“በእኔና በኢትዮዽያ ቡና ጉዳይ ብቸኛው ተስፋ ቆራጭ እኔ ብቻ ነኝ”
“ብሄራዊ ቡድን ያሰለጠኑትን አሰልጣኞች ጨምሮ ከካሳዬ አራጌና አሸናፊ በቀለ ውጪ ሃሳብ አላቸው ማለት አልችልም”
ዳዊት እስጢፋኖስ/ጅማ አባጅፋር/
የሚገርመኝ ነገር ሲል ትዝብቱን በድፍረት ይናገራል… “እኔ ካለሁበት ቡድን ጋር ሲጫወቱ ሁሉም እንዳያጠፋን ዳዊትን ያዙ ብለው መመሪያ ይሰጣሉ እነዚሁ አሰልጣኞች ብሄራዊ ቡድን ሲይዙ ግን አይመርጡኝም ይሄ ሁሌ ይገርመኛል”ሲል ይናገራል.. “ጠያቂ እንጂ ተሟጋች አይደለሁም… ዲሲፕሊንን በሚገባ አከብራለሁ የቃል የጽሁፍ ይሁን የቅጣት ደብዳቤ ደርሶኝ አያውቅም ይሄን ያሰለጠኑኝን በሙሉ መጠየቅ ይቻላል” ሲልም ያክላል…የመሃል ሜዳው ኮከብ ዳዊት እስጢፋኖስ…..ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ምን ያልተነሳ ጉዳይ አለ…? ለብሄራዊ ቡድኑ ለምን እንዳልተመረጠ፣ ብሄራዊ ቡድኑ የሚመረጠው በግሩፐኞች ነው ማለቱ፣ ኢትዮዽያ ቡና መግባት ለምን እንዳልቻለ፣ የሰበታ ከተማው ኮንትራት ለምን እንዳልታደሰና ወደ ባህር ዳርስ ለምን እንዳልተጓዘ፣ ስለ ካሳዬ አራጌና አሸናፊ በቀለ፣ ስለ ኢትዮዽያ ቡና ደጋፊ፣ 2003 ስለነበረው ቡናና ባለፉት 10 አመታት ሰለነበረው የቡና ቦርድ ስብስብ….በርካታ ጉዳዮች ላይ የሚሰማውን በድፍረት መልሷል።
ሀትሪክ:- እረፍቱ እንዴት አለፈ..?
ዳዊት:- ዘንድሮ ከሌላው አመት የተለየ ይመስለኛል… በፊት ደርሶ መልስ ስለነበር ውድድሩ ከከተማ ውጪ ተጫውተን በመልሱ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ስለምንጫወት በአጋጣሚው የመገናኘት እድሉ ነበረን ዘንድሮ ግን ረጅሙን አመት ያሳለፍነው በካምፕ ነው በዚህም ከቤተሰብ ጋር የበለጠ መነፋፈቅ ውስጥ ገብቼ ነው ያሳለፍኩትና በናፍቆት ውስጥ ሆነን ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ችለናል… ናፍቆቱን ለመወጣት ከባለቤቴና ልጆቼ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ነበረኝ ብዙ ቦታ በማየት ክረምቱን አሳልፈናል ሰሞኑን ደግሞ የ2ኛ ልጄ ሁለተኛ አመት ልደት አክብረናል በአጠቃላይ ዕረፍቱ ጥሩ ሆኖ አልፎልኛል ማለት እችላለሁ
ሀትሪክ:- ቀለል ያለ ልምምድስ አልተሰራም ..ተወፈረ?
ዳዊት:- /ሳቅ/ ያማ አይቀርም … የተለመደው የ2 ወር እረፍት ከኮቪዱ የውድድር መቋረጥ ጋር ተያይዞ ስፖርተኞች ወፍረው ይመጣሉ የሚል ሀሜት አለ ከወሬው ለመራቅ ለጤንነትም ሲባል እንቅስቃሴ ይደረጋል በኮቪዱ ጊዜ ብዙ ነገር ዝግ ስለነበር ውፍረት ሊከሰት ይችላል አሁን ግን ክፍት እየሆነ ስለሆነ ልምምድ አላቆምኩም
ሀትሪክ:- የ2013 የሰበታ ከተማንጉዞ እንዴት አየኸው?
ዳዊት:- እንደ ቡድን ከባድ ጊዜ አሳልፈናል… አንድ ቡድን ሊሟላለት የሚገባቸው ነገሮች በአብዛኛው ሳይሟላ ነው ላለመውረድ ተጫውቶ በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ለመጨረስ ተችሏል ውጤቱ ባያመረቃም እስከ ዋንጫ የመፎካከር አቅም ነበረው ነገር ግን ከክፍያ ጋር ተያይዞ ደስ የማይል ጊዜ እንደማሳለፋችን እግር ኳስን በሚጻረሩ መንገድ ልምምድ እየሰራን የተገኘ ውጤት ነው በሳምንት አንዴ ብቻ ልምምድ ሰርተን ግጥሚያ የምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ነበር እንዲህ ምስቅልቅል ብሎም ውጤቱ መጥፎ አልነበረም እንደውጤት መጥፎ ባይሆንም እንደ አመራር ደካማ ጊዜ አሳልፈናል።

ሀትሪክ:- በግልህ ጥሩጊዜ ማሳለፍህን ታምናለህ?
ዳዊት:- ብዙ ውጣውረዶች በነበሩበት ሂደት እንደ ዳዊት መጥፎ ሲዝን አላሳለፍኩም በዲ ኤስ ቲቪ መተላለፉ እንደገና ጨዋታዎችን የማየት እድል ነበረና ለራሴ ጥሩ እንዳሳለፍኩ እየነገርኩት አመቱ ተጠናቋል። ስህተትን ለማረም እድል ነበረና እንደ ሰበታና እንደዳዊት ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል ብዬ አምናለሁ።
ሀትሪክ:- የበርካቶችም እምነት ዳዊት ጥሩ ጊዜ አሳልፏል የሚል ነው… ለምን ለብሄራዊ ቡድን አልተመረጠም የሚሉም ወገኖች ነበሩ… አንተስ ባለመመረጥህ ተከፍተሃል? ወይስ?
ዳዊት:- ለሀገሬ ብሄራዊ ቡድን ባለመመረጤ ተበሳጭቻለሁ.. መለስ ብለን የሊጉን ጨዋታዎች ስናይ ዳዊት ያሳየው አቅም ያስመርጠዋል ብዬ አምናለሁ ሌላ ጊዜ ምርጫው በደፈናው ነበር የክልሉን ጨዋታ ተመልካቹም አሰልጣኙም ሆነ ጋዜጠኛው የማየት እድል አልነበራቸውም ዘንድሮ ግን እድሎች ተፈጥረዋል በተጨማሪ ዲኤስቲቪ ቁጥራዊ መረጃዎችን ይለቃል ይሄን የማየት እድል ስለነበር እስከዛሬ መመረጥ ነበረብኝ ካልኩት በላይ ዘንድሮ በልበ ሙሉነት መመረጥ ነበረብኝ ብዬ አምናለሁ..ለዚህ ነው አለመመረጤ ያበሳጨኝ.. ባለመመረጤም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተከፍቻለሁ።
ሀትሪክ:- የሰበታ ከተማ ውልህስ አለመታደሱ ምክንያቱን አውቀኸዋል? የክለቡ ስራ አስኪያጅ አንተና መስኡድን ጠብቁ ብለዋችሁ እንደነበር ሁሉ ሰምቻለሁ..እውነት ነው?
ዳዊት:- እውነት ነው እረፍት እያለን ስራአስኪያጁ አቶ አለማየሁ እንደምንቀጥል ነግረውን ነበር ነገርግን አልሆነም አሰልጣኙም ዘላለም ሽፈራው ስላልፈለገን ነው የአሰልጣኙ አለመፈለግ ደግሞ እግርኳስኛ በመሆኑ አልተከፋሁም… በርግጥ አሰልጣኙ ድርጊቱን በተደጋጋሚ ማድረጉ ቅር ያሰኛል። መከላከያ ላይም ውላችን ሲያልቅ እሱ ተረከበና አልፈልግም ብሎ ተሰናበትን ከዚህ በፊትም ድሬዳዋ ከተማ አስፈርሞኝ ውሉ ፌዴሬሽን ሄዶ ሊጸድቅ ሲል አይቻልም ብሎ ለቀናል ይሄ አሁን ገና ሰበታን እንደተረከበ መቀጠሉ ቅር ያሰኛል..የተለየ ግንኙነት ወይም ጸብ ያለን እስኪመስል ድረስ መከታተሉ ገርሞኛል በርግጥ ግሩፐኝነት በበዛበት መሆኑ ላያስገርም ይችላል በሙያ ወይም በአቅም እየተሰራ አለመሆኑ ሙያውን በማያከብሩ ግለሰቦች እየተመራ መሆኑን ያሳያል አንዳንድ አሰልጣኞች ሌላውን ለማጥቃት የሚመጡ ይመስላል። ከነበረኝ ብቃት አንጻር አለመቀጠሌ በአሰልጣኙ ውሳኔ መሆኑን ሰምተናል ይሄ አድሎአዊ አካሄድ ግሩፐኝነትን የሚያሳይ ከብቃት አንጻር ሳይሆን አብሮ በመብላትና መጠጣት የሚሰራ መሆኑን አሳይቶኛል ይህን ማድረግ አለመቻሌ አሁን ድረስ እየተገፋሁ እንድመጣ አድርጎኛል
ሀትሪክ:- እየተገፋህ ጅማ ደርሰሃል… ጅማ አባጅፋር እድለኛ ነው ምርጡን ዳዊት ነው ያስፈረመው ማለት ይቻላል?
ዳዊት:- አዎ ትክክለኛ አገላለጽ ነው አመቱን በጥሩ አቋም እንደማሳለፌ በቀጣይ የተሻለውን ዳዊት መጠበቅ ተገቢነት ያለው ነው ሁሌ መታሰብ ያለበት ወርቅ ታሽቶ ተፈትኖ ወርቅ እንደሚሆን ማለት ነው.. ሜዳ ውስጥ የሚተላለፉ መልእክቶችን የማስተላለፍ ችግር ሲፈጠር ማኔጅ የማድረግ ስራ የሚሰራው በሲኒየር ተጨዋቾች ስለሚሆን ጅማ አባጅፋርም ያንን ግልጋሎት ያገኛል ስለዚህ ጅማ አባጅፋር ምርጡን ዳዊትን ነው ያገኘው ማለት ይቻላል።
ሀትሪክ:- አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለና ዳዊት የአጨዋወት ፍልስፍና ልዩነት አላቸው የሚሉ ወገኖች አሉ.. ምን ምላሽ አለህ?
ዳዊት:- ሁለታችን አብረን የመስራት እድል የተፈጠረልን ለሁለተኛ ጊዜ ነው ስለዚህ እንተዋወቃለን ማለት ነው አሰልጣኝ አሸናፊ ደግሞ የራሱ ፍልስፍናና አጨዋወት ያለው አሰልጣኝ ነው አሁን ላይ የሚከተለው ፍልስፍና ምንም ይሁን ምን ለፍልስፍናው ታማኝ ነው የሰራቸውን ቡድኖች እናውቃለን በተደጋጋሚ ቡድኖቹንም አሳይቶናል ይሄ የአሸናፊ ቡድንነው ብለን መናገርም እንችላለን ተመጣጣኝ ተጨዋቾችንም አካትቶ አሳይቶናል ቡድኑንምእንዴት እንደሚሰራ የሚያውቅ ሃሳብ ያለው አልጣኝ ነው ስለማውቀውም ጭምር ምርጫዬ አድርጌዋለው በርሱ ሀሳብ ውስጥ እንደምሄድ ሀሳቡ የሚገዛኝ እንደሆነ አምኜበታለሁ ምንም አይነት የጨዋታ ስታይል ቢመጣ አብሬ መጓዝ እችላለሁ በአጠቃላይ አሰልጣኝ አሸናፊ ሀሳብ አለው በርሱ ሀሳብ ውስጥ የመግባት አቅም ስላለኝ የሚፈጠር ችግር የለም ባይ ነኝ። በኔ እምነት ሀሳብ ካላቸው አሰልጣኞች ቁጥር አንዱ አሸናፊ ነው ብዬ አምናለሁ።
ሀትሪክ:- ኢትዮዽያ ቡናስ እገባ ይሆን ካሳዬ ጋር እፈርም ይሆን የሚል ጉጉት አልነበረህም?
ዳዊት:- /ሳቅ/ ለመግባት ፈልጌ በተደጋጋሚ ሳይሳካ ሲቀር መቀለድ ጀመርንኮ… ብገባ ነው የምገረመው ወደሚለው ዞሬያለሁ/ሳቅ/ ትላንት አይገባም ያሉት የቦርድ አመራሮች ዛሬ ይግባ ይላሉ ብዬ አልጠብቅም ምክንያቱም ተሸናፊ ናቸውና.. በጉዳዩ ላይ ተሸናፊ የሆነ ደግሞ አሸናፊ አይሆንም በንግግር ወደተሻለው ጉዳይ መምጣት ይቻላል መመለስ አልረፈደም ነገር ግን መነጋገር መወያየት አንፈልግም የሚሉ አመራሮች ባሉበት ሰዎች ተመልሰው ገብተው ይሰራሉ ማለት ዘበት ነው። በኔና በቡና ጉዳይ ብቸኛው ተስፋ ቆራጭ እኔ ብቻ ነኝ።

ሀትሪክ:-የወጣ አይመለስም የሚል አቋም አላቸው ከተባለኮ ዳዊት አይመለስም ይሄስ እንዴት አገኘኸው?
ዳዊት:- አዎ የተባለውንማ የምሰማው በመላ ምት ነው.. ተጠቅመውበት ስለማያውቁ ይህን ህግ ያወጣሉ ብዬ አላምንም ህግ ቢሆን ኖሮ በዚህ አምስት አመታት ብቻ ከዋና ስራአስኪያጁ ጭምር ከ10 ሰው በላይ ወጥተው ተመልሰዋል.. የሚመስለኝ የተጻፈ ህግ ስላልነበር ትተውት ይሆናል ብዬ አስባለሁ በመነጋገር የማያምን ያረጀ አስተሳሰብ /ይቅርታ ለዚህ አባባሌ/ የማይለወጥ ጊዜውን የማይመጥን ሀሳብ ይዘህ ግትር የምትል ሰው ላይ ዝም ብለው የሚፈርጁ መሆናቸው ያሳዝናል። በዚህ ላይ ደግሞ ለምን ሆነ ለምንስ አልሆነም ብሎ የማይጠይቅ ደጋፊ ባለበት ዳዊት ይመለሳል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው እንደ ዳዊት ግን የመከጀል ነገር ውስጤ አለ።
ሀትሪክ:- ገንዘቡን መልሶ ይቅርታ ጠይቆ መግባት ይችላል የሚል ሃሳብም አለ…የምትመልሰው ብር ካለ ለምን መልሰህ አትገባም?
ዳዊት:- /ሳቅ/ በነሱ በኩል ለኔ የቀረበ ጥያቄ የለም ነገር ግን የሚመለስም ብር የለም ይቅርታ የምጠይቀውም ነገር የለም በተቃራኒው ከምፈልገው ቦታ በመባረሬ ካሳ ተሰጥቶኝ ነው ወደኢትዮዽያ ቡና መመለስ ያለብኝ.. በህግ በፍትህ አካል ተዳኝተን ከተሸነፉ ህግን ተጻርረው ነው የወሰኑት ብሎ ፌዴሬሽኑ ከወሰነልኝ ይቅርታ የሚጠበቀው ከነርሱ ነው የማዝነው ለደጋፊው ነው የማይጠይቅ ደጋፊ ዝም ብሎ ማሊያ ለብሶ መዞር ሳይሆን ጠያቂ መሆን አለበት በአንዳንድ ነገሮች መደለል ደጋፊ አያስብልም እግርኳሱን አይጠቅምም ቡና ዋንጫ ለምን አይወስድም?ለምንድነው ትልቅ የማይሆነው? ለምንድነው የራሱ ስታዲየም የማይኖረው? ለምንድነው ትልልቅ የሚባሉ ተጨዋቾችን ከፍሎ የማያመጣው? ብሎ መጠየቅ የማይችል ደጋፊ ነው ያለው… መጠየቅ ከተቻለ የዳዊት ጥያቄ መልስ ይመለሳል።
ሀትሪክ:- እናንተ እያላችሁ ዋንጫ ካነሳ ዘንድሮ 10ኛ አመት ሞላው…ይሄስ ለምን ሆነ? ከናንተ ጊዜስ ምን የተለየ ነገር አለው?
ዳዊት:- በወቅቱ የነበረው መልካም አስተሳሰብ ፍቅር መከባበር ነው ዋንጫ እንዲገኝ ያደረገው… ያኔ ከክለቡ ቦርድና ፕሬዝዳንት ጀምሮ እስከ ኳስ አቀባዩ ድረስ በተዋረድ አስተዋጽኦ ነበራቸው የዚያ ውጤት ነው ዋንጫ ያስገኘው… በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ አቶ ኤሊያስ ኡመር ይባላሉ የትራኮን ሪልስቴት ባለቤት ናቸው… እኚህ መሰል ፕሬዝዳንት ከመራህ ዋንጫ ደጋግመህ ታነሳለህ ምክንያቱ ደግሞ እግርኳሱን የሚወዱና ቅርብ የሆኑ ሰው ናቸው እግርኳሱ ገብቷቸዋል ከምላቸው ሰው አንዱ ናቸው ብዬ አስባለሁ እግር ኳስ ከሞራል ጋር የተያያዘ መሆኑ ገብቷቸው በየጨዋታው እየመጡ የቃላትና የገንዘብ ማበረታቻዎችን ያቀርቡ ነበር በወቅቱ በነፍስ ወከፍ ከ1 ሺህ እስከ 3ሺህ ይሰጡን ነበር ለኛ በጣም ቅርብ ነበሩ
ለዚህ ነው ችግር ሳይፈጠር ኮሽታ ሳይሰማ ያሸነፍነው.. ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ችግር ፈጣሪ አልነበሩም.. ከዚያ በኋላ ያሉትንም ጉዳዮች ሲታዩ በችግር ውስጥ የተዘፈቁ ነበሩ እንዴት አስር አመት ሁሉ ዋንጫ አልወሰድንም ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይገባል ዋንጫ ስንወስድ ተከታትሎ የመጣ ነገር አለ የአሁኖቹ ስፖንሰሮችኮ የዚያ ድል ውጤቶች ናቸው ይሄን የሚመረምር የሚጠይቅ አካል ያስፈልጋል ጠያቂው ማነው? ለሚለው ግን እኔ መልስ መስጠት አልፈልግም።
ሀትሪክ:- በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ መፈለግህስ ምን ስሜት ይፈጥራል?
ዳዊት:- በጣም ክብር ይሰማኛል ሁለት ጊዜ የመገናኘቱ እድል ነበረኝ በእግርኳሱ ዙሪያ አውርተን አቅሙን ተረድቻለሁ እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ብሄራዊ ቡድን ያሰለጠኑትን አሰልጣኞች ጨምሮ ከካሳዬና አሸናፊ ውጪ ሀሳብ አላቸው ማለት አልችልም የሁለታችን አብሮ መስራት ያልተፈጠረው በቦርዱ በመሆኑ አዝናለሁ ያለሁበትን ደረጃ የነገረኝ አቅሜን እንድረዳ ያደረገኝ በመሆኑ ክብር ይሰማኛል ሃሳብ ባላቸው ሁለቱም አሰልጣኞች መፈለግ ያኮራል በዚሁ አጋጣሚ አሰልጣኝ ካሳዬንና አሰልጣኝ አሸናፊንም አመሰግናለሁ።
ሀትሪክ:- ሀትሪክ ላይ ግን በሰጠሃቸው ቃለ ምልልሶች ላይ ስለ ሀሳብ ያላቸው አሰልጣኞች ያልከው ነገር አልነበረም ወይም ብዙም አታወራም…አሁን ደግሞ ስለዚህ ነገር እያወራህ ነው..ለውጡ ከየት የመጣ ይሆን?
ዳዊት:- በእግርኳሱ ተደጋጋሚ አይነት የጨዋታ ቅርጽና ቡድን ሲኖራቸው ነው ሀሳብ አላቸው የምለው..ይሄ የእከሌ ቡድን ነው የሚያስብለው ከአመት አመት ክለብ ቢቀያየርም ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የቻለውን ነው። በዚህ አይነት ደግሞ ከምንጠራቸው አሰልጣኞች ብቸኞቹ ካሳዬና አሸናፊ ናቸው… በተለይ አሸናፊ ባለፉት 6 አመታት ያሳየን ቡድን የአሸናፊ ቡድን ነው እንድንል አስገድዶናል። ሌሎቹ አሰልጣኞች ዛሬ ጥሩ ቡድን አሳይተው በቀጣይ ስትጠብቃቸው ተቃራኒ ሆነው ይቀርባሉ ወርቅ ሳይሆን ወርቅ ቅብ አይነት ይሆናሉ አሸናፊና ካሳዬ ወርቅ ወይም ብር ናቸው እንጂ የወርቅ ቅብ አይደሉም ሌሎቹ ግን ኳሷን እንደሚያቋት የሆነ ፍልስፍና እንዳላቸው ነግረውህ ሜዳ ላይ ግን የተገላቢጦሽ ናቸው..እነ አሸናፊ ግን የሚያወሩትን ሜዳ ላይ ይዘው ይገባሉ… ለዚህ ነው ሀሳብ አላቸውያልኩት…. ለዚህም ነው ወርቅ ወይም ብር እንጂ እንደሌሎቹ ወርቅ ቅብ አይደሉም ያልኩት..
ሀትሪክ:- ከኢንስትራክተር አብርሃም ጋር ለባህር ዳር ትፈርማላችሁ ሲባል ቆይቶ ሳይሳካ ቀርቷል..በክፍያ ነው? አሰልጣኙ አልፈለጋችሁም? ወይስ ከአሰልጣኙ ጋር ዞሩ እንዳትባሉ?
ዳዊት:- /ሳቅ በሳቅ/እግዚአብሄር ይመስገን በዚህ መንገድ አልታማሁም አብሬ ተጉዤም አላውቅም።ነገር ግን ጥሩ የውድድር አመት ካሳለፍክ የታየ እውነት ስለሚሆን ዝውውር ሊከሰትይችላል..ይሄ የሚያሳማው ተቀያሪ የነበረ በጉዳት ወይም በሌላ ምክንያት ካልተጫወትክ ነው አብረህ ስትጓዝ የምትታማው…ከነዚያ ነጻ ነኝ…ጥሩ ጊዜ ከማሳለፋችን አንጻር ወደባህር ዳር ይጓዛሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር በቃ ግን አሰልጣኙ አልፈለገም ነገርግን ምርጫዎቹ እግርኳሳዊ ቢሆኑ መልካም ነው.. እኔ ከአሰልጣኝ አብርሃም በፊት ነው ሰበታ ከተማ የገባሁት….2013 ላይ አብረን የሰራነው መርጦ አስፈርሞኝ ሳይሆን ውሌ አስገድዶኝ ነው…. የአሰልጣኝ አብርሃም ምርጫ ሆኜ አልነበረም የቆየሁት… አሰልጣኙ ወደሌላቦታ ሲሄድ አለመጓዜ ያልገረመኝ ለዚያ ነው.. በርግጥ መናገር የምፈልገው እኔን የሚመርጡኝ ሀሳብ ያላቸው አሰልጣኞች ብቻ ናቸው
ሀትሪክ:- ተሟጋች ነውጠኛ ተጨዋች ስለሆንክ ይሆን?
ዳዊት:- /ሳቅ/ ተሟጋች አይደለሁም ጠያቂ ግን ነኝ አብረውኝ የሰሩ አሰልጣኞች መናገር ይችላሉ ለአንድም ቀን ጎርብጫቸው አላውቅም። ምክንያቱም በሲስተም ውስጥ የመሄድ ችግር የለብኝም አሁን ደግሞ እንደ በፊቱ አይደለሁም ትዳር አለ ልጆች አሉና አሰልጣኙ አድርግ የሚለውን የማድረጉ ነገር አለ.. ግን ዳዊት እስጢፋኖስ የሚለው ስም የሚያስፈራ መሰለኝ/ሳቅ/ በዘመኔ በምንም ምክንያት አንድም ቀን የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝም ይሁን ተቀጥቼ አላውቅም በቀጣዩ አመት ግን ያሳምጻል ተብሎ ሌላ ስም ይሰጠኛል የኔ መንፈስ እንዳይሆን የሚያስጨንቃቸው የመንፈስ ጭንቀት ይመስለኛል/ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ :- የደመወዝ ገደብ መነሳቱን እንደ ተጨዋችና እንደ ተጨዋች ማህበር ስራ አስፈጻሚነት ምን ትላለህ?
ዳዊት:- ይሄ ትክክለኛው መስመር እየገባን ይመስለኛል… አለም እየተከተለው ወዳለው መስመር ውስጥ ገብተናል ማለት እችላለሁ የኢትዮዽያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር ከመጣና ጥያቄ ማንሳት ከጀመረ በኋላ ለውጦች እየታዩ ነው ይሄም ያስደስታል ተጨዋቹ ራሱ ሄዶ መደራደር መጀመሩ ሙስናን የሚቀንስ ይመስለኛል ነገር ግን የቀደመው አሰራር ያመጣው ችግር ገና አልተወገደም እሱን ለማስተካከል እንጥራለን አንድ ላይ ብትችልም ባትችልም በጋራ ተወቀጥ የሚለው ህግ በመወገዱ ደስ አሰኝቶኛል በርግጥ ግሩፐኛ በዝቷል ቡድን ያወረደ አሰልጣኝና ተጨዋቾች ሌላ ቡድን ተያይዘው ሲሄዱ ይታያል ጥሩ ባይሆኑም ክለብ አያጡም በመደዋወል ሻይቡና በማለት በችግሬ ጊዜ አብሮኝ የነበረው ማነው በሚል ሲሰራ ቆይቷል። ማነው ምርጡ አቅሙ ምን ይመስላል የሚለው ቀርቷል ለዚህ ነው የገንዘብ ልዩነቱ የጠበበው ማን ነበር መልካም ለኔ ማነው ሲደውልልኝ የነበረው
የሚለው ከችሎታ መመዘኛ ውጪ ሆኗል ማለት ነው አንደኛው በችሎታው ሌላኛው በመደወሉ እኩል ክፍያ ያገኛሉ ግሩፐኝነት ካልጠፋ ይሄ ችግር ይወገዳል ብዬ አላስብም ማህበራችን ግን እስከቻለው ድረስ የሚታገለው ይሆናል። አብሮ መብላትና አብሮ መጠጣትን ከእግርኳስ ጋር ማገናኘት ኋላቀርነት በመሆኑ የምንታገለው ይሆናል። በርግጥ ትልቁ ፈተና እንደሚሆንብን አምናለሁ…
ሀትሪክ :- እስቲ ወደ ብሄራዊ ቡድን እናቅና…ከ8 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፈው ቡድን ውስጥ ይሁን ለአለምዋንጫ ማጣርያ ከተጠሩት ተጨዋቾች ዝርዝር ውስጥ ስምህ የለም… እድል? ወይስ ፊትህ ያስፈራል?
ዳዊት:- እኔን የሚመርጠኝ ሀሳብ ያለው ሰውነው የሚለውን አቋሜን አትርሳ…ያው ብሄራዊ ቡድኑ ላይ አሳብ ካለ መኖር ነበረብኝ ብዬ አስባለሁ አመቱን ስናየው ከነበረኝ ጥሩ አቋም መመረጥ ነበረብኝ ብዬ አስባለሁ… ምርጫው የአሰልጣኞቹ ቢሆንም በጣም የሚያስከፋ ነው ከሌላው አመታት በዘለለ ቅር ተሰኝቻለሁ….
ብሄራዊ ቡድኑን የመረጡት አሰልጣኞች ጨዋታዎቹን ደግመው ቢያዩት ደስ ይለኛል… ማን የተሻለ ነበር ጥሩ የነበረው ማነው ለሚለው ምላሽ ቢያገኙ ደስ ይለኛልና ዳዊት የሚባለው ስምማ ተጽዕኖ አምጥቶብኛል..ትልቁ ተጽእኖ ያመጣብኝ ለተጨዋቾች መብት መቆሜም ይመስለኛል። የኛ ማህበር መመስረቱ ደግሞ ያስደነገጣቸው ይመስለኛል ለዚያም ነው ብዙ ቦታ ላይ የተገፋሁት..በርግጥ ከማህበሩም በፊት ብዙ አልተመረጥኩም አሁን ግን ጠብቄ አለመሳካቱ አናዶኛልም ከብዙ ነገር ጋርም ይያያዛል ያው እንዳልኩት ያለው ግሩፑ ካልወደደህ እንኳን ብሄራዊ ቡድን ክለብም ላትገባ ትችላለህ ሰፈር ውስጥም ላትጫወት ትችላለህም ምንም ማድረግ አልችልም ለዋሊያዎቹ ባለመመረጤ እስከዛሬ እንደማዝነው አሁንም አዝኛለሁ ወደፊት ዳዊት እስጢፋኖስ የሚለውን ስሜን ቀይሬ እመጣ ይሆናል/ሳቅ/

ሀትሪክ:-ይሄ የግሩፑ ጉዳይ እንዲወገድ ፌዴሬሽኑ ምን ማድረግ አለበት ?
ዳዊት:- ፌዴሬሽኑም ይሁን የተጨዋቾች ማህበር ገብተው የሚያጸዱት ጉዳይ አይደለም…ለህሊናቸው ሲሰሩ የሚቆም ብቻ ይመስለኛል ..እግርኳስ ብቻህን የምትሰራው ሳይሆን በግሩፕ የሚሰራ ነው ነገር ግን ግሩፑ ኦፊሺያል ሊሆን ይገባል ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለብ ቀጥሮ የሚሰሩ ከሆነ ተመካክረው በሚሰሩት ስራና ውሳኔያቸውን እንዲሁም ምርጫቸውን ታከብራለህ
ቁጥራዊ መረጃና አመታዊ ብቃቱ ስለሚለካ በውሳኔው የማመን ነገር ይኖራል። አሁን ግን ከእግርኳሱ የራቁ ሰዎች ናቸው ብሄራዊ ቡድኑም ላይ ሆነ ክለቦች ላይ ያሉትና የትም እንደማያራምድ ሊያውቁ ይገባል አሰልጣኙም ሆነ ተጨዋቹ ለሙያችን ክብር ይሰጠን እያልን ራሳችን አላስከበርነውም… ለሙያና ለባለሙያው ክብር መስጠት የግድ መሆኑን አምናለሁ ያኔ ነው ዳዊት በአቅሙ ሊመረጥ ወይም አቅም የለውም ተብሎ የሚዘለለው..ያ ካልሆነ ደስ አላልከኝም አልደወልክልኝም ከኔ ጋር ጥሩ ግኑኝነት የለውም እየተባለ ከቀጠለ ዳዊት ይህን ማድረግ ስለማይችል መቼም አይመረጥም ማለት ነው
ሀትሪክ: በቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጤት ዙሪያ ምን ትላለህ..?
ዳዊት:- እጅግ በጣም ተቆጨቻለሁ ስፖርት ውስጥ እንዳለ ሰው ደግሞ ሙያው ምን ያህል በአመራሮች ተጽእኖ ውስጥ ወድቆ ውጤት ሊበላሽ እንደሚችል ማሳያ ነው አንገት የሚያስደፋ ነው እኔ ደግሞ እግርኳስ ውስጥ ከአሰልጣኝ ጀምሮ የቡድን አመራር ቦርድ በለው ፕሬዝዳንት አንገታችንን ስንደፋ ስለኖርን ስሜቱን አውቃለሁ እንደ ኢትዮዽያዊ አንገቴን ደፍቻለሁ እንደ ባለሙያ ግን ለሌላ ጊዜ ማስተማሪያ ይሆናል ባይ ነኝ አሁን ጋዜጠኛውን ጨምሮ ጠያቂ ይሁን ጠያቂ ትውልድ ይምጣ ባይ ነኝ ስንጠይቅ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ መከሰቱ አሪፍ ነው ወደ ኋላ እንድንመለስ ያደርገናል የዛሬ 10 ወይም 15 አመት የነበረ ችግር ውጤትኮ ነው የአሁን ብቻ ነው? አይመስለኝም ችግሩ ሲስተም ስላተዘረጋ ነው የተከሰተ ነው
ሀትሪክ:- ኢትዮዽያ ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈች የዘንድሮ ኦሎምፒክ ደካማ ውጤት ደግሞ ከ31 አመት በኋላ የተመዘገበ ነው..ግጥምጥሞሹን እንዴት አገኘኸው?
ዳዊት:- /ሳቅ በሳቅ/ይሄ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ነው የሚሆነው ሌላ ምንም አይባልም ነገር ግን ሁለቱም ለመፍትሄ አሪፍ አጋጣሚ ነበሩ…በኳሱ ከ31 አመት በኋላ ማለፋችንን ለተሳትፎ ብቻ አደረግነው እንጂ..ራሳችንን መገምገምና መመርመር ባለመቻላችን 3 የአፍሪካ ዋንጫ አልፎን እንደገና ከ8 አመት በኋላ አለፍን..በየአመቱ ማለፍ የምንችልበትን እድል መፍጠር እንችላለን ብዬ አምናለሁ ሀሳብና እውቀት ካለ ማለፍ ይቻላል.. ምክንያቱም ከ31 አመትም ይሁን ከ8 አመት ስናልፍ ያለፍነው በዚሁ በኢትዮዽያዊው ተጨዋችና በኢትዮዽያዊ አሰልጣኝ ነውና..በየ 2 አመቱ ይቻላል ባይ ነኝ ይህን የኦሎምፒክ የታሪክ ግጥምጥሞሹን ለመልካም ካዋልነው እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ አይተን ከተነሳን ለቀጣይ መማርያ መለወጫ ልናደርገው እንችላለን ብዬ አስባለሁ የሀገራችን ዜጎች እኛ ልናገኝ የሚገባንን ሜዳሊያ ሲወስዱብን በዚህ ብቻ ልናዝን ይገባል ባይ ነኝ። አትሌቶቹ የአመራርና የሲስተም ችግር አለ ብለው ስለሄዱ መነሻውን አይተን መፈተሽ እንችላለን ብዬ አስባለሁ።

ሀትሪክ :- የቀረ ነገር አለ?
ዳዊት:- አዎ… ባለሙያ ሲባል ተጫውቶ አልፎ እያደገ ቢሄድ መልካም ውርርስ ይሆናል በርግጥ ሌላው አያሰልጥን ሳይሆን ይበልጥ የሚሰማው ተጫውቶ የመጣ ከሆነ ነው ተብሎ ይታመናልና እግርኳስን ያሳድጋሉ ያንጻሉ ተብለው የመጡት ወጣት አሰልጣኞች ላይ መናገር እፈልጋለሁ የተሻለ ያደርጋሉ ተብለው መጥተው የዛሬ 40 አመት የተውነውን ይዘው የመጡ ነው የሚመስለኝ.. የተለመደ አሰራር..አብረዋቸው የሰሩትን የበሉትና የጠጡትን ይዘው የመዞር አዝማማሚያዎችን አይቻለሁና መታረም ያለባቸው ይመስለኛል። እግር ኳሱን እንለውጣለን አንድ ርምጃ ከፍ እናደርጋለን ብሎ ከታሰበ ይሄ ወገንተኝነት መቆም አለበት አገራችን እየታመሰች ያለችውም በዚህ የወገንተኝነትና የክለላ ጠባብነት የመጣ ነው ይሄ ደግሞ ኳስ ውስጥ ሲታይ ያበሳጫል አለም አቀፋዊ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል? በተለይ በወጣቶቹ በጣም ነው የማዝነው እንዴት ነው ኳሱን የሚለውጡት? ሰዎችን ከቦታ ቦታ ከማዘዋወር ሀሳብ ይዞ መምጣት ነው የሚያዋጣው …ወጣቶቹ አሰልጣኞች መልካም ግንኙነት ሳይሆን መልካም እግርኳስን ማስቀደም አለባቸው..ብሄራዊ ቡድንም ይሁን ክለቦች ላይ የሚቀድመው መልካም ጨዋታ ሳይሆን መልካም ግንኙነት ነው… ለነገሩ ቅርብ ስለሆንኩ ነው የማወራው ያን ማድረግ ያልቻሉ ሰዎች ከኳሱ ወጥተዋል ወይም ለመውጣት እየተንደረደሩ ናቸው..ወይም በቅርቡ ይወጣሉ..ይህን አባባሌን ደግሞ እግርኳሱ ውስጥ ያሉ መቶ በመቶ ያውቁታል። ወጣቶቹ የተገፉበትን የተበደሉበትን ሊያሻሽሉ የመጡ ነው የመሰለኝ የማየው ግን እንደዚህ አይደለም ትላንት ተገፍታችሁ በመጣችሁበት መንገድ ዛሬ ሌላው ላይ ማሰብ የለባችሁም እያልኩ ነው… አቅም ላይ የተመረኮዘ ስራ ብቻ እንዲሰሩ አደራ እላለሁ ዕውቀትና ችሎታ ብቻ ይቅደም ሙያውን አስከብሩ ለማለት ነው
ሀትሪክ:- የምታመሰግነው አለ?
ዳዊት:- እዚህ ያደረሰኝን አምላኬ ልዑል እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ… ከዚያም መላው ቤተሰቤን ፣ ባለቤቴንና ልጆቼን ፣ በኔ ላይ ያመኑትን አሰልጣኞች፣ አሰልጣኝ ካሳዬና አሰልጣኝ አሸናፊን፣ ጓደኞቼን፣ ለኔ በጎ የሚመኙትን ከጎኔ የማይለዩትን በሙሉ አመሰግናለሁ
አስተያየት ይስጡ