በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ዲቻ መርሐግብራቸዉን ያለ ግብ በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች በአብዝሀኛዉ ወደ መስመር ባደላ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አደጋዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ ነገር ግን የሚያገኟቸዉን ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የነበራቸዉ ስልነት ያን ያህል ሆኖ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት ጅማሮዉን ባደረገዉ ጨዋታ አፄዎቹ በተደጋጋሚ የሚያገኟቸዉን ዕድሎች በመጠቀሙ ረገድ ደካማ ሆነዉ የተመለከትን ሲሆን አጋማሹ ሊጠናቀቅ አምስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ የግቡን አግዳሚ ጨርፋ ወጥታለች። ከዚች የአፄዎቹ ተጠቃሽ የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራ በኋላ ናታን ጋሻዉ በዲቻዎች በኩል በ44ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ነገር ግን ግብ ሳይቆጠር ጨዋታዉ አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።
በሁለተኛዉ አጋማሽ በተሻለ የፉክክር መንፈስ በተመለሰዉ ጨዋታዉ በተለይ ወላይታ ዲቻዎቼ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋለ ሲሆን በ54ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ናታን ጋሻዉ ያቀበለዉን ኳስ ብዙአየሁ ሰይፉ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በሚኬል ሳማኪ ቅልጥፍና ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች። ከዚች ቅፅበት ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ናታን ጋሻዉ ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ሳማኪም በድጋሚ ሙከራዋን አምክኗታል።
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተቀዛቀዘ በቀጠለዉ የዕለቱ ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ አፄዎቹ የተሻለ ተንቀሳቅሰዉ በፍቃዱ አለሙ እና ዳግም አወቀ አማካኝነት ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ነገር ግን ሳይሳካላቸዉ ጨዋታዉ ያለ ግብ 0ለ0 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
48ተኛዉ የሸገር ደርቢ ጨዋታ አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል ተደርጎ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል ።
በኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር ተደጋጋሚ ብልጫ በጀመረዉ የደርቢ ጨዋታ ቡናማዎቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ወደ መስፍን ታፈሰ ባመዘነዉ ሜዳ ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን ሲሆን በሙከራም ረገድ የተሻሉ ሁነዉ በመሀመድኑር ናስር እና መስፍን ታፈሰ አማካኝነት በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተጠቃሽ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተቃራኒው ብልጫ ተወስዶባቸዉ የነበሩት ፈረሰኞቹ በመልሶ ማጥቃት በሚገኙ ኳሶች አደጋዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ የተነሳ አደጋ መፍጠር ተስኗቸዉ ተስተውሏል።
በ16ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ቡናማዎቹ የነበራቸዉን ብልጫ ተጠቅመዉ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከግራ መስመር በኩል ከመስፍን ታፈሰ የተቀበለዉን ኳስ መሀመድኑር ናስር በግሩም ዕርጋታ ኳሷን ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በአብዝሀኛዉ የጨዋታዉ መለኪያ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አልፎ አልፎ ወደ ቡናማዎቹ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ይልቁንስ ተከላካዩ ብሩክ በሰራዉ ስህተት ምክንያት ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበዉ የነበረ ቢሆንም በፍሪፕሞንግ ግሩም ጥንካሬ ገና በጊዜ ሁለት ለዜሮ ከመመራት ተርፈዋል።
የመጀመሪያዉ አጋማሽ ተጠናቆ በ47ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ብልጫ ተወስዶባቸዉ የነበሩት አንድም ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከማዕዘን ምት ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከወደ ቀኝ መስመር በኩል በረከት ወልዴ ያሻገረዉን ኳስ ፍሪፕሞንግ በጭንቅላቱ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡ ከአጋማሹ ሳይጠናቀቅ አቻ እንዲሆን አስችሏል።
ከዕረፍት መልስ በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ጨዋታዉ በመግባት ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ሲሆን በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸዉን ፍፁም ብልጫ ማስቀጠል ተስኗቸዉ ተስተውሏል።
በ49ነኛዉ ደቂቃ ላይ ግን አብዱልከሪም ወርቁ ከአማኑኤል የተቀበለዉን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ባህሩ ኳሷን እንደምንም አምክኗታል። ከዚች ሙከራ በኋላ አጥቂዉን አማኑኤል ኤረቦ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት እና ጫና ፈጥረዉ ለመጫወት የሞከሩት ፈረሰኞቹ ግን ያን ያህል ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ እንደተቸገረዉ የጨዋታዉን ደቂቃ የገፉ ሲሆን ቡናማዎቹም በቀሪ ደቂቃዎች ላይ ምንም እንኳን ጫና ፈጥረዉ ቢጫወቱም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ መርሐግብሩ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ፍፃሜዉን አግኝቷል።