የቅዱስ ጊዮርጊስን ችግር ለመቅረፍ ያለመ በቀድሞው ተጫዋቾች የተሰየመ ማህበር በዛሬው ዕለት በይፋ ተመሠረተ።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ስሙን ከፍ አድርጎ መቀመጥ የቻለው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስሙን በማይመጥን መልኩ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለፋይናንስ ችግር እየተዳረገ መጥቶ አሁን ላይ ለከፋ ችግር ውስጥ መብቃቲ ይታወሳል። ይህንን ክለብ ወደነበረው ዝና ለመመለስ በርካቶች ርብርብ ከማድረግ ባለፈ ለክለቡ መፃዬ ዕድል ሲባል በቅርቡ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ቀደም ሲል የተቋቋመውን ኮሚቴ ይደግፋል ፣ ያግዛል አልያም የመፍትሔ ሀሳቦችን ያመጣል ተብሎ በቀድሞው ተጫዋቾች የተቋቋመ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ በይፋ ተቋቁሟል።
በአካል ከተገኙ የክለቡ የቀድሞው ተጫዋቾች በተጨማሪ ከሀገር ውጪ የሚገኙ የቀደሙ ተጫዋቾችም በኦንላይን ይህንን መግለጫ መከታተል የቻሉ ሲሆን ይህ ኮሚቴም ለመስራት ያሰባቸውን ስራዎች ከዘረዘረ በኋላ በመጨረሻም ዘጠኝ ጊዜያዊ አባላት ተመርጠዋል። ገብረመድህን ሀይሌ ፣ ሰለሞን መገርሳ ፣ ስዩም ከበደ ፣ ፍቅሩ ተፈራ ፣ ፋሲል ተካልኝ ፣ ፍፁም ገ/ማርያም ፣ ታረቀኝ ቢሻው ፣ ፉአድ አብዱልቃድል እና አዳነ ግርማ ሲሆኑ ኮሚቴው በዋናነት ለወቅታዊ የክለቡ የፋይናንስ መፍትሄ ማፈላለግ ፣ ክለቡን ማዳን እና ለመጪው ትውልድ መሰረት ሆኖ እንዲቆም ድጋፍ ማድረግ መሆኑ ተመላክቷል።

አስተያየት ይስጡ