በ24ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ የተደረገው የወልቂጤ ከተማ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ቀድሞ በተቆጠረባቸው ግብ ሲመሩ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች ከኋላ በሳሙኤል ሳሊሶ እና ዱሬሳ ሹቢሳ ግቦች 2 – 1 ማሸነፍ ችለዋል ።
ወልቂጤ ከተማዎች በ23ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ሰይድ ሀብታሙ ፤ ዮናታን ፍስሀን እና አክሊሉ ዋለልኝን በሮበርት ኦዶንግካራ ፤ ተስፋዬ ነጋሽ እና ዮናስ በርታ ምትክ ሲያሰልፉ በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ጅማ አባጅፋርን በረቱበት ጨዋታ በነበረው ምርጥ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉበት ሲሆን በተለይም በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎች በወልቂጤ ከተማም ሆነ ከሰበታ ከተማ በኩል ተፈጥረው ነበር ።
በ2ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ወልቂጤ ከተማ የግብ ክልል ደርሰው ጌቱ ሀይለማርያም ከአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ግሩም ኳስ ደርሶት የነበረ ቢሆንም ጌቱ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
በ7ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከበሀይሉ ተሻገር የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውሰጥ ሆኖ በግራ እግሩ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረትም በግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ተመልሶበታል ።

በሁለቱም በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት የነበሩ ጥረቶች በቀጠሉበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ጠንከር ያለ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ደቂቃዎች ተቆጥረዋል ።
ከውሀ እረፍት መልስ ወልቂጤ ከተማዎች በጥሩ እንቅስቃሴ መጀመር ቢችሉም የአጋማሹ የመጨረረሻ 10 ደቂቃዎች ላይ ግን ሰበታ ከተማዎች የተሻለ ሆነው ታይተዋል ።
29ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ለነበረው ለጫላ ተሺታ አቀብሎቶ ሮጦ ወደ ሳጥን በመግባት ከጫላ መልሶ የተላከለትን ኳስ ሳይደርስበት ቀረርቷል ።
በቀጣዩቹ ደቂቃዎች ላይ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች በ37 እና 39ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን መጠበቅ የቻሉ አልነበሩም ።
41ኛው ደቂቃ ላይም ሃይለሚካኤል አደፍረስ ከሳጥን ውጪ ሳይታሰብ የመታው ኳስ ሰይድ ሀብታሙ ይዞታል ።

44ኛው ደቂቃ ላይ ጌቱ ሀይለማርያም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በንስባምቢ እና ጅብሪል አህመድ ከኩል አልፎ ያገኘው አብዱለሀፊዝ ቶፊቅ የመታውን ኳስ ሰይድ ሀብታሙ እና የግቡ ቋሚ አውጥተውበታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ወልቂጤ ከተማዎችን በጥሩ እንቅስቃሴ የጀመሩት ሲሆን በተለይም ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል ።
52ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት የመታውን ኳስ ለአለም ሲይዘው ከአንድ ደቂቃ በኋላም ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
62ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን በሳጥኑ ግራ አቅጣጫ መግቢያ ላይ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በጌቱ ሀይለማርያም ተደርቦ የደረሰው ጌታነህ ከበደ በግንባር በመግጨት ከመረብ ላይ አሳርፎታል ።

ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ሰበታ ከተማዎችም መልስ መስጥት ችለዋል ። ጌቱ ሀይለማርያም ከቀኝ ያሻገረውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ አስተዋጽኦ ተጨምሮበት ኳሱ ከመረብ ላይ አርፏል ።
ከግቡ በኋላም በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረቶችን የተደረጉ ሲሆን የወልቂጤ ከተማን የኳስ ሂደት በማቋረጥ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር ።
80ኛው ደቂቃ ላይም አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ለዱሬሳ ሹቢሳ በግሩም ኳስ ሁኔታ ያቀበለውን ምርጥ ኳስ ዱሬሳ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ላይ አሳርፎታል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በሚሻገሩ ኳሶች ወደ ሰበታ ከተማ ሳጥን ኳሶችን ማድረስ ቢችሉም የሰበታ ከተማ ተከላካዮችን ማለፍ የቻሉ አልነበሩም ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች ላይ ሰበታ ከተማዎች ሶስተኛ ግብ ማከል የሚችሉበትን ዕድል ማግኘት ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
በመጨረሻም ሰበታ ከተማዎች 2 – 1 በማሸነፍ ከ16ኛ ደረጃ የተላቀቁበትን ውጤት አስመዝግበዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በ29 ነጥብ በነበረበት 11ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።

በ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 14 ( እሁድ ) ረፋድ 4:00 ላይ ሰበታ ከተማ አዳማ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ግንቦት 15 ( ሰኞ ) 7:00 ላይ ወልቂጤ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን የሚገጥም ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ