*…ምክንያት የተደረገው ደግሞ ኮንትራክተሩ ሃላፊነቱን አልወስድም በማለቱ ነው ተብሏል….
የአዲሰ አበባ ስታዲየም ከ40 ወራት ክልከላ በኋላ የዋሊያዎቹና የሌሴቶ ጨዋታን የሚያስተናግደው ያለተመልካች መሆኑ ከታማኝ ምንጭ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።
ከ2013 በኋላ ምንም አይንት የእግርኳስ ጨዋታ ያልተስተናገደበት የአዲስ አበባ ስታዲየም በፊፋ ካላንደር መሰረት እውቅና ተሰጥቶት ሲሆን ኢትዮጵያና ሌሴቶ ነገ እና እሁድ የሚያደርጉትን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በጂቡቲያዊያን ዳኞች እየተመራ ሲካሄድ የጨዋታ ድምቀት ለሆነው ተመልካቹ ዝግ መሆኑ ታውቋል።
የግንባታውን ሃላፊነት የያዘው ተቋም “ስራውን ጨርሼ አላስረከብኩም ተመልካቹ ቢገባና ንብረቶቹ ላይ ምንም ጉዳት ቢደርስ ሃላፊነቱን አልወስድም” በማለት ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በማሳወቁ ጨዋታዎቹ በዝግ ያለተመልካች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሚዲያ አካላት ብቻ ገብተው እንዲመለከቱ መወሰኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።