የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጥቂት ወራት በፊት ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተቋማቸው ካለበት የገንዘብ ዕጥረት አንፃር ውድድሮችን ሊሰርዝ እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።
በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተደረገ በሚገኘው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በገንዝብ ዕጥረት ከውድድሩ ራሱን አግሏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ተከታዩን ብለዋል።
- ማሰታውቂያ -
“እንደሚታወቀው የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድናችን መሳተፍ አልቻለም። ባለመሳተፋችን እኛም የምንቆጭበት ነው። ምክንያቱም የታዳጊዎች ልማት ላይ ሰራን ካልን እንደዚህ አይነት ውድድሮችን መሰረዝ ከጠቀሜታው ጉዳቱ ያመዝናል የሚል ዕምነት አለን።”
“ቀጣዩም ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን የምንፈልገው እንደዚህ ከታች ጀምሮ በሚደረጉ ውድድሮች እና የልማተ ስራዎች በሚመጣ ውጤት እንደሆነ ይታወቃል።
አቶ ባህሩ ጥላሁን አክለውም በርካታ አማራጮችን ፈልገን ነው በመጨረሻም ለመሰረዝ የተገደድነው ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።
“በነገራችን ላይ የተለያዩ አማራጮችን ፈልገን ነው የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን ወድድር የሰረዝነው ፤ ብዙ አማራጮችን ተመልክተናል። የተለያዩ አካላቶችን የመጠየቅ ዕድሉ እና ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችን እንደ ፌዴሬሽን ተመልክተን ባለቀ ሰዓት ነው ያንን ውሳኔ የወሰነው ማለት ይቻላል።”
በጣም ብዙ ሙከራዎች አድርገን ነው ይሄ ውሳኔ የተወሰነው ያሉት አቶ ባህሩ ውሳኔውን በጣም የሚያስቆጭ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
በተያያዘም በቻን ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኑ ሱዳንን ረቶ ማለፍ ከቻለ በተመሳሳይ ጉዳይ ያለመሳተፍ ነገር ሊኖር ይችል ይሆን ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄም ነገሮች የተመቻቹ ባይሆኑም እንኳን ቡድኑ ተሳታፊ እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
“ይሄን ውድድር ማለፍ በራሱ የሚያመጣቸው ተጨማሪ ጥቅሞች ይኖሩታል። በመንግሥት በኩል ከዚህ በፊት ያለው አቋም እናንተ ለዋና ውድድሮች እለፉ እንጂ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል የሚለው ነገር በፊትም ሲሰራበት የነበረ ነው።”
ከዚህ ቀደም በነበሩ የዋና ውድድሮች ተሳትፎ የመንግሥት ዕገዛ እንደነበር በማስታወስም በቀጣይ ቡድኑ ወደ ቻን ስናልፍ የመንግሥትን ድጋፍ እንጠብቃለን ሲሉ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ቡድኑን ከመደገፍ አንፃር ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ያለንባቸው ሒደቶች አሉ እነዚህ ነገሮች ወደ መልካም አጋጣሚ የሚቀየሩበት ጊዜ ይመጣሉ የሚል ዕምነት አለን ሲሉም አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልፀዋል።


