“ያለፉትን እናውሳ ያለነው በቅዱስ ጊዮርጊሳዊ ሀሳብ እንበርታ” የሚል መሪህ ቃል አንግበው ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ወደ ሀዋሳ ከተማ በእግራቸው የተጓዙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ መዳረሻቸው በመቃረብ ላይ ይገኛሉ።
የሀሳቡ አመንጪ ከነበሩት እና የጉዞው አካል ከሆኑት መካከል የሆነችው ፀጋ ልቡ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ጋር ባደረገችው አጠር ያለ ቆይታ የጉዟቸው ዓላማ በዋነኝነት ከ11 ዓመታት በፊት ህይወታቸው ያለፉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ለማሰብ ነው ትላለች።
“መነሻ ሀሳቡ ከዛሬ 11 አመት በፊት የሚወዱትን እና ውዱ ክለባቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ካለ ደጋፊ ሜዳ አይገባም ብለው ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሀዋሳ የሔዱ ሶስት ወንድሞቻችን(መሐሪ እስጢፋኖስ ፣ ሲሳይ ኃይሉ እና ዘላለም አንዱአለም)ነበሩ። በህይወት ከቤተሰቦቻቸው ወተው በህይወት ግን ወደ አዲስ አበባ መመለስ አልቻሉም።”
መሐሪ ፣ ሲሳይ እና ዘላለም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ላይ ከሀዋሳ ከተማ ላለበት ከመርሐግብር ማሟያነት ያልዘለለ ትርጉም ላልነበረው ጨዋታ ክለባቸውን ለመደገፍ ሰኔ 29/2005 ወደ ሀዋሳ በማቅናት ላይ ሳሉ የመኪና አደጋው አስተናግደው ህይወታቸው ያለፉ ሶስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ናቸው። የዚህ ጉዞ ዋና አላማም እነሱን ለማሰብ መሆኑ ተመላክቷል።
- ማሰታውቂያ -
ክለባቸውን ለመደገፍ ተጉዘው ህይወታቸውን ያጡትን ሶስቱን ደጋፊዎች ባለፉት አመታት ላይ በተለያዩ መንገዶች የማሰብ የማስታወስ ስራዎች ተሰርተዋል።
ካለፉት አመታት የማሰቢያ መንገዶች በተለየ የዘንድሮውን ለሸገር ደርቢ ወደ ሀዋሳ የእግር ጉዞ በማድረግ የመጓዝ ሀሳብ የመጣው እነሱም በህይወት ቢኖሩ ከዚህ ጨዋታ እንደማይቀሩ በማሰብ ነው ሰትል ተናግራለች።
“እነሱ በህይወት ቢኖሩ ይህንን የሸገር ደርቢ ለማየት ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ ይሄዱ ነበር። ይሄንንም ጨዋታ የምናስበው በእግር ብንሔድ አንደኛ ያልተደረገ ነገር ነው ፤ በማንም በእግር ጉዝ ታስቦ አያውቅም። በአጠቃላይ ዋናው አላማው እነሱን ለማሰብ ለማመስገን ነው። በጊዮርጊስ ቤት የሰራ ሁሌም ይመሰገናል ይከበራል። ያንን የሚገልፅ መዝሙርም አለን።”
“በዚህም እነሱን ማሰብ በነሱ ውስጥም ደሞ እንቁ ብርቅ የሆኑ ደጋፊዎቻችንን ለማወደስ ነው።”
ሀሳቡ ሲነሳ 30 የክለቡን ደጋፊዎች መዝግበን ነበር ያለችው ፀጋ በተለያዩ ምክንያቶች ስድስት ደጋፊዎች ጉዞውን ጀምረው ለመጨረስ መቃረባቸውን ትናገራለች።
“መጀመሪያ ስንመዘገብ 30 ሰው ነበር። ይሄዳሉም ብለን ያሰብነው 30 ሰው ነበር ቁጥሩን ገድበነው ነበር። በፋይናንስ ፤ በስራ እና ለተማሪዎች የፈተና ወቅት በመሆኑ የተጓዦቹን ቁጥር ቀንሶታል” ስትል ገልፃለች።
እነዚህ ተጓዥ ደጋፊዎች ሶስቱ ደጋፊዎች ህይወታቸው ያለፈበት ቦታ ላይም የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት አካሂደዋል።
በጉዞ ላይ በየደረሱባቸው እና በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ስለገጠማቸው ሁኔታ በመገረም የምታነሳው ፀጋ አዕመሯችን ላይ ብቻ ተስላ የቀረችውን ኢትዮጵያ ያየሁባት ነው ብላለች።
“በጉዞ ላይ አዕምሮአችን ላይ ብቻ ተስላ ያለችውን ኢትዮጵያ ያየሁበት ነው። ይህ የኔ የግሌ ሀሳብ ብቻ አይደለም። ማታ ላይ ከጉዞ መልስ ተሰባስበን እናወራለን ። መፅሐፍትም ይዘናል ዝክረ ጊዮርጊስም ስለሆነ የምናነሳውም ሀሳብ ከጊዮርጊስ ስለማይለይ ስንነጋገር ይበልጥ የሚወስድብን ነገር ምንድነው ቀን ላይ ያሳለፍናቸው ነገሮች ናቸው።”
“እኛ ጉዞውን ስናቅድም የጉዞ ሰዓት ብለን ያስቀመጥነው አለ ፤ ከጠዋት 1 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ስለዚህም ለምሳ የምንቆምበት አጋጣሚም አይኖርም። ወይም የምናርፍበትን ለማዘጋጀት ካልሆነ በስተቀር ጉዞ አናቆምም ነበር።”
“እናም የምናያቸውን እናቶች ጨምሮ የድሮዋ ኢትዮጵያ ትላልቅ ሰዎች ጋር ብቻ ቀርታለች የሚለውን ነገር የሚያፋርሱ ወጣቶችንም አግኝተናል። የነገሮት ትኩሳት ያልያዛቸው በርካታ ወጣቶችን ነው ያየነው።”
ሰምተን ስጋት ሆነውብን የወጣንባቸው ነገሮች ነበሩ የምትለው ፀጋ መንገድ ከመጠቆም አንስቶ አብረዋቸው የተወሰኑ መንገዶችን በመከተል የሚሸኟቸው እንደነበሩ ታወሳለች።
ለማደሪያ እንኳን ቤታቸውን የሚለቁላቸው ሰዎችንም በጉዟቸው ወቅት ማግኝተቻውን ተናግራለች።
“ማህበራዊ ሚድያ ላይ የምትንሸራሸረው ነገሮች የጎደሉባትን ኢትዮጵያ ሳይሆን ትክክለኛነትን ፤ ሀቀኝነትን ፤ ማህበራዊነትን የምትተገብረውን ኢትዮጵያን እኛ በመንገዳችን ላይ አግኝተናታል።”
ረጅም ጉዞው ብዙም አለመልመደቻው ፤ የመንገዱ ሁኔታ እና ከአየር ሁኔታው ውጪ ይህ ነው ተብሎ ሊነሳ የሚችል የከበዳቸው አልያም የገጠማቸው ፈተና አለመኖሩን በፀጋ የተወከሉት እነዚህ ደጋፊዎች ተናግረዋል።
በቀጣይም ከዚህ በተለየ መልኩ መሰል ፕሮግራም ሊደረግ እንደሚችችልም ተጓዣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ፍንጭ ሰጥታለች ። “ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድ ቅዱስ ጊዮርጊስነቱ ባህር ነው። ጥቂት ሀሳብን ብቻ የምታነሳለት ክለብ አይደለም። ገና ከምስረታው ጀምሮ በርካታ እክሎች የነበሩበት በርካቶች ለአንድ ህይወታቸው ሳይሰስቱ ፤ ከመቁሰል እስከ መድማት እስከ መታረዝ እስከ መጠማት የደረሱ እልፍ ደጋፊዎች አሉት። ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድ ቅዱስ ጊዮርጊስነቱ እልፍ ታሪክ ያለው ነው እና ባህርን በማንኪያ ነው የሚሆንብን እነዚህን ሶስት ልጆት ብቻ አንስተን እንዘክር ብንል።”
ይህ ጅማሮ ነው ቀጣይ በተለየ ፣ ባማረ እና ለጊዮርጊስ ክብር በሚመጥን መልኩ ተዘጋጅተን እንመጣለን የፀጋ ቃል ነው።
እነዚህ ተጓዥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሀዋሳ ለመግባት ጥቂት ኪሎ ሜትሮት ብቻ የቀሯቸው ሲሆን ከገቡ በኋላም ከክለቡ ተጫዋቾች ጋር የመገናኘት ፕሮግራም ይዘዋል። በምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈው መታሰቢያነቱን ለሶስቱ ደጋፊዎች እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
በመጨረሻም በጉዟቸው ከጅምሩ ድጋፍ ላደጉላቸው በጉዟቸው ወቅትም ከጎናቸው ለነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በላይ ደጀን ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፤ ኦሜጋ የትጥቅ አምራች ቢጂአይን እና በየከተማው ትብብር ላደረገላቸው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።