በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች በቅደመ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠቀሙትን የቡድን ስብስብ ማስመዝገቢያ ቀነ ገደብ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል ።
የውድድሮቹ የበላይ አካል የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን(CAF) በቅድመ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ላይ ክለቦች የሚጠቀሟቸውን ተጫዋቾች እንዲያስመዘግቡ ከሰኔ 24 ጀምሮ ክፍት አድርጎ ቆይታል ።
ለአንድ ወር የቆየው የተጫዋቾች ማስመዝገቢያ ጊዜም ዛሬ ለሊት 6:00 ላይ ያበቃል ።
ክለቦችም በደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ የሚጠቀሟቸውን እና ዝውውር ፈፅመው ዝውውራቸው በየፌዴሬሽናቸው የፀደቁ ተጫዋቾችን እስከተጠቀሰው ሰዓት ድረስ የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው ።
- ማሰታውቂያ -
በዛሬው ዕለት ልምምዳቸውን የሚጀምሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማም ከዛሬ ዝውውሮቻቸው መጠናቀቅ በኋላ አጠቃላይ ስብስባቸውን እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል ።
እስከዛሬው ዕለት ድረስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባረጋገጣቸው ዝውውሮች መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ የአስር ተጫዋቾቹን ውል ሲያራዝም አማኑኤል አረቦን ከለገጣፎ ለገዳዲ እንዲሁም ፋሲል ገብረሚካኤልን ከባህርዳር ከተማ አስፈርሟል ።
ባህርዳር ከተማ በበኩሉ ፍሬው ሰለሞንን ከሲዳማ ቡና ፣ አላዛር ማርቆስ ከሀዋሳ ከተማ ፣ ረጂብ ሚፍታህ ከቤንች ማጂ እንዲሁሕ ፍሬዘር ካሳን ከሀድያ ሆሳዕና ማስፈረሙ ይታወሳል ።