ገና በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነው፤ዕድሜው ትንሽ ቢሆንም ህልሙ ግን ትልቅ ነው።ሀገራችንን በተለያዩ የውድድር መድረኮች በመወከል ስማን ለማስጠራት ያለው ጉጉት በቃላት የሚገለፅ አይደለም።የትግራይ ምድር ያበቀለው የነገው የአትሌቲክሱ ዓለም አልጋ ወራሽ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ከወዲሁ የሚተነብዩለት አትሌት ልዑል ገ/ስላሴ።
“የሩጫውን አለም የተቀላቀልኩት ውጤታማው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በፈጠረብኝ ተፅእኖ ነው፤በአጭሩ ወደ ሩጫው ዓለም አስገድዶ ያስገባኝ ለቀነኒሳ ያለኝ አድናቆትና ፍቅር ነው”በማለት የሚናገረው አትሌት ልዑል ከሀትሪክ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር የካናዳ ዋና ከተማ የሆነችው ኦታዋ ላይ ተገናኝተው ነገ ሰለሚጀመረውና እሱ ሰለሚሳተፍበት የኦታዋ ማራቶን የ10ኪ.ሜ ውድድርና ስለሚጠብቀው ውጤት፣ወደ ሩጫው እንዴት እንደገባ፣ሰለ ቀጣይ ዕቅድና በሌሎች ወቃታዊ ጉዳዮች ላይ የብቻ ለብቻ ቆይታ አድርገዋል።
እነሆ ቃለ-ምልልሱ :-
ከትትራክ ወደ አስፍልት ስለመግባቱ…
“ቀደም ሲል የምታወቀው በ10.000 እና በ5000 ሜትር ነበር፤ ዘንድሮ ግን ወደ አስፓልት የጎዳና ላይ ውድድር ገብቻለሁ ።እንደሚታወቀው የለንደኑ የአለም ሻምፒዮና ከፊታችን አለ ሚኒማ ለማማላት ይረዳኛል ብዬ ገብቼበታለሁ”
- ማሰታውቂያ -
ቀደም ሲል ያስመዘገበውና በትልቅነቱ ስለሚያነሳው ውጤት…
“በትልቅነቱ የማነሳው የብራዚሉን ነው፣ውድድሩ በጣም ፈታኝ ቢሆንም 1ኛ በውጣት አሸንፌያለሁ።ከእሱ ውጪ ናይጄሪያም በቅርቡ ሄጄ ትልቅ ፈተና ገጥምኝ እሱንም በድል ተወጥቻለሁ፤ናይጄሪያ ላይ ከፍተኛ ሙቀት ነበር እስከ አሁን የፈተነኝ ውድድር እሱ ነበር እሱንም በድል ተወጥቻለሁ።”
ኦታዋ ማራቶንን እንዴት ልትመረጥ ቻልክ..
“ውድድሮችን የሚመርጡት ማኔጀሮቻችን ናቸው ።እንዳልኩህ ለአለም ዋንጫ ሚኒማ ለማማላት ነው የመጣሁት፤ኦታዋ ማራቶን ላይ በመወዳደር ምን ደረጃ ላይ እንዳለሁ ለማወቅና ለመፈተሸ ያለኝን ጉድለት ለለመሙላት ነው የመጣሁት”
ውጤት ማስመዝገብንስ አታስብም ማለት ነው …
“ምንም ጥያቄ የለውም፤ከላይ ከጠቀስኩልህ በተጨማሪ ወደ ኦታዋ የመጣሁት ለማሸነፍ ጭምር ነው፤ለማሽነፍ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ”
ስለማሸነፍህ እርግጠኛ መሆን አይከብድም ምክንያቱም ከአንተ ጋር አብረው የሚሮጡት አትሌቶች በጣም ጠንካሮች ናቸው በተለይ ኬንያዊው ኒኮላስ እና ጃፓናዊው ኬንታዊ ከዚህ አንፃር እንዴት ታየዋለህ…
“ሁለቱም የየራሳቸው ጠንካራ ጎን ቢኖራቸውም ከእነሱ ይልቅ ፕሬስ ኮንፈረንሱ ላይ የሌሉት የሀገሬ ልጆች በጣም ጠንካራ ናቸው።ጃፓናዊው ፊኒሺንግ ላይ ከደረሰ በጣም ጎበዝ ነው ወደ ፊኒሺንጉ እንዳይደርስ አድርገን ለማሸነፉ እንጥራለን”
የልጅነት ሮል ሞዴልህ ማነው ?እሱን ብሆን ብለህ ተመኝተህ ያደከው,..
“ቀነኒሳ በቀለ ብቻ ነው፤በ2001ዓ.ም 10ኛ ክፍል እያለሁ ስለ ቀነኒሳ በቀለ ብዙ ይወራ ነበር በወቅቱ ወደ ፊት ምን መሆን ትፈልጋለህ?ስባል እንደ ቀነኒሳ በቀለ ታዋቂ ራጭ መሆን እያልኩ ነበር ያደኩት። ቀነኒሳን እያየሁ ነዉ ያደኩት።በአጭሩ ወደ ሩጫዉ በፍቅሩ አስገድዶ ያስገባኝ እሱ ነው።አሁን እንደ እሱ ውጤታማ ባልሆንም ወደፊት ግን እንደ እሱ ውጤታማ ለመሆን እጥራለሁ።”
ቀጣይ ዕቅድህ?…
“ከእግዚአብሔር ፋቃድ ጋር የለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ላይ ሀገሬን ወክዪ በመገኘት ታሪክ መስራት፤ከዚህ በፊት ግን ሚኒማ ለማማላት እስትራቫ ላይ እሮጣለሁ”
በመጨረሻ… ጃፓን ነበርክ. ..ለምን እዛ ድረስ ሄድክ…
“ጃፓን የሄድኩት ለሩጫ በኮንትሪት ስምምነት ነው፤እዛ አንድ ዓመት ከ3 ወር ተቀምጬያለሁ፤አሁን ምቹ ሁኔታ በማግኘቴ ተመልሼ እየሰራሁ ነው።በዚህ አጋጣሚ ወደ ጃፓን እንድሄድ የረዳኝ አቶ ዱቤ ጁሎ ነው ምንም ረዳት በሌለኝ ጊዜ ዕድሉን ፈጥሮልኛልና በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለሁ.”