በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስማቸውን በጉልህ ማፃፍ የቻሉ ስመ ጥር ተጫዋቾችን እንካችሁ በማለት ከሚታወቁ ጥቂት የሀገራችን አካባቢዎች መካከል አርባምንጭ ከተማ እና ዙሪያዋ ይጠቀሳሉ። በ80ዎቹ መጨረሻ አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ በሚል ብቅ ብሎ ከብዙሀኑ ጋር የተዋወቀ ክለብ ቢመጣም የኋላ ኋላ የመፍረስ አደጋ ገጥሞት ደብዛው ጠፋ በመጨረሻም ዘለግ ካሉ አመታት በኋላ ግን አካባቢውን ዳግም በሚያስታውስ መልኩ አርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በሚል ተመስርቶ በ2004 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መሳተፍ ቻለ። ቡድኑ ስድስት አመታትን ብቻ በፕሪምየር ሊጉ ከቆየ በኋላ በ2010 በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ዓመቱን ጀምሮ ፣ በረከት ደሙን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት አቆይቶ ፣ የአሁኑ የንብ አሰልጣኝ እዮብ ማለ (አሞካቺን) አስከትሎ በመጨረሻም በአሁኑ የጋሞ ጨንቻ አሰልጣኝ ማቲዮስ ለማ እና የቀድሞው የክለቡ ግብ ጠባቂ ጃክሰን ፊጣ አማካኝነት በትግግዝ ከተመራ በኋላ በመጨረሻም በሊጉ መቆየት ሳይችል ለመውረድ ተገደደ።
በርካታ ተጫዋቾችን ለተለያዩ ክለቦች በማበርከት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብስራት መሆን የቻለው አርባምንጭ ከተማ በቡድኑ ውስጥ በጊዜው የነበረው ጣልቃ ገብነት ፣ አሰልጣኞች ላይ የሚደረገው ስርሰራ በአግባቡ ስራዎችን እንዳይሰሩ በማድረግ በጥቅሉ በነበሩ መጠላለፎች ክለቡ ለመውረድ ዋነኛው ምክንያቶቹ ነበሩ። በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ መሪነት ከከፍተኛ ሊጉ 2013 ላይ ማደጉን አረጋግጦ በድጋሚ በ2014ቱ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለመሳተፍ የበቃው ክለቡ በደስታ ጮቤ በሽልማቶች ተንበሽብሾ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ቢመጣም ባደገበት አመት አሁንም በቡድኑ ውስጥ የሚታዩ የመከፋፈል ስራዎች ፣ ጣልቃ ገብነቶች ፣ የክለቡ አመራሮች በማይመለከታቸው መግባት መቻላቸው ፣ እከሌን ያዝልኝ በሚል መደናቆር በቡድኑ ውስጥ በሚፈጠሩ ሌሎች ውስብስብ ችግሮች 2015 ላይ ከመሳይ ተፈሪ መሰናበት በኋላ በአሰልጣኝ በረከት ደሙ አማካኝነት አመቱን ቢያጠናቅቅም የጠቅስኳቸው ችግሮች ከሜዳ ላይ ውጤት ጋር ተደማምረው ለመውረድ ተገደደ።
በ2016 በከፍተኛ ሊጉ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ተከፋይ በመሆን በ2017 ተመልሶ በፕሪምየር ሊጉ ላይ መወዳደር ቢችልም ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ መቅረት የነበረበት ችግሮቹ አብረውት ቀጥለው ቡድኑ እየተንገዳገደም ቢሆንም አመቱን ቋጭቶ ለዚኛው የውድድር ዘመን ፈተናዎችን በጭላንጭል ማለፍ ቻለ። አሰልጣኝ በረከት ደሙ ከሐምሌ 2017 ጀምሮ በተጫዋች ዝውውር ላይ ለመሳተፍ የተጫዋቾችን ስም ዝርዝር ቢያሳውቁም የክለቡ አመራሮች ከመምህርት በአንዴ ቴክኒክ ሀላፊ መሆን በቻለ ሰው ዝውውሩ መታየት አለበት በሚል ሰበብ በአሰልጣኙ ስራ ላይ ክረምት የጀመረው ጣልቃ ገብነት በፕሪምየር ሊጉ ላይ እየተባበሰ ቀጥሎ ቡድኑ እንዲከፋፈል በሚያደርጉ ሀሳቦች ፣ የመስራት ነፃነቶች አለመኖራቸው ፣ ሁሉም የስራ ድርሻውን ለይቶ አለማወቁ እና ሌሎችም በርካታ ውስብሶች አመታትን ተሻግረው ዛሬም ተጉዘው መቀረፍ ሳይችሉ አሰልጣኝ በረከትን በማሰናበት በቀድሞው ተጫዋቹ አበባው ቡጣቆ ቢመራም በዚህኛው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቡድኑ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች በ8 ተሸንፎ በ8 አቻ ወጥቶ 17 ጎል ተቆጥሮበት 5 ብቻ አግብቶ በ12 የግብ ዕዳ በ8 ነጥብ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ ተቀምጦ ይገኛሉ።
አራት ክለቦች በሚወርዱበት በዚህ አመት 19ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ወልዋሎ በ5 ነጥብ ርቆ የሚገኘው ክለቡ በሜዳ በመከላከልም ይሁን በማጥቃት ያለበት ቴክኒካዊ ስህተቶች አርሞ በይበልጥ በማሸነፍ ዕሳቤ ውስጥ ሆኖ አሸናፊየት በመላበስ ማስተካከል ካልቻለ ሽንፈትን ልምምዱ እያደረገ መጓዙን ከቀጠለ ቡድኑ ውስጥ ያሉ ጣልቃ ገብነቶች ህግን የተከተሉ መሆን ካልቻሉ ገደል አፋፍ ላይ ቆሞ የሚገኘው ክለቡ አፋፉን አልፎ ቁልቁል ተንደርድሮ መግባቱ የሚቀር አይመስልም።


