“የጅማ አባጅፋሩ ስራ አስኪያጅ ክስ ተከሰንም ሆነ ከሰን ምንም አልሆንም፤ ፌዴሬሽንኮ ሰው አለን ሲሉኝ ደነገጥኩ” አሸናፊ ቢራ /ጅማ አባጅፋር/

ጅማ አባጅፋር ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ምንም አይነት ግልጋሎት እንዳያገኝ ተወስኗል፡፡

በየካቲት 10/2013 በዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ፊርማ የወጣው ደብዳቤ እንደሚለው “የታህሳስ 2013 የኤፍሬም ጌታቸው ሙሉ ክፍያ ለመፈፀም፣ የጥር ወር 2013 የሁሉም ተጨዋቾች የሁለት ወር ክፍያ እንዲሁም የካቲት 2013 የሁሉም ተጨዋቾች የሁለት ወር ክፍያ ለመክፈል ተስማምታችሁ እግዱ መነሳቱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ባላችሁት መሠረት ክፍያውን ባለመፈፀማችሁ ደብዳቤው ከተፃፈበት ቀን ጀምሮ ክለባችሁ ፌዴሬሽኑ ከሚሰጣቸው ማንኛውም አገልግሎቶች የታገዳችሁ መሆኑን እናሳውቃለን” ሲል እገዳው መፅናቱን አስታውቋል፡፡

በርካታ ተጨዋቾች ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ በጅማ አባጅፋር ላይ ቅሬታ ቢያቀርቡም ክለቡ እየታገደ ከቆይታ በኋላ እገዳው ዳግም እየተነሣ በፌዴሬሽኑ የፍትህ አካሄድ ሚዛናዊነትና አካልነትና እኩልነት ላይ ጥያቄ እንዲነሣ አድርጓል፡፡ በክለቡ ጉዳት ደርሶብኛል በማለት ቅሬታ እያቀረቡ ካሉ ተጨዋቾች መሃል የአሸናፊ ቢራ ቅሬታ ትኩረት የሳበ ሆኗል፡፡ ተጨዋቹ የ2013 ውል ቢኖረውም ደመወዝ የተከፈለው የመስከረምና የጥቅምት ወር ብቻ ሲሆን የህዳር፣ የታህሳስ የጥር ወር ደመወዝ ለሌሎቹ ሲገባ የእርሱ መከልከሉን ለሀትሪክ አስረድቷል፡፡

አሸናፊ ሲናገር “የ3 ወር ደመወዜን ስጡኝ ስላቸው መጀመሪያ ከግማሽ አመቱ በኋላ ያለውን ውል ለማቋረጥ ተስማምቻለሁ የሚል ደብዳቤ አስቀድመህ አስገባና ነው ቀሪውን ደመወዝ የምንሰጥህ ሲሉኝ ስለቀጣዩ እናወራለን ችግር የለውም የ3 ወር ደሞዜን ግን ስጡኝ አልኳቸው እነሱ እንቢ ብለው መልሰውኛል” ሲል ይናገራል፡፡ “በኔ ቦታ ሰው ማምጣት ፈልገዋል ገብቼ ከተጫወትኩ ለምን ተቀመጠ ተብለው እንዳይጠቆሩ ስጋት ውስጥ ገብተዋል አዲሱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በርታ እያለኝ አበረታቶኛል ሊያሸማግለን ሲሞክር አንተ እንድትከፋ አልፈልግም እኔ ግን ተበድያለሁ ደመወዜን ስጡኝ ስላቸው እንቢ ብለውኛል እኔ ፌዴሬሽን ሄጄ እከሳለሁ ስለው ስሜትህ ይገባኛል ችግር የለም ብሎኛል እነርሱ ሲጀመር የሚሄዱና የሚቀሩ ተጨዋቾች ብለው ሊስት ሰጥተውታል ያንን መንካት አልፈለገም” ሲል ያለውን ሁኔታ አስረድቷል፡፡

“ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከመጫወታችን በፊት ተሰላፊ ዝርዝር ተነግሮን ቁርስ ከበላን በኋላ ወደ ስታዲየም ልንሄድ ስንል አሰልጣኙ የሱፍ መጣና ማልያውን አትልበስ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው ምን ላድርግ አለኝ ተገረምኩ አሰልጣኙ አንተ አይደለህ ስለው ምን ላድርግ ታዝዣለሁ ብሎ መለሰልኝ አሰልጣኙ መብት የለውም” ያለው አሸናፊ “አሰልጣኝ ጳውሉስ ጌታቸው እያለ ለምንድነው የማያሰልፍህ አንተኮ ትችላለህ ችግሩ የእርሱ ነው ይለኝ ነበር፤ አሰልጣኙ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ከቡድኑ ጋር ከተለየ በኋላም አንተ አላሰለፍከኝም ለምን የጳውሎስን ስም ታነሣለህ ስለው አይ አንድ ወር ሙሉ ልምምድ አልሰራህም አለኝ ትምላለህ እኔ አልሰራሁም? ብዬ ስጠይቀው አልምልም ብሎኝ ሄደ ይህን ያህል ይዋሻል” ሲል በዚያዊነት ቡድኑን እያሰለጠነ ስላለው አሰልጣኝ ተናግሯል፡፡

አሸናፊ በጣም የገረመውን ጉዳይ ለሀትሪክ ሲናገር “ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ሱልጣን ዛኪር ጋር ሄጄ ስናገር ባልንህ ተስማማ ፌዴሬሽን ሰው አለን ከሰንም ተከሰንም አይተነው እንደፈለግን እየሆንን ነው ቡድኑ አበል እየከፈለኝ ነው የምንቀሳቀሰው አንተ ግን ያለህን ብር ትጨርሳለህ አርፈህ የተባልከውን አድርገህ ብትወስድ ይሻላል ሲለኝ ሚዲያውና ፌዴሬሽን የሰረቃችሁኝን ውል አስመልሰውልኛል በቀጣይ የሚሆነውን እናያለን በህጉ መሠረት እከሳለው አልኩት” በማለት ተናግሯል፡፡

“አሸናፊን አሳምነው ብለውት ይመስላል የበረኛ አሰልጣኙ መጣና አናገረኝ ምንም አትልፋ መጀመሪያ የለፋሁበት ደመወዜ ይከፈለኝና በቀሪው ውል ላይ መነጋገር እንችላለን ስለው ይሄ ቡድን በብዙዎች ተከሶም ሆነ ከሶ አሁንም ቀጥሏል ምንም አልሆነም ያሉህን አድርገህ ብርህን ብትወስድ ይሻላል አለኝ አልሰማማም ፌዴሬሽን ሄጄ እከሳለሁ ሕጉ ይዳኘናል ብዬው ሄድኩ” ሲል በክለቡ አመራሮች ላይ ያለውን ችግር ለሀትሪክ አብራርቷል፡፡

በዚህ ቅሬታ ዙሪያ የክለቡ ምላሽ ምንድነው በማለት ወደ ክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ዛኪር የግል ስልክ ላይ የደውልን ሲሆን ከብዙ ሙከራ በኋላ ስልካቸውን አንስተው ኃይለ ቃል በመጠቀም ለጥያቄያችን ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም፡፡ የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ማንኛውም ውሣኔና የውስጥ ጉዳይ የመግለፅ ኃላፊነቱ የእሳቸው ቢሆንም ኃላፊነታቸውን በሚገባ ሳይወጡ ቀርተዋል፡፡ አሁንም ሥራ አስኪያጁ ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ የመስጠት ግዴታቸውን እንዲወጡ እየጠየቅን ክለቡ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ እርግጠኞች ነን፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *