የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ለሁለት ቀናት በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዶ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል። በዕለቱ በጉባኤው የተነሱትን አጠቃላይ ሁነቶች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
በትላትናው ዕለት ጅማሮዉን ያደረገዉ 13ኛዉ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጠቅላላ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ዉሎ በዛሬዉ ዕለት ተካሂዶ የተለያዩ ዉሳኔዎች ተላልፈዉበት ተጠናቋል።
በጋሞ አባቶች ምርቃት በተጀመረዉ ጉባኤም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸዉም ፌዴሬሽኑ ያከናወናቸውን አጠቃላይ ስራዎች ፣ ስኬቶች ፣ ተግዳሮቶች እና የመሳሰሉትን ሀሳቦች አንስተዉ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በመቀጠልም በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰብስቤ ቡናቤም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

ከክብር ዕንግዳዉ መልዕክት በመቀጠል የ2013 የዕድቅ አፈፃፀም ሪፖርትን የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በዝርዝር አቅርበዋል። ከተነሱት ሀሳቦች መካከል:-
የታዳጊዎችን እና ወጣቶች ልማትን በተመለከተ ፣ የኢንስትራክተሮችን ፣ አሰልጣኞ ፣ ዳኞች እና የህክምና ባለሙያዎችን በተመለከተ ፣ የአሰልጣኞች ስልጠናን በተመለከተ ፣ የሀገር ዉስጥ ዉድድሮችን በተመለከተ ፣ የስፖርት ማዘዉተሪያ ቦታዎችን እና ማሰልጠኛዎችን ለዉድድር ምቹ ማድረግን በተመለከተ ፣ የሴካፋ ከ23 አመት በታች ዉድድርን በተመለከተ ፣ የፌዴሬሽኑ የስፖንሰር አቅም በተመለከተ ፣ የሰዉ ሀብትን በተመለከተ የተከናወኑ ስራዎች ፣ ብሔራዊ ቡድኖችን በተመለከተ የተከናወኑ ተግባራትን ፣ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በተመለከተ ተነስተዋል።
ከሪፖርቱ በመቀጠልም የግዥ እና ፋይናይስ ዳይሬክተሩ የሂሳብ መግለጫ በሶስት ክፍሎች ተከፍሎ የተሰጠ ሲሆን በመግለጫውም በገቢ ደረጃ ፌዴሬሽኑ ከፊፋ 67 ሚሊዮን ገደማ ከካፍ ደግሞ 10 ሚሊዮን ገደማ እንዲሁም ከመንግሥት 21 ሚሊዮን ገደማ የተገኘ ሲሆን በበጀት አመቱም አጠቃላይ 124 ሚሊዮን የሚጠጋ ገቢ እንደነበረዉ ገልፀዋል።

በወጪ ደረጃም ለከፍተኛ ሊግ ፣ ለአንደኛ ሊግ ፣ ለአስተዳደር ፣ ለክልሎች እና ለሴቶች አጠቃላይ 121 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ወጪ መደረጉን የገለፁ ሲሆን በበጀት አመቱም ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በትርፍነት መመዝጉ ተገልጿል። ከ2012 አመት ሲነፃፀርም በ3ሚሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱ ተጠቁሟል።
ከዚህ በመቀጠል በስፍራው የተገኙት ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እና ሀሳባቸዉን ለፊዴሬሽኑ አመራሮች አቅርበዋል።
ከጥያቄዎቻቸው መካከልም :-
የአደረጃጀቶች ችግር መኖራቸዉን፣ በዕቅድ መመራት ላይ ችግር ስለመኖሩ ፣ የዉድድር ስፍራዎች ወስን መሆናቸውን ፣ በፓይለት ፕሮጀክት ዉስጥ የማቴሪያል ዕጥረት መኖራቸውን ፣ የሴቶች እግርኳስ ላይ በቂ ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑን እንዲሁም የዉድድር ቦታዎች እና የጨዋታ ሰዓቶች ለሴቶች አመቺ አለመሆናቸውን እና ተያያዥነት ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከዚህ ባሻገርም ፌዴሬሽኑ የሰራቸዉን ስራዎች እንዲሁም የሚበረታቱ ስራዎችን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
ከነዚህ መካከልም:-
ፌዴሬሽኑ ይሄንን ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ከባድ ወቅት በዚህ ባማረ መልኩ በማዘጋጀቱ ሊመሰገን ይገባዋል ያሉ ሲሆን በተጨማሪም የፓይለት ፕሮጀክት መጀመሩ እና ወደስራ መገባቱም አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አጠቃላይ የቀረበው ሪፖርት አመርቂ እንደሆነ እና በዚሁ እንዲቀጥል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የተሳታፊዎችን ጥያቄ ተከትሎም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ምላሽ እንዲሁም ጠቅለል ያለ ማጠቃለያ ሰጥተዋል።
ካነሷቸዉ ነጥቦች መካከልም:-
ስታዲየሞችን
በተመለከተ መሰረተ ልማቶች የሚሰሩት በፌዴሬሽኑ አይለይም እነዚህን የመስራት አቅም የለንም ፤ ከካፍ ጋር ባለኝ መልካም ግንኙነት ጨዋታዎችን በሀገር ዉስጥ ስናደርግ ቆየን እንጅ ካፍ ከሀገር ወጥተን እንድንጫወት ካዘዘ ቆይቷል። ከባህርዳር ስታዲየም ጋር ተያይዞ የተቀጣዉ የባህርዳር ስታዲየም ሳይሆን ኢትዮጵያ ነች የተቀጣችሁ ይሄንን በተመለከተ ይነሳ የነበረው ሀሳብ የተሳሳተ ነበር። ስታዲየሞችን በተመለከተ ከምክትል ጠ/ሚንስትር ጋር ተነጋግረናል። በቅርቡ ችግሮቹ ይቀረፋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው መገባደጃ ወቅትም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳት ያቀረባቸዉን አባላት ጉባያተኞቹ በሙሉ ድምፅ ያፀደቁ ሲሆን በዚህም የቀድሞው የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዝዳንት ኮለኔል አወል በአሁኑ ሰዓት በፌዴሬሽኑ የመራርነት ስራ ላይ ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ስለማይገኙ በእርሳቸዉ ምትክ የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዚዳንት በመሆን አቶ አበበ ገላጋይ የተመረጡ ሲሆን የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሜቴ አባል በመሆን ደግሞ አቶ ዮሴፍ ካሳ ተመርጠዋል። በተጨማሪም እግድ ላይ የነበሩት ወ/ሮ ሶፍያ አልማሙን ወደ ስራ አስፈፃሚነት ስራቸዉ ተመልሰዋል።

በአርባምንጭ ሀይሌ ሪዞርት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረዉ ጠቅላላ ጉባኤም የተለያዩ ወሳኔዎች ተላልፈዉበት እንዲሁም ሪፖርቶች የፀደቁበት ሲሆን በዕለቱም በቅርቡ በሞት ለተለዩት ዶ/ር ሲራክ ሀ/ማርያም የህሊና ፀሎት ተደርጎ ጠቅላላ ጉባኤዉ ተጠናቋል።

በተያያዘም የፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጋቢት ወር ላይ በአዲስ አበባ የሚደረግ ሲሆን አጠቃላይ የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ደግሞ ሰኔ ወር ላይ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ እንደሚደረግ ተገልጿል።
አስተያየት ይስጡ