ዋልያዎቹ ድሬዳዋ ላይ ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔን በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ መርሀግብር ሲገጥሙ የሚመሩ ዳኞችን ሀትሪክ ስፖርት አረጋግጣለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ወደ ማጣሪያ ድልድሉ ለመግባት በቅድመ ማጣሪያው ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔን የሚገጥሙ ሲሆን የመጀመሪያ ማጣሪያቸውንም ለማድረግ ጨዋታው ወደ ሚደረግበት ሞሮኮ አልጀዲዳ ከተማ ከረጅም ጉዞ በኋላ ዋልያዎቹ አምርተው ከደቂቃዎች በፊት አመሻሹን የመጀመሪያ ልምምዳቸውን መስራታቸውን አውቀናል።
ከነገ በስቲያ ዕርብ መጋቢት 18/2018 በሞሮኮው አልጀዲዳ ስታዲየም የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ሲደረግ አራት ሴኔጋላዊያን ዳኞች እንደሚዳኙት በቀዳሚነት ከሳምንት በፊት የነገርኳችሁ ሲሆን በድሬዳዋ ስታዲየም መጋቢት 22/2018 የመልሱ ጨዋታ ሲከናወን አራት ግብፃዊያን ዳኞች እንዲመሩት በካፍ መመረጣቸውን ሀትሪክ ስፖርት ባገኘችሁ ዝርዝር መረጃ አረጋግጣለች።
የ39 አመቱ መሐመድ ማሩፍ ኢድ መንሱር በመሐል ዳኝነት ሲመሩ የሀገሩ ልጆች ሰሚር ጀማል ሳድ እና አህመድ ቶፊክ ተሊብ ረዳቶቹ እንዲሁም ደግሞ መሐመድ አህመድ መሐመድ ባሲኦኒ አራተኛ ዳኛ ሆኖ በጋራ ሲመሩት ደቡብ ሱዳናዊው ሰቢት ሊብራቶ በጊ ራሳ የጨዋታ ታዛቢ ኮሚሽነር እንዲሁም ደግሞ ኮንጓዊው ሞሙዚጋ ጃግስ በአሰሰርነት በጋራ ሆነው የሚመሩ ይሆናል።
በሞሮኮ የሚደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ሴኔጋላዊያኑ ኤልሀጂ አማዱ ሲ በመሐል ዳኝነት በረዳት ዳኝነት ደግሞ ማማዱ ናጎም እና መሐመድ ፎል አራተኛ ዳኛ አዳልበርት ዲዮፍ የጨዋታ ታዛቢ ማጋሳ ሲዴ ቤካዬ ከማሊ መሆናቸውን ከሳምንታት በፊት በዘገባችን ነግረናችሁ ነበር።
አስተያየት ይስጡ