ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቅጥር በኋላ ወደ ዝዉዉር ፊታቸዉን በማዞር የተለያዩ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ተጨማሪ የሶስት ተጫዋቾችን ዝዉዉር አገባደዋል።
የዉድድር አመቱን በወልቂጤ ከተማ ተጫዉቶ ማሳለፍ የቻለዉ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰዉ ከክለቡ ወልቂጤ ከተማ ጋር ከተለያየ በኋላ በዛሬዉ ዕለት ወደ አዳማ ከተማ በሁለት አመት የስምምነት ዉል ማምራቱ ዕርግጥ ሆኖአል።
ሌላኛዉ የክለቡ ፈራሚ ደግሞ ረዘም ላሉ አመታት ከተጫወተበት ሲዳማ ቡና ጋር በትላንትናው ዕለት በስምምነት የተለያየዉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዮሴፍ ዮሀንስ ሲሆን ተጫዋቹ ከሲዳማ ቡና ጋር በተለያየበት ማግስት ወደ አዳማ ከተማ በማምራት በዛሬው ዕለት ፊርማውን አኑሯል።
ሶስተኛዉ ፈራሚ ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ቤት ረዘም ላሉ አመታት በወጥ ብቃት መጫወት የቻለዉ የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሀንስ መሆኑ ታዉቋል። በተጨማሪም በትላንትናው ዕለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ዉበቱ አባቱ አማካኝነት ጥሪ ከደረሳቸው 28 ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።


