የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሻምፒዮንነት ጉዞ ትንቅንቁ ቀጥሏል
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታድየም ተደርገዋል።
ከረፋድ 04:00 ጀምሮ በተደረገው በቀዳሚው የዕለቱ ጨዋታ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቻልን ገጥሞ በ90ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረበት ግብ ነጥብ ለመጣል ተገዷል።
66ኛው ደቂቃ ላይ ንግስት በቀለ ያስቆጠረችው ግብ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን ቡድን እስከ 89ኛው ደቂቃ ድረስ መሪ አድርጎ ነበር።
ነገር ግን 90ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ ያስቆጠረችው ግብ ለመቻል ጣፋጭ አንድ ነጥብ ሲያስገኝ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወሳኝ 2 ነጥቦች ያሳጣች ሆናለች።
ከ09:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ የመሪውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥብ መጣሎ ተመልክቶ የገባው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ህዳት ካሱ ሁለቱንም የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግቦች በ53ኛው እና በ57ኛው ደቂቃዎች ላይ አስቆጥራለች።
የዕለቱ ውጤቶችንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተመሳሳይ 54 ነጥብ ላይ ሲገኙ በንፁህ ግቦች ተለያይተው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በቀጣይ የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባህርዳር ከተማ ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ፤ ከድሬዳዋ ከተማ ፤ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ከሀዋሳ ከተማ ይጫወታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ከአርባምንጭ ከተማ ፤ ከይርጋጨፌ ቡና ፤ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከአዳማ ከተማ ይጫወታል።
በተያያዘም የሊጉ መርሐግብር በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይርጋጨፋ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ ፤ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከባህርዳር ከተማ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ።
አስተያየት ይስጡ