከሰታቸው የማይቀር ቢሆንም ከስፖርት ቤተሰቡ የሚፈለገውን እምነት ለማግኘት በአቶ ኢሳያስ ጅራ የሚመራው ካቢኔ ለጽ/ቤቱ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport