መነሻ ገጽ ቃለመጠይቅ “ወንድሞቻችን ሰርተው ያለፉትን ታሪክ እንደግመዋለን” “ፋሲል ከነማን ያሸነፍንበት ጨዋታ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል” “በደከምንም በበረታንም ሰዓት ከጎናችን ሆነው ይደግፉናል” “ለአንድ ሰዓት ያህል የከተማው መግቢያ ላይ ቆመን ስንጠብቅ ነበር” ቢንያም ገነቱ (ወላይታ ድቻ)
ቃለመጠይቅወላይታ ድቻዜናዎችየኢትዮጵያ ዋንጫ

“ወንድሞቻችን ሰርተው ያለፉትን ታሪክ እንደግመዋለን” “ፋሲል ከነማን ያሸነፍንበት ጨዋታ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል” “በደከምንም በበረታንም ሰዓት ከጎናችን ሆነው ይደግፉናል” “ለአንድ ሰዓት ያህል የከተማው መግቢያ ላይ ቆመን ስንጠብቅ ነበር” ቢንያም ገነቱ (ወላይታ ድቻ)

አጋራ
አጋራ

በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ የሻምፒዮንነት ታሪክ ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ ወላይታ ድቻ ነው።

ወላይታ ድቻ በ2009 የውድድር ዘመን በፍፃሜው ጨዋታ መቻልን በማሸነፍ ዋንጫውን ከፍ አድርጎ አንስቷል።

አምና ውድድሩ ዳግም ሲመለስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በፍፃሜው የቀረበው ክለቡ ተሸንፎ ዋንጫውን ሳያሳካ ቀርቷል።

ዘንድሮ ደግሞ ለተከታታይ አመት ለፍፃሜው ጨዋታ በመድረስ ሲዳማ ቡናን በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ስታድየም ይገጥማል።

በተከታታይ አመታት የቡድኑን ግብ በብቃት በመጠበቅ ላይ የሚገኘው ቢንያም ገነቱ የነገውን የፍፃሜ ጨዋታ አስመልከቶ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አስቀድሞ ስለ ሊግ ጉዞው ያነሳው የግብ ዘቡ ቢንያም በአመዛኙ ጥሩ ነው የሚል ሀሳብን ሰጥቷል።

“የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ እጅግ አጓጊ ሆኖ ቀጥሏል። ምክንያቱም ከባድ የሆነ የውድድር አመት ነው። ከሊጉ የሚወርደው ቡድን ቁጥር መጨመሩ ፕሪሚየር ሊጉ ውጥረት እንዲኖረው እና ሁሉም ተጠንቅቆ እንዲጫወት ያደረገ ነው። ከዛ አኳያ እኛም 75 አልያም 80 በመቶ ጥሩ ነገር ሰርተናል ብዬ አስባለሁ።”

በአምናው ውድድር ለፍፃሜ መድረሳቸው እና የገጠማቸውም ሽንፈት የፈጠረባቸው ቁጭት ዘንድሮ በድጋሚ በፍፃሜው ጨዋታ ለመገኘታቸው ምክንያት ነው ሲል ቢንያም ተናግሯል።

ጠንክረን መስራታችን እና ቡድኑ አንድ ላይ የቆየ መሆኑም ጠቅሞናል ያለው ቢንያም የአምናውን ጨዋታ እንዲህ ሲል ያነሳል።

“የአምናው የነበረው ነገር ዘንድሮ ለፍፃሜ ለመድረስ በጣም ረድቶናል። ምክንያቱም አምና እንዴት እንዳጣነው ሁላችንም ስለምናውቀው እና ስሜቱ እስካሁንም አለ።”

የአምናውን የፍፃሜ ጨዋታ ሽንፈት እንደ ትናንት የሚያስታውሰው ቢንያም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንኳን የጨዋታው ቪዲዮዎች ሲመጡ ቶሎ ነው የማሳልፋቸው አልመለከታቸውም ብሏል።

“የጨዋታው ቪዲዮዎች ሶሻል ሚዲያ ላይ ተቆራርጠው ሲመጡ ማየት አልፈልግም። ምክንያቱም ሜዳው ላይ የነበረውን ነገር ሁሉም ቤተሰብ ተመልክቶታል ብዬ ነው የማስበው። ጥሩ ነበርን ግን ፈጣሪ አልፈቀደውም። በሰዐቱ የተፈጠሩ ነገሮችም ለኛ አልተመቹንም። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ነገሮች አምልጠውናል። በእግር ኳስ ደግሞ ያለፈውን ነገር ምንም ማድረግ ስለማትችል የነገውን ማስተካከል ነው። የነገውን ደግሞ የተሻለ ነገር ሰርተን ትናንት ወንድሞቻችን ሰርተው ያለፉትን ጓደኞቻችን ሰርተው ያለፉትን እኛ ደግሞ እንደግመዋለን ብዬ አስባለሁ።”

ወላይታ ድቻ በ2009 የኢትዮጵያ ዋንጫን በማሸነፍ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ደግሞ የግብፁን ዛማሊክ ጥሎ በማለፍ ትልቅ ታሪክ መስራት ችሏል።

በክለቡ ደጋፊዎች እንዲሁም በአጠቃላይ በክለቡ ዙሪያ ባሉ ዘንድ በትልቅ ስኬት የሚነሳው የዛማሊኩ ድል ለነገው ጨዋታም እንደ መነሳሻ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ቢንያም ተናግሯል።

በወቅቱ የነበሩ ተጫዋቾችን ጭምር ስለ ጨዋታው በመጠየቅ በቡድኑ ላይ ትልቅ መነቃቃት መኖሩን ግብ ጠባቂው ገልጿል።

ከወላይታ ድቻ ውጪ ሌላ ማልያ ሳይለብስ ከታዳጊነት ጀምሮ ክለቡን እያገለገለ የሚገኘው ቢንያም ወላይታ ድቻ በ2009 የኢትዮጵያ ዋንጫን ሲያሸንፍ እሱ የነበረበትን ሁኔታ እንዲህ ነው የገለፀው።

“አዲስ አበባ ነበርን። የተስፋ ቡድን ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታ አድርገን በቀጣዩ ቀን ወደ ወላይታ ሶዶ እየተመለስን ነበር በጠዋት ተነስተን።እኛ ወደ ሶዶ ልንገባ ስንል ጨዋታው አልቋል። እና ከተማው ውስጥ የምንገባበት መንገድ ስለሌለ ወደ አንድ ሰዓት ያህል የከተማው መግቢያ ላይ ቆመን ስንጠብቅ ነበር ሰው እስኪረጋጋ ፤ በጣም የሚገርም ድባብ ስለነበር።”

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጉዞ ፈታኝ ጨዋታዎችን ማድረጋቸውን የገለፀው ግብ ጠባቂው በጣም የፈተናቸውን ጨዋታ እንዲህ አብራርቷል።

“እውነት ለመናገር ትንሽ የፈተነን ሀዋሳ ከተማ ነበር። ሁሉም ጨዋታዎች በጣም ጠንካራ ናቸው። ሸገርም ብትል ሌሎች የገጠምናቸው ቡድኖች ሁሉም ጠንካራ ናቸው ግን ትንሽ ሀዋሳ ከተማ ፈትኖናል። ውድድሩም በሰዓቱ የተደረገው እነሱ ሜዳ ላይ ስለነበር የፈተኑን እነሱ ናቸው።”

ወላይታ ድቻ ከተከታታይ አራት ድል አልባ የሊግ ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ረቡዕ ምሽት ፋሲል ከነማን 3 ለ 0 አሸንፏል።

“ምንም ጥርጥር የለውም ትልቅ የሆነ መነሳሳት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ተሸንፈህ እና አሸንፈህ ወደ ቀጣይ ጨዋታ መሄድ አንድ አይደለም እና ፋሲል ከነማን ያሸነፍንበት ጨዋታ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል።”

በ2009 ክለቡ ዋንጫውን ሲያሳካ በተስፋው ቡድን ይጫወት የነበረው ቢንያም ከስምንት አመታት በኋላ ዋንጫውን ወደ ሶዶ ለመውሰድ ሁለተኛ ዕድል አግኘቷል።

ህዝቡ እና ደጋፊው ለክለቡ ያለው ስሜት የተለየ ነው በማለት በድጋሚ ለማስደሰት በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ብሏል።

“ከተስፋ ቡድን ጀምሮ እያገለገልኩ ያለሁት ክለብ ነው። የህዝቡን ፍላጎቱ እና የህዝቡን ስሜት ለክለቡ ምን ያህል እንደሆነ ስለምረዳ ለዚህ ደግሞ ዋንጫ መስጠት ምን ያህል ደስ የሚል እንደሆነ ስለማቅ በግሌ ተዘጋጅቻሁ። እሱ ብቻ ሳይሆን ፕሪምየር ሊጉ ላይ እንኳን ምን ያህል የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በየሄድንበት ሁሉ በደከምንም በበረታንም ሰዓት ከጎናችን ሆነው ካላቸው ነገር አብልጠው መጥተው ይደግፉናል። ለዚህ ደጋፊ ደግሞ ይሄ ያንሳቸዋል እግዚአብሔር ፈቅዶ ዋንጫ አንስተን ብናሳያቸው በጣም ደስ ይለኛል።”

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት ላይ በጣቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት የተወሰኑ የሊጉ ጨዋታዎች ያመለጡት ቢንያም ያ ጉዳት ባያጋጥመው በሊጉ ላይም ከዚህ የተሻለ ነገር እንደ ግልም እንደ ክለብም ጥሩ ነገር ማሳየት እችል ነበር ነገር ግን ሁሉም ነገር በእኛ ሳይሆን በፈጣሪ ነው የሚሆነው ብሏል።

ልክ እንደ መስፍን ታፈሰ ሁሉ የውጤት ግምት ከመስጠት የተቆጠበው ቢንያም ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን ድል እንደምናደርግ አልጠራጠርም በማለት ደስ የሚል መነሳሳት አለ ሲል የቡድኑን መንፈስ ገልጿል። እጅግ በጣም የሚል ነገር ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች ስታፍም አመራሮችም ጋር አለ ሲል ተናግሯል።

ህዝቡም ጋር ያለው ነገር እጅግ በጣም ደስ የሚል ስለሆነ ከኛ የሚቀር ነገር ስሌለ እግዚአብሔር ረድቶን ደግሞ እናሸንፋለን።

በመጨረሻም ቢንያም ገነቱ ለደጋፊዎች ተከታዩን መልዕክት አስተላልፏል።

“እጅግ በጣም ብዙ ደጋፊ ነው የሚመጣው። አውቃለሁ የወላይታ ድቻ ደጋፊ ካለበት አካባቢ ባይመጣም እንኳን አዲስ አበባ ያለው የኛ ደጋፊ በርካቶች ስለሆኑ ሜዳም የሚገኙት የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች በርካቶች ስለሆኑ ለነሱ የማስተላልፈው መልዕክት እግር ኳስ ዲሲፕሊን ነው መጀመሪያ። እግር ኳስ ላይ ምንም ነገር ሊፈጠር ይችላል። ግን ያን ጨዋታ በሰላም ደግፈውን እንዲጠናቀቅ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።”

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

በ5 ሳምንታት 39 ጨዋታዎች፣ 72 ጎሎችና ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተመዘገበ!

በአቤኔዘር አበበ በ2019 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ አምስት የውድድር ሳምንታት...