……ታሪክ ነቃሹ ፍልሚያ…
ቅዱስ ጊዮርጊስ vs ከአርባምንጭ ከተማ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ አሸናፊን ይጠቁማል ከተባሉት ጨዋታዎች አንዱ ነው የተባለለት የቅዱስ ጊዮርጊስና የአርባምንጭ ከተማ ፍልሚያ ነገ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ፈረሰኞቹ በ59 ነጥብና 34 ግብ ሊጉን እየመሩ ቀሪ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ሲሆን አርባምንጭ ከተማም በ40 ነጥብና 3 ግብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሆነው የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑ ታውቋል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ 1ለ1 መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን የነገው ጨዋታ ከፍተኛ ፍልሚያ የሚደረግበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
አርባምንጭ ከተማ በ1995 ዋንጫ ያጣበት መንገድ እግር ኳሳዊ አይደለም በሚሉ በስፖርት ቤተሰቦች የሚነገር ሲሆን በ1995 በነበረው ውድድር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ ከነበሩት አንድም የቡድን አባል የለም። በአርባምንጭ ግን አሰልጣኙ መሳይ ተፈሪ፣ ምክትል አሰልጣኝ አበባው ታምሩና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ስለሺ ሽፈራው በዚያኛው ቡድን የነበሩ መሆናቸው ይታወሳል።
ከጨዋታው በፊት አሰልጣኝ መሳይ ሲናገር ” እውነት ነው ዘመን ያስቆጠሩ ቅሬታዎች አሁንም አሉ ይሄን መካድ አልችልም ነገር ግን በነገው ጨዋታ በቀል ብሎ ነገር የለም በቀል የእግዚአብሄር ነው በ40 ነጥብ ከያዝነው 7ኛ ደረጃችንን ወደ አራተኛነት ከፍ ስለሚያደርገን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማሸነፍ ወደሜዳ እንገባለን” ሲል የተለየ ዓላማ ይዘው እንደማይገቡ ተናግሯል።
በነገው ወሳኝ መርሃ ግብር ከቀኑ 7 ሰዓት ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና 10 ሰዓት ላይ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ የሚጫወቱ ሲሆን የጨዋታ አርቢትሮች ምደባ ላይ ኮሚቴው ጥንቃቄ እንደሚወስድ ይጠበቃል።
አስተያየት ይስጡ