በ2013 የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛና ሁለተኛ ሆነውና በማጠናቀቅ በአፍሪካ ደረጀ ኢትዮዽያን የሚወክሉት ፋሲል ከነማና ኢትዮዽያ ቡና ዝግጅታቸውን በቀጣይ ሳምንት ይጀምራሉ።
በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ የሚሳተፈው ፋሲል ከተማ በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ወደ ባህርዳር በማቅናት ዝግጅቱን እንደሚጀምር አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናግረዋል።
“ተጋጣሚያችን ማን እንደሆነ ባናውቅም ለተሻለ ውጤት አልመን ዝግጅታችንን እንጀምራለን ከተጨዋቾቼ ጋር በየጊዜው በስልክ እየተገናኘሁ ስለዝግጅታችን እናወራለን ሀገር እንደመወከላችን ትልቅ ሀላፊነት አለብን” ያሉትንም አሰልጣኙ “የብሄራዊ ቡድናችን የአለም ዋንጫ ማጣርያ ከኛ ጋር እንዳይጋጭ ስጋት ውስጥ ገብቻለሁ ፌዴሬሽኑ ሀገር መወከላችንን አይቶ ማስተካከያ እንደሚያደርግ ተስፋ አለኝ” ብለዋል።
በጉዳዩ ዙርያ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በሰጡት ምላሽ ” ከጋና ብሄራዊ ቡድን ያለው የአለም ዋንጫ ማጣርያ ከነሀሴ 26-28 ጋና በምትመርጠው ቀን ጋና ላይ ስለሚደረግ ዋሊያዎቹ ነሀሴ መጀመርያ ዝግጅት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
የሻምፒየንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ጨዋታዎች ደግሞ ዻጉሜ ውስጥ የሚደረግ በመሆኑ ካፍ ማስተካከያ ያደርጋል ብለን እንገምታለን በዝግጅቱ ዙርያ በክለቦቹና በዋሊያዎቹ አሰልጣኞች መሃል የውይይትና የመረጃ መለዋወጥ ቢኖር ብዙ ነገር ሊስተካከል ይችላል ብለን እናስባለን” ሲሉ ተናግረዋል።
በኮንፌዴሬሽን ካፕ ሀገራችንንና የሚወክለው ኢትዮዽያ ቡና ለዚህ ውድድርና ለ2014 ፕሪሚየር ሊግ ውጤታማነት በቢሾፍቱ ከነገ ጀምሮ ዝግጅቱን እንደሚጀምር የክለቡ ኦፊሺያል ፔጅ ይፋ አድርጓል። በኮንፌዴሬሽን ካፕ ጠንካራ ሆኖ የተሻለ ጉዞ ለማድረግ ራሱን የሚፈልጋቸውን ተጨዋቾች ሲያስፈርም መቆየቱ ታውቋል።
ሁለቱ ክለቦች የመርሃ ግብር ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር የመጀመርያ ጨዋታቸውን መስከረም 10 እና 12/2021 ሲያደርጉ የመልስ ጨዋታቸውን ደግሞ መስከረም 17 እና 19/2021 እንደሚካሄድ ካፍ ያወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።
አስተያየት ይስጡ