የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መጋቢት 09 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አምስቱ በመሸናነፍ ቀሪ ሶስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 23 ጎሎች በ17 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 42 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ ሶስት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።
በሳምንቱ በሶስት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። እንየው ካሳሁን(ሀዋሳ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ 1 ጨዋታ እንዲታገድ ፤ አንተነህ ጉግሳ(ወላይታ ድቻ) የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ የማግባት ዕድል በማበላሸት በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 እንዲከፍል ፤ አብዲሳ ጀማል(ኢትዮጵያ መድን ) ሆን ብሎ የተጋጣሚ ቡድንን ተጫዋች በክርን በመማታት በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በሶስት ክለቦች ላይም ተመሳሳይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ከወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ብስራት በቀለ ፣ አዛሪያስ አቤል ፣ አንተነህ ጉግሳ እና ቢኒያም ገነቱ ፤ ከሲዳማ ቡና ጊት ጋትኩት፣ ሔኖክ ፍቅሬ ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ፣ መክብብ ደገፉ እና ይገዙ ቦጋለ ፤ ከመቻል በኃይሉ ግርማ ፣ስቴፈን ባዱ አኖርኬ ፣ ግሩም ሃጎስ ፣ አልዌንዚ ናፊያን እና ነስረዲን ሀይሉ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሶስቱ ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡