የጨዋታ ዘገባ | ዋልያዎቹ ቀድመው መምራት ቢችሉም አራት ግብ አስተናግደው ተሸንፈዋል

የአፍሪካ ዋንጫው የምድብ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲጀመሩ አስተናጋጇን ሀገር ካሜሩንን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችልም በሁለተኛው አጋማሽ ያንን መድገም ተስኖት 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኬፕቨርዴን ከገጠመው ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ቅያሪዎችን ያደረገ ሲሆን በቀይ ካርድ ምክንያት በዛሬው ጨዋታ መሰለፍ ባልቻለው ያሬድ ባየህ ቦታ ምኞት ደበበን እንዲሁም ከፊት መስመር ላይ ባልተጠበቀ መልኩ ጌታነህ ከበደን በዳዋ ሆቴሳ ተተክተዋል በካሜሩን ብሄራዊ ቡድን በኩል ቾፖ ሞቴንግ ፤ ማርቲን ሀንግላ እና ጂን ቻርለስ በቡርኪናፋሶ ጨዋታ በቋሚ አሰላለፍ ያልነበሩ በዛሬው ጨዋታ ግን በቋሚ 11 ውስጥ መካተት የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው ።

ዋልያዎቹ በጨዋታው ግብ ለማስተናገድ 4 ያህል ደቂቃዎችንጰብቻ ነበር የጠበቁት ። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል መሬት ለመሬት የላከውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ አግኝቶ ቀዳሚውን ግብ አስቆጥሯል ። መልስ ለመስጠት በፈጣን እንቅስቃሴ የተጫወቱት የማይበገሩት አናብስት ከዳዋ ግብ 4 ደቂቃዎች በኋላ አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ማግኘት ችለዋል ።

አምበሉ ቪንሰንት አቡበከር ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ተክለማርያም ሻንቆ ሲመልሰው በቀኝ መስር ላይ የነበረው ንጎራን ፋይ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ካርል ቶኮ ኢካምቢ በግንባር በመግጨት ከመረብ አሳርፎታል ።

በኬፕቨርዴው ጨዋታ ባሳየው አቋም በብዙ የተተቸው የዋልያዉ ስብስብ በዚህ ጨዋታ ግን በተለይም እስከመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ድረስ ድንቅ ሊባል የሚችል የሜዳ ላይ እንቅሰቃሴን ማሳነት ችሎ ነበር ። ከካሜሩን ተጫዋቾች የሚነጠቁ ኳሶችንም በፍጥነት ወደ ፊት በመውሰድ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን በመፍጠር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠርም ጥረቶችን አድርገው ነበር ።

በአቡበከር ናስር እና በሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ የተደረጉት ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ሲመለሱ በአማኑኤል ግብረሚካኤል አማካኝነት በፈጣን አጨዋወት ወደ ፊት የሄዱ ኳሶች በካሜሩን ተካላካዮች በቀላሉ ተይዘዋል ። ካሜሩኖች በተለይም የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥነረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 39ኛ ደቂቃ ላይ ቶኮ ኢካምቢ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጪ ለግብ የቀረበ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር ።የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ ።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በዋልያዎቹ በኩል ላይ የቢጫ ካርድ ተመልክቶ በነበረው ሱራፌል ዳኛቸው ወጥቶ ፍሬው ሰለሞን ገብቷል ። አጋማሹ ካሜሩኖች ያቀዱትን ያሳኩበት ነበር ማለት ይቻላል ። በተለይም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የግራ መስመር በኩል በተደጋጋሚ ወደ ግብ የሚደርሱ ኳሶች አደጋ የፈጠሩ ነበሩ ። 48ኛ ደቂቃ ላይ ንጎራን ፋይ ለቪንሰንት አቡበከር ያደረሰውን ኳስ ተክለማርያም ሻንቆ ወጥቶ መልሶበታል ።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መቀጠል የቻለው እስከ 53ኛ ደቂቃ ድረስ ነበር ። በተከታታይ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች 1 ለ 1 የነበረው ጨዋታ ወደ 3 ለ 1 ተቀየረ ። ቀደም ብለን በጠቀስነው መስመር ላይ ንጎራን ፋይ ያሻገረውን ኳስ አምበሉ ቪንሰንት አቡበከር በግንባር መትቶ የካሜሩንን ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ 55ኛ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ቪንሰንት አቡበከር ሙሚ ንጋሜሉ ያቀበለወሰን ኳስ ተንሸራቶ በማስቆጠር ለራሱ ሁለተኛ ለሀገሩ ደግሞ ሶስተኛውን ግብ አስቆጠረ ።

ከግቦቹ በኋላ የማይበገሩት አናብስት በፈጣን ማጥቃት የቀጠሉ ሲሆን የዋልያዎቹ ተጫዋቾች ይህን መቋቋም ተስኗቸው ነበር ። በተጨማሪም በተለይም ከቆሙ ኳሶች እና በረጅም በሚላኩ ኳሶች ላይ የካሜሩን ተጫዋቾች እንደፈለጉ ኳሶችን ማግቸትም የቻሉበት ነበር ። 67ኛ ደቂቃ ላይ በመሀል የሜዳው ክፍል ላይ ካሜሩኖች የነጠቁትን ኳስ በፍጥነት ወደ ግብ በመውሰድ የመጀመሪያውን ግብ ባስቆጠረላቸው ቶኮ ኢካምቢ አማካኝነት አራተኛ ግብ አስቆጠሩ ።

ከግቡ በኋላ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኩል ሶስት ቅያሪዎች የተደረጉ ሲሆን መሱድ መሀመድ ፤ ረመዳን የሱፍ እና ዳዋ ሆቴሳ ወጥተው በዛብህ መለዮ ፤ አህመድ ረሺድ እና ሽመክት ጉግሳ ገብተዋል ። ከቅያሪዎቹ በኋላ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ቢችሉም የማጥቃት ሶስተኛውን ዞን ላይ ሲገቡ ገሰን ኳሶችን በቀላሉ ይነጠቁ ነበር ።

86ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ ከተካላካዮች የነጠቀውን ኳስ አቀብሎ በዛብህ መለዮ ቢያገኘውም ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ። ጨዋታውም በካሜሩን 4 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ በመጪው ሰኞ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ከያውንዴ 250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ባፎሳም ከተማ በኩዌኮንግ ስታድየም ላይ የሚያደርግ ይሆናል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *