“የትናንቱ ድል ወደ ጅማ ተጉዘን ለምናደርጋቸው ቀጣይ ጨዋታዎቻችን ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው የሚሆነን “አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ /ባህር ዳር ከተማ/

 

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን በአህመድ ረሺድ ብቸኛ የድል ግብ 1-0 ካሸነፈ እና የነጥብ ልዩነቱንም ከእሱ በላይ ካሉት ቡድኖች ጋር ካጠበበ በኋላ በመልበሻ ክፍላቸው ውስጥ “አሲናበል አሲናገናዬ እዮሀ አሲናበል እዮሀ አሲናገናዬ” የሚለውን የገና በዓል ዝማሬ ዘምረው ደምቀው ወጥተዋል።

ባህር ዳር ከተማ በዛሬው ጨዋታ በእኩል 7 ነጥብ ላይ ይገኘው የነበረውን ተጋጣሚውን ድሬዳዋን ካሸነፈ በኋላ እና ነጥቡንም ወደ 10 ካሳደገ በኋላ ወሳኟን የድል ግብ ካስቆጠረው የቡድኑ ተጨዋች አህመድ ረሺድ ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጠር ያለን ቆይታ ያደረገ ሲሆን ቃለ ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

ሀትሪክ፦ ድሬዳዋ ከተማን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸንፋችኋል። ጨዋታው ምን መልክ ነበረው? ውጤቱስ ይገባችኋል?

አህመድ፦ የዛሬው ጨዋታ ለእኛ ጥሩ ነበር። ግጥሚያውን ለማሸነፍም ቆርጠን ተነስተን ስለነበር የሁለተኛው አጋማሽ ላይ አሰልጣኛችን ፋሲል ተካልኝ ያለንን ታክቲክ ስለተገበርን ግጥሚያውን እኔ ባስቆጠርኩት ብቸኛ ግብ ልናሸንፍ ችለናል።

ሀትሪክ፦ የድሉን ግብ በማስቆጠርህ ምን አይነት ስሜት ተፈጠረብህ?

አህመድ፦ በጣም ነው ደስ ያለኝ። የተደሰትኩትም ግቧን እኔ ስላስቆጠርኳት ብቻ ሳይሆን ቡድናችንን ባለ ድል ያደረገች እና ወደ መሪዎቹ በነጥብ ያቃረበችንም ስለሆነ ነው።

ሀትሪክ፦ ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን ለማሸነፍ የቻለበት ጠንካራ ጎኑ ምን ነበር?

አህመድ፦ የቡድናችን ህብረቱ ይለያል። በአንድ ላይ እንንቀሳቀሳለን፤ በአንድ ላይም እናጠቃለን። ህብረታችን ጠንካራ ጎናችን ነው።

ሀትሪክ፦ ድሬዳዋ ከተማን በዛሬው ጨዋታ እንዴት አገኘካቸው?

አህመድ፦ ጠንካራ ቡድን ነው። ውጤቱንም እንደ እኛ ሁሉ ይፈልጉት ነበር። ያም ሆኖ ግን ከእነሱ በተሻለ ጥሩ ተንቀሳቅሰን ስለነበር ልናሸንፋቸው ችለናል።

ሀትሪክ፦ ሁለታችሁ ዛሬ የተገናኛችሁት እኩል ነጥብ ይዛችሁ ነበር። የጨዋታው አሸናፊ ሆናችሁ በመውጣታችሁ በደረጃው ሰንጠረዥ ወደ ላይ ከፍ አላችሁ። በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ……?

አህመድ፦ እኛና ድሬዎች እኩል ነጥብን ይዘን በተገናኘንበት የዛሬው ጨዋታ ሁለታችንም የድል ውጤቱን ብንፈልገውም በመጨረሻ አሸናፊ የሆንነው እኛ ነን። ይሄ ጨዋታ ለእኛ የመጨረሻው የአዲስ አበባ ግጥሚያችን ስለሆነም ቀጣይ ለምናመራበት የጅማ ከተማ ጨዋታዎቻችንም ትልቅ ስንቅም ነው የሚሆነን።

 

ሀትሪክ፦ ባህር ዳር በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የት ድረስ ለመጓዝ ተዘጋጅቷል?

አህመድ፦ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፋችን አሁን ላይ ከመሪዎቹ ጋር ያለን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 ጠቧል። የቡድናችን የእዚህ ዓመት ዓላማም ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው ለሊጉ ሻምፒዮናነት መጫወት ሲሆን ሌላው ደግሞ ያን ካላሳካን የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ወስደን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ መሳተፍ ነው።

ሀትሪክ ባህር ዳር ከተማ ስለያዘው የተጨዋቾች ስብስብ እና ስለ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ምን የምትለው ነገር አለ?

አህመድ፦ የተጨዋቾቻችንን ስብስብ በተመለከተ ጥሩ እና ካለፈው ዓመት አኳያም ምንም እንኳን ዓምና እኔ የዚህ ቡድን ተጨዋች ያልነበርኩ ቢሆንም የተሻለ ነው ብዬ ነው የማስበው።
ከጅማሬው ቡድናችንን ስመለከተውም ጥሩ ቡድን እየተሰራ ነው ብዬም አስባለሁ። ሌላው ስለ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መናገር የምፈልገው ወጣት እና ጥሩ አሰልጣኝ ነው። ስናጠፋ እኛ ላይ ከመጮህ ይልቅ እንደ አባት እና ወንድም ሆኖ የሚመክረን ነው። ይሄ ጉዞአችንም በውጤት ደረጃ በጥሩ መልኩም እያስጓዘን ነው።

ሀትሪክ፦ ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረጋችሁትን የደርቢ ጨዋታ ለማሸነፍ ተቃርባችሁ እና ሁለት ተጨዋችም በቀይ ካርድ ወጥቶባችሁ በአቻ ውጤት አጠናቃችኋል። ያ ግጥሚያ አሁን ላይ አስቆጫችሁ?

አህመድ፦ በጣም ከሚገባው በላይም ነው ያስቆጨን። የጨዋታው አሸናፊ ለመሆን ተቃርበንም ነው ባለቀ ሰዓት ላይ በተቆጠረብን ግብ በጎዶሎ ልጅ በመጫወታችንና የድካም ስሜት ስለነበረብን እንደዚሁም ደግሞ የትኩረት ማነስ ስለነበረብንም ነው ግጥሚያውን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅም ዋጋ ልንከፍል የቻልነው።

ሀትሪክ፦ በመጨረሻ….?

አህመድ፦ ባህር ዳር ከተማ በዛሬው ዕለት የተቀዳጀው ድል ጣፋጭ ነው። በየቦታው ተተካክተው መጫወት የሚችሉ የጥሩ ተጨዋቾች ስብስብንም የያዘ ቡድን ስላለን ይሄ ስኬታችን የሚቀጥል ነው። ይህን ካልኩ በኋላ ደግሞ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እና ጓደኞቼ መልካም የገና በዓል እንዲሆንላቸው እመኛለሁ።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor