➢…የሚቀጡ ዳኞች ቁጥር ወደ አምስት ከፍ ብሏል…
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻና ሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ ውጤት ለዋጭ ስህተት የሰሩት አርቢትሮች ከባህርዳር እንዲመለሱ ተወሰነ።
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ ሁለቱ ዳኞች ኢንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴና ረዳቱ አብዱ ይጥና በጨዋታው የሰጧቸው የፍጹም ቅጣት ምት ተገቢ ያልነበረ የከለከሉትም ሪጎሬ ትክክለኛ የነበረ ከተሰጡት ደግሞ የሲዳማ ቡናው በረኛ ተንቀሳቅሶ የመለሰው በመሆኑ መደገም ሲኖርበት አለመደገሙ በአጠቃላይ የጨዋታውን ውጤት የወሰኑ ግዙፍ ስህተት መስራታቸው በጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት መደረጉ ታውቋል።
የጨዋታው ኮሚሽነር ኤፍሬም መንግስቱ ለዳኞቹ ከ7 ነጥብ በታች የሰጡ መሆናቸውን የተመለከተው የዳኞች ኮሚቴ ሁለቱ አርቢትሮች እንዲመለሱ በመወሰኑ እንዲመለሱ ተደርጓል። ኮሚቴው እንዲመለሱ ያደረጋቸው አርቢትሮች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤልና ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ አሁን ደግሞ ኢንተርናሽናል አርቢትር ለማ ንጉሴና ረዳቱ ፌዴ.ረዳት ዳኛ አብዱ ይጥናን ለመቅጣት እየተዘጋጀ ቢሆንም ቅጣቱን በነበረው ህግ ሳይሆን በአዲሱ ህግ ለማስተላለፍ እየጣረ መሆኑ ታውቋል።
በኮሚቴው የዲሲፕሊን ደንብ መሠረት አንድ ዳኛ ውጤት ለዋጭ ስህተት ከሰራ ስድስት ወር ከደገመ አንድ አመት ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ ደግሞ ሁለት አመት ይታገዳል ቢልም ኮሚቴው ማሻሻያ ሳያደርግበት አምስቱን አርቢትሮች በአዲሱ ህግ ሊቀጣ ማሰቡ ታውቋል። ባልጸደቀ ህግ ውሳኔ መስጠት ባይቻልም አዲሱን ህግ ቶሎ አርቅቆና በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አጸድቆ ወደተግባር ለመግባት መወሰኑም እየተነገረ ነው። በተለይ ለዋሊያዎቹ ሲባል ውድድሩ ሲቋረጥ በሚኖረው ጊዜ አስልቶ ከ26ኛው እስከ 30ኛው ሳምንት ከዛሬ ተሰናባች ዳኞች ውጪ ሌሎቹን ለመመደብ ማሰቡ ታውቋል።
አስተያየት ይስጡ