በሀያ ስምንተኛዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር የመዝጊያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ገና በጊዜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች በጀመረዉ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች መጠነኛ ፉክክር ያስመለከቱን ሲሆን ፈረሰኞቹም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መጨዋታቸዉን ከቀጠሉ በኋላ በ21ኛዉ ደቂቃ ላይ የባንክ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት የተገኘዉን ኳስ ዳግማዊ አርአያ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ክልሉ ሲቀንሰዉ ተከላካዩ ኤፍሬም በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹ መሪ መሆን ችለዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ክለቦች በኩል ጎሎችን ለማስቆጠር የጋለ የሜዳ ላይ ፉክክርን እየተመለከተን የቀጠልን ሲሆን በዚህም ባንኮች አየቻነት ግብ ፍለጋ በተደጋጋሚ የፈረሰኞቹን የግብ ክልል ሲያንኳኩ የቆዩበት ሂደት ፍሬ አፍርቶ በ41ኛዉ ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። በዚህም ከማዕዘን የተሻማዉን ኳስ ሳይመን ፒተር ሲገጨዉ በቅርብ ርቀት የነበረዉ ባሲሩ ዑመር ኳሷን ጨርፎ ወደ ግብነት በመቀየር በአጋማሹ መገባደጃ ወቅት አቻ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች በተሻለ የማጥቃት መነሳሳት በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ለመድረስ ያደርጉ የነበረዉ ጥረት ጥሩ የሚባል የነበረ ቢሆንም ነገር ግን አፈፃፀም ላይ ሁለቱም ክለቦች ደካማ ሁነዉ ተስተዉለዋል። ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ግን በመጠኑም ቢሆን እየተቀዛቀዘ በቀጠለዉ ጨዋታ በ76ተኛዉ ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ በረመዳን የሱፍ አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ከጨዋታ ዉጭ በሚል ተሽሮባቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሳይመን ፒተርን በቀይ ካርድ ያጡት እና ቀሪ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ባንኮች ምንም እንኳን በቀሪ ደቂቃዎች እጅጉኑ ጫና ፈጥረዉ መጫወት ቢችሉም ነገር ግን በጨዋታዉ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር መርሐግብሩ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ፍፃሜዉን አግኝቷል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ወላይታ ዲቻ ጨዋታቸዉን ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ፈፅመዋል።
አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ ወላይታ ዲቻዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ብልጫ ወስደዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ዕድሎችን በመፍጠር እና የፈጠሯቸዉን ዕድሎች ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ ግድ ደካማ ሁነዉ ተስተዉሏል። በተቃራኒው በይበልጥ ወደ መከላከሉ አመዝነዉ በመጫወት እንቅስቃሴያቸውን የቀጠሉት ሀምበሪቾዎች ደግሞ አልፎ አልፎ በሚያገኟቸዉ የመልሶ ማጥቃት እና የቆሙ ኳስ አደጋዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ያን ያህል የጠራ የግብ ሙከራ ሳያስመለክተን ፍፃሜዉን ሲያገኝ ከዕረፍት መልስ በተሻለ ለማጥቃት በሚል ቢኒያም ፍቅሬን ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት ዲቻዎች በተደጋጋሚ የሀምበሪቾን የግብ ክልል በመፈትሹም ነገር ግን በሀምበሪቾዉ የግብ ዘብ ምንታምር መለሰ ጥሩ ብቃት ኳሶቹ ግብ ከመሆን ከሽፈዋል። ከዕረፍት መልስም እንደ መጀመሪያዉ አጋማሽ ሁለለ በጥብቅ መከላከል መጫወት የቀጠሉት ሀምበሪቾዎች በ52ተኛዉ ደቂቃ ላይ በተመስገን አማካኝነት ከርቀት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱ አምክኖባቸዋል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ዲቻዎች የተሻለ ብልጫን ወስደዉ በቢኒያም ፍቅሬ እና ናታን ጋሻዉ በመሳሰሉ ተጫዋቾቻቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ጨዋታዉ ያለ ግብ 0ለ0 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።