የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በ12ኛ ሳምንት እና በአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ላይ የቀረቡትን ሪፖርቶች ተመልክቶ የቅጣት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
የሲዳማ ቡናው ብርሀኑ በቀለ ቡድኑ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ባደረገው ጨዋታ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታቱ ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ይታወቃል።
በዚህም ተጫዋቹ የአራት ጨዋታዎች እና የሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥቶለበታል።
የመቀሌ 70 እንደርታው አጥቂ ያሬድ ብርሀኑ በበኩሉ ቡድኑ በስሁል ሽረ በተረታበት መርሐግብር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጨዋታውን ዳኛ አፀያፊ ስድብ ሰለመሳደቡ ሪፖርት ቀርቦበታል።
- ማሰታውቂያ -
ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋትም ሶስት ጨዋታዎች እንዲታገድ እና ሶስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
በተጨማሪም መቀሌ 70 እንደርታ ስሁል ሽረን በገጠመበት ጨዋታ ላይ የቡድኑ አምስት ተጫዋቾች የቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ክለቡ አምስት ሺህ ብር ተቀጥቷል።
በተያያዘም የኢትዮጵያ ቡናው ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እና የመቀሌ 70 እንደርታው ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ኮሚቴው ሊያነጋግራቸው ጥሪ አድርጎላቸዋል።


