“የቀጠረኝ ኢትዮጵያ ቡና ነው እያገለገልኩ ያለሁት ግን ካሳዬን ነው”
ዘላለም ፀጋዬ (የኢት.ቡና ምክትል አሰልጣኝ)
በጋዜጠኝነት ህይወቴ ከበርካታ አሰልጣኞች ጋር ድፍረት የተሞላው ቃለ ምልልስ ሰርቻለሁ…የዛሬ እንግዳዬም ከነኚያ መሃል አንዱ ነው… አንዴ ከርሱ ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ ስራውን አሳጥቶታል የደደቢትን ተስፋ ቡድን ይዞ መስቀል አደባባይ ልምምድ መስራታቸውን በተመለከተ ቅሬታውን ተጨዋቾቹ ሊጎዱ ይችላሉ ብሎ እንደሚሰጋ የተናገረበትን ቃለ ምልልስ ጋዜጣ ላይ ይዤ ከመውጣቴ የክለቡ አመራሮች ተቆጡ ከርሱም ጋር ተጋጩ…እናም ከክለቡ አሰልጣኝነት ተነሳ..ለምን አልዋሽህም አሉት እርሱም አልዋሽም ብሎ ቦታውን በኩራት ለቀቀ…ከአመታት በኋላ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ፍቃድ የሰጠበትን ቃለምምልስ ሃትሪክ ላይ ሰራን.. ከካሳዬ አራጌ ጋር እጅና ጓንት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሆነው ያለፉት 3 አመታት በኢትዮዽያ ቡና አሰልጣኝነት ዘልቀዋል…አሰልጣኝ ዘላለም ጸጋዬ ከካሳዬ ጀርባ ያለው ግድግዳ ግን ብዙ ቅሬታ በሚያቀርቡበትና በሚወዱት ሰዎች መሃል ሆኖ ነገን እያለመ ነው… ከሃትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር የተፋጠጠው አሰልጣኝ ዘላለም ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል…ይሄ ቃለ ምልልስ ከኢትዮዽያ ቡና የመሰናበቻው እንደማይሆን ግን ተስፋ አለኝ…
ሀትሪክ:- አሰልጣኝ ዘላለም ጸጋዬ በኢትዮዽያ ቡና ምክትል አሰልጣኝነቱ ደስተኛ ነው?
ዘላለም:- አዎ…በተለይ ከካሳዬ አራጌ ጋር የርሱ ምክትል ሆኜ በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ
ሀትሪክ:- በነጻነትስ እየሰራህ ነው ማለት ይቻላል?
ዘላለም:- ከአለቃዬ ጋር ተከባብሬና ተግባብቼ እየሰራሁ ነው በተለይ በስነምግባሩ ጥሩ ከሆነው አሰልጣኝ ጋር እየሰራሁ መሆኔ አስደስቶኛል ነጻነቱ አብረኸው ከምትሰራው ጋር ነው የሚሆነው የርሱ እምነቱና ሰብአዊነቱ ይበዛል በመከባበር ውስጥ ሆነን እየሰራን ስለሆነ ምንም የሚጎረብጠኝ ነገር የለም

ሀትሪክ:- ብዙ ጊዜ ምክትሎች ኮን ደርዳሪ ወይም ሰርሳሪ ናቸው ይባላል… አንተስ?
ዘላለም:- በዚህ አይነት መንገድ ውስጥማ የለሁም አንድ አይነት አይዶሎጂ ያለን ሰዎች ነን ምንም የሚያሰራስር ነገር የለም ዝም ብሎ ኮን ደርዳሪም አይደለሁም በምናነሳቸው ሃሳቦች ላይ ተረዳድተን እየሰራን ሶስተኛ አመታችንን ይዘናል።
ሀትሪክ:- ያለፉትን ሶስት አመታት እንዴት ታየዋለህ?
ዘላለም:- ጥሩ ጊዜ ነበረን ጠንካራም ደካማም ጎናችንን እያየን እያረምን ሄደናል የሚሰራ ሰው ይሳሳታል ስህተቶችን እያረምን ተጉዘናል ስህተትን የሚቀንስ አለቃም ስላለኝ ደስ ብሎኛል አመቶችን እየተሻሻልን እየጨመርን ስህተቶችን እያረምን ተጉዘናል
ሀትሪክ:- ከዝውውር ጋር ተያይዞ ትልቁ ድርሻ የካሳዬ ወይስ የዘላለም ነው?
ዘላለም :- በምክትል አሰልጣኝነቴ እገዛዬን የማሳይበት አንዱ መንገድ ምልመላ ላይ ነው። በምልመላና ዝውውር የኔ ተጽዕኖ ብቻ ነው ያለው ማለት አልችልም ምክንያቱም ዋናው አሰልጣኝ አለ እየተማከርን ነው የምንሰራው በመላው አለም ላይ ስካውቲንግ አለ በአለም ላይ ለአጨዋወታችን ይሆናሉ ወይ ተብለው የሚገመግሙና የሚያቀርቡ አሉ እዚህ ግን እንደሱ አይደለም ኤጀንቶች በሚያመጡት ነው… እገሌኮ አሪፍ ነው ተብሎ በሚመጡልንም አይደለም እየመለመልን ያለው…እኛ ዐይን አለን አሰልጣኞችም ነን ለምንፈልገው አጨዋወት ይሆናል ወይም ስህተት ይቀንስልናል ብለን ተጨዋችን እየመለመልን አለን በኢትዮዽያ ቡና የዝውውር ሂደት የተለየ ድርሻ ያለው አንበሳ የለም ምናልባት የሁለታችን ስሜት አንድ በመሆኑ ነው አንበሳ የሆነው…
ሀትሪክ:- አንተ አይተህ ያመጣኸውን ተጨዋች ሌላው አመጣ የሚል ወሬ ሲወራ ይሰማል.. አሉባልታውን ከማጥራት አንጻር የአንተ ስሜት ምን ይመስላል?
ዘላለም:- እኔ አሰልጣኝ ካሳዬ በሰጠኝ ሃላፊነትና መብት ያስፈረምኳቸው ተጨዋቾች አሉ እነዚያን ልጆችን ተጠቅመን ደግሞ እዚህ ደርሰናል የተሰጠኝ ሃላፊነት እንደምወጣ እምነቱን የጣለብኝን ካሳዬን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ የሚያምንብኝ ዋናው አሰልጣኝ ጋር አይኑር እንጂ አሉባልታው በአሉባልታነቱ ይቀጥላል ታማኝ ሆኜ መቀጠል የኔ ሃላፊነት ነው ክዚያ ውጪ ከካሳዬ ጋር ያገናኘኝ ይህን ስራዬን ወድጄዋለሁ
ሀትሪክ:- ከስነ ምግባር ጋር ተያይዞ ተጨዋቾቻችሁን መቆጣጠር አልቻላችሁም ተብሎ ይታማል.. እውነት ነው?
ዘላለም:- በፕሮፌሽናልነት ደረጃ ከሚታዩ ከሚከፈላቸውም አንጻር ሲታዩ ሃሳብ መስጠት እንጂ ማገድ ይከብዳል 130 ሺህ ብር የሚከፈለውን ተጨዋች ከካምፕ አትውጣ በዚህ ግባ በዚህ ውጣ ማለትን ዘመኑ አይፈቅድም። ራሳቸውን ችለው እንዲሄዱ ግን አቅጣጫ እናሳያለን የመጡበትን መንገድንም ማወቅ ይገባል በትእዛዝ ውስጥ የመጣን ተጨዋቾች እንዴት ነው ማስተማር ያለብን የሚለው መታየት አለበት…እያስረዳነው ነው መቀጠል ነው ያለብን ባይ ነኝ.. በቀጣይ ቤተሰብ መስርቶ እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ማሰብ አለበት ያን እያስተማርን መቀጠል እንጂ ሁሌ ቁጣ አያስፈልግም ከዚህ በፊትምኮ ካምፕ ይቅር ተብሎ ነበር ጨዋታው ሁለት ቀን ሲቀረው ነው ካምፕ የሚገቡት..በየትኛውም አለም እንደሚደረገው ተጨዋቾቹ ራሳቸውን መርተው መምጣት ነው ያለባቸው ከአሰልጣኝ ካሳዬ የሚሰጡ ትምህርቶችም እያስተካከላቸው ነው የተስተካከሉም አሉ

ሀትሪክ:- ዝውውር ላይ ምን እያደረጋችሁ ነው?/ ቃለ ምልልሱን የሰራነው ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ነው/
ዘላለም:- ዝውውሩ ከበድ ብሏል.. በርካታ ብሮችም እየተጠሩ ነው በንጽርር የምናያቸውም ነገሮች አሉ… እስካሁን እያናገርን ነው ከክለቡ አቅም በላይ እየተጠራ ነው ይሄን እንዴት ነው የምናስታርቀው የሚለው ነው ዋናው ነገር…አንዳንዱ መላምት ውስጥ ይከታል ተጨዋች አያግኝ አልልም ነገር ሲያገኝ እንዴትና በምን አይነት መንገድ ነው የሚያገኘው የሚለው መታየት አለበት…የሊጉን ክለቦች 16 ሲሆኑ እያንዳንዱ ክለብ በአመት 30 ጨዋታ ይጫወታል ከዚህ 30 ጨዋታ ምን ያህሉን ይጫወታል? የሚለው መታየት አለበት እንደሰለጠነ ሰው ማውራትኮ አለብን የሚጠየቀው ብርና የክለቦች አቅም በጣም ተራርቋል ብር አያገኙ አላልኩም የምትጠራው ብር ግን ከጥቅምህ አንጻር መታየት አለበት
ሀትሪክ:- የነባር ተጨዋቾችን ውል ከማደስ አንጻርስ ምን እየሰራችሁ ነው?
ዘላለም:- ከኛ አቅም አንጻር ነው የምንነሳው… ብዙ መንገድ ተጉዘናል ቡድኑ አቅሜ ይሄ ነው ካለን መስመር ማለፍ አንችልም ያ ከሆነ ሌላ የድርድር ሀሳቦች ይቀርብና ትደራደራለህ ከማቆየት አንጻር የምንችለውን ያህል መጓዛችን የግድ ነው መታወቅ ያለበት ግን አንዱ ተጨዋች ሲሄድ ሌልው መተካቱን ነው… ውል ለማራዘም ታግለን ተጨዋቹ ሳይስማማ ቢሄድ ቅር አይለኝም በመሄዱም ተጎዳን የምል አይነት ሰው አይደለሁም
ሀትሪክ:- ከካሳዬ ምክትልነት ውጪ ሌላ ክለብ ገብቶ የማሰልጠን ብቃት አለኝ ብለህ ታምናለህ?
ዘላለም:- የካሳዬ ምክትል በመሆኔ ያገኘኋቸው ነገሮች በርካታ ናቸው… ትምህርት አይቆምምና ገና ከካሳዬ ላግኛቸው የሚገቡኝ ብዙ ነገሮች አሉ ከርሱ ጋር በመቆየቴም ደስተኛ ነኝ ለጥያቄህ ግን ዋና አሰልጣኝ የመሆን አቅም አለህ ወይ ላልከው አዎ በሙሉ ልብ ነው የምናገረው ወዋና አሰልጣኝ ለመሆን አቅም እንዳለኝ ጥርጥር የለኝም።
ሀትሪክ:- የአቡኪ 29 ግቦች በዋናነት በርሱ አቅም የተገኘ ወይስ በቡድኑ አጨዋወት ያገኘው ነው?
ዘላለም:- አቡበከር ገና ወጣትና ብዙ ተስፋ ያለው ተጨዋች ነው ጥሩ ነገርም አለው… እንደ አሰልጣኝ የርሱ ችሎታ እንዳለ ሆኖ ግን እንቅስቃሴው አቡበከርን እንዲጎላ አድርጎታል ብዬ አምናለሁ።
ሀትሪክ:- የሚወዱህና የሚጠሉህ ተጨዋቾች አሉ… በመሰለፍና ባለ መሰለፍ የመጣ ይመስልሃል?
ዘላለም:- በኳስ ውስጥ ሰላሳ ተጨዋቾች ይያዛሉ… ሰው ናቸውና የሚለያዩበት ነገር አይጠፋም.. አሰልጣኙ ከሚሰጠው ስልጠና አንጻር ቶሎ የሚረዳ ቶሎ የሚገባው አለ..በንጽጽር አወዳድረን ነው የምናሰልፈው.. ሜዳ ላይ ከምንሰጠው ስልጠና አንጻር ነው አድርገውልናል ላልነው ነው ቅድሚያ መሰለፍን የምንፈቅደው.. ያልተጫወተው ቅር ሊለው ይችላል…ቋሚ የገባው ሜዳ ገባ ማለት ተጠባባቂውን መቼም አንጠቀምም ማለት አይደለም.. በቃ በንጽጽሩ ቅር ያለው ሊያኮርፍ ግን ይችላል ይሄን ምን ታደርገዋለህ… ? ምናልባት ቅሬታው ከዚህ ሌላ መነሻ አለው ብዬ አላምንም በነገራችን ላይ የኛ ሀገር ተጨዋቾች ፕሮፌሽናሊዝምን ከማስፈን አንጻር ደካማ ናቸው እግር ኳስን ብቻ ማሰብ በንጽጽር ልዩነት መሰለፍ እንዳለ መረዳትን ይጠይቃል የምሰለፈውም ሆነ የማልሰለፍውም ስለሚወደኝም ሆነ ስለማይወደኝ ነው ማለትን ልክ አለመሆኑን መቀበል ይገባል…
ሀትሪክ:- የቡናን ግብ ጠባቂዎች/ አቤልና ተክለማርያምን/ አናግሬያቸው ተጠባባቂ የምንሆነው በብቃት ማነስ አይደለም ብለዋል…የናንተ ምላሽ ምንድነው?
ዘላለም:- ቅድሚያ ሊጉ ሲጀመር የተሰለፈው አቤል ማሞ ነበር..ያኔም በሰጠናቸው ደረጃ የተሻለ ነገር ያሳየን እርሱ ነበረና ነው… እዚህ ላይ የኛም የብሄራዊ ቡድኑም አጨዋወት መለያየቱን ማወቅ አለብን… ንጽጽሩ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ሳይሆን ከኛው ከኢትዮዽያ ቡና ከውስጣችን ጋር ነው .. እኛ ጋር ያሉት ግብ ጠባቂዎች ሶስት ናቸው በንጽጽር የሚሰለፈው አንዱ ነው ከምንፈልገው አንጻር ተክለ ማርያም ተጠባባቂ ሆነ ማለት አይችልም ማለት አይደለም ነገር ግን በተሻለ መንገድ ብቃቱን ያሳየው ማነው በሚል ነው ቋሚ የምትሆነው ሌላ ጉዳይ የለውም..በቃ እንዲህ ነው መታሰብ ያለበት.. ካሳዬ ጋር የተለየ ሃሳብ ከመጣ ተከራክረን ነው የሚወሰነው… ምንም ተንኮል የለውም እኛ ሰጥተናቸው ተቀብለው በሰጡን ልክ ነው የምናሰልፈው….ተክለማርያምና አቤል ለመሰለፍ ወሳኙ ነገር በእለቱ የሚሰጡን ነገር መሆኑን ሊቀበሉ ይገባል..
ሀትሪክ:- በአጨዋወትም ይሁን በውጤት ከካሳዬ ውጪ አብሬው ብሰራ ደስ ይለኛል የምትለው አሰልጣኝ የለም?
ዘላለም:- ሁሉም አሰልጣኞች ሊከበርላቸው የሚገባ የየራሳቸው ፍልስፍና አለ እንደዛም ሆኖ ስለነሱ እንዲህ ነው ብዬ መናገር አልችልም መናገር የምችለው አጠገቤ ስላለው ሰው ነው.. አንድና አንድ የምናገርለት የተማርኩበት ካሳዬ አራጌ ብቻ ነው ከውጪ ግን ማርሴሎ ቢየልሳ፣ ፔፕ ጋርዲዮላና አርሴን ቬንገር ይመቹኛል።

ሀትሪክ:- እስቲ እንደ ሰው ስብዕና እንዲሁም እንደ አሰልጣኝ ካሳዬን እንዴት ነው የምትገልጸው?
ዘላለም:- በጣም አስተዋይ ቶሎ ለውሳኔ የማይቸኩል አይነት ሰው ነው ተጨዋች በፍጹም እንዳይነካ የሚጥር አስተውለው እንዲጓዙ የሚደግፍ ሰው ነው አሉባልታና ወሬ እሱ ጋር የለም ድብቅ ሰው አይደለም በግልጽነት ያምናል የስራ ሰው ነው አሰልጣኞቹን ተጨዋቾችን ኮሚቴውን የሚያይበት የራሱ መነጽር ያለው ሰው ነው ስህተት አይሰራም እያልኩ ግን አይደለም..ስብዕናው ምርጥ የሆነ ሰውም ባለሙያም ነው ሀገሪቷ እንደዚህ አይነቱ ሰው ያስፈልጋታል ብዬ አስባለሁ
ሀትሪክ:- አሰልጣኝ ዘላለም እምነት የሚጣልብኝ አይነት አሰልጣኝ ነኝ ብሎ ያምናል?
ዘላለም:- አዎ በደንብ ነው የማምነው…
ሀትሪክ:- ከኢትዮዽያ እግርኳስ ላይ እንዲወገድ የምትፈልገው ምንድነው?
ዘላለም:- ሌብነት….በስህተት መራመድ..
ሀትሪክ:- ማለት? እስኪ አብራራልኝ?
ዘላለም:- ልታጫውተው ከምትፈልገው ተጨዋች ገንዘብ ተቀብለህ እንዴት ነው ላቡን የምትጠይቀው? የምትፈልገውን ነገርንስ እንዴት ታገኛለህ? በአይኔ ያየሁትን ነገር ግን የለም በሰማሁት ነገር ግን ከኳሱ እንዲወገድ እፈልጋለሁ… ተጨዋቹ ታዞ እንዲሰራ እውነትን ብቻ ይዞ መጓዝ ያስፈልጋል
ሀትሪክ:- አንተ ግን ከዝውውር ጋር ተያይዞ እጄ ጉቦ ተቀብሎ አያውቅም ለማለት ትደፍራለህ?
ዘላለም:- /ሳቅ/ ከምንፈልገው ተጨዋች ጋር በፍላጎታችን ዙርያ ከተስማማን በኋላ ክፍያው ላይ የሚደራደሩ ቢሮ የተቀመጡ ሰዎች አሉ.. እነሱ ናቸው በክፍያ ጋር በተያያዘ የሚወያዩት..እስካሁን ድረስ ከክፍያ ጋር ያናገርነው ተጨዋች የለም
ሀትሪክ:- አሰልጣኝ ካሳዬና ስራ እስኪያጁ አቶ ገዝኸኝ ወልዴ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ተጨዋቹን እንደሚያናግሩ መረጃው አለኝኮ?
ዘላለም:- አይ ያለኝ መረጃ ይሄ ነው የምንፈልገውን ተጨዋች ካሳዬ አግኝቶ ያወራዋል ክፍያ ላይ የተዋቀረ ኮሚቴ እንዳለና እንደሚያናግራቸው ነው የማውቀው.ካሳዬም ሆነ ዘላለምን አይመለከታቸውም
ሀትሪክ:- አንተ የለህም.. ካሳዬና አቶ ገዛኸኝ ግን ከክፍያ ጋር በተያያዘ ተጨዋቾቹን ያነጋግራሉ ይሄ መረጃ አለኝ እያልኩህ ነው?
ዘላለም:- አቶ ገዛኸኝ ስራ አስኪያጅ ስለሆነ ያገባዋል ካሳዬ ግን ያለበት አይመስለኝም
ሀትሪክ:- በ24 የሊጉ ጨዋታዎች መሃል በመሸነፋችሁም ሆነ በጨዋታ ተፈተናችሁ የተናደድከው በማን ነው?
ዘላለም:- በጨዋታ የተፈተንበት የምለው ከሃዋሳ ከተማ ጋር ባደረግነው የ2ኛ ዙር ጨዋታ ላይ ከዕረፍት በኋላ እኛ በምንፈልገው አጨዋወት የተሻሉ ሆነውብናል። በመሸነፋችን የተበሳጨሁበት በሀዋሳ ከተማ ደርሶ መልስ መሸነፋችን ነው
ሀትሪክ:- አሁን ላይ ቆመን ኢትዮዽያ ቡናን በ2014 ዋንጫ ያነሳል ብለን መገመት እንችላለን?
ዘላለም:- እኛ እንዘጋጃለን እሱን የሚገልጸው ግን ጨዋታው ይመስለኛል። ተግባብተን በመስራት ስህተት የምንቀንስበትና ጥሩ ውጤት ለማምጣት የምንችለውን እናደርጋለን ነገር ግን ያለውን ሁኔታ ጌሙ ነው የሚወስነው..በኛ በኩል የምንችለውን ያህል እንዘጋጃለን
ሀትሪክ:- ከስልጠናው ውጪ ትጥቅ መሽጫ ሱቅ 22 ጎላጎል ላይ ከፍተሃል.. እንዴት ነው ገበያው?
ዘላለም:- /ሳቅ/ ሱቁ የተከፈተው ማሰልጠን ከመጀመሬ በፊት ነው.. ማንኛውም ሰው ከፊልዱ ውጭ ሌላ ገቢ ያስፈልገኛል ብሎ ማሰቡ አይቀርም የኔም እንደዛ ነው የሆነው… ከስልጠናው ጋር ተያያዥነት አለው የስፖርት ትጥቅ መሆኑ ደግሞ አሪፍ ነው.. ስራዬም ሙያዬም ተያያዥነት ሲኖረው በራስ መተማመንን ያዳብራልና ደስ ብሎኝ ነው የምሰራው… በኔ እምነት አሰልጣኝነት ወደኸው የምትሰራው እንጂ የችግር መወጣጫ መሆን የለበትም ብዬ ስለማምን በዚህ መንገድ ተከስቻለሁ/ሳቅ/
ሀትሪክ:- ኢትዮዽያ ቡና አስተዳደር አግዞናል ማለት ትችላለህ?
ዘላለም:- አዎ… እንደዛ ነው ብዬ ነው የማስበው…እገዛው ለተጨዋቾቹ ተገቢ ክፍያ መስጠት ማበረታታት ነው ብዬ አስባለው.. ቡድኑ የሚፈልገውን በማድረግ ጥሩ ድጋፍ እያደረጉ ነው..ደመወዝና ኢንሴንቲቭ ቀርቶባቸው ተቋርጦባቸውም አያውቅም ይሄ የድጋፉ ማሳያ ነው ብዬ አስባለሁ.. ሌሎቹ ክለቦች ጋር የሚሰማው ወሬ ቡና ጋር የለም.ይሄ ደግሞ ትልቅ ድጋፍ ይመስለኛል
ሀትሪክ:- እንዴ የአስተዳደር ክፍሉ ጫና በርትቶብህ ተናደህ የኢትዮዽያ ቡና ሳይሆን የካሳዬ ምክትል ነኝ ማለትህን ሰምቻለሁ…እውነት ነው?
ዘላለም:- እውነት ነው ጫና ነበረው ከሌላው ይልቅ ሃላፊነቴን ከመወጣት አንጻር ካሳዬ ነው ያመነኝ… ጫናው ሲበዛ እንደዚህ አይነት ነገር ይከሰታል… አሁንም የቀጠረኝ ኢትዮዽያ ቡና ነው እያገለገልኩ ያለሁት ግን ካሳዬን ነው ምክንያቱም ያመነኝም ያመጣኝም ካሳዬ ነው….. በውጪ ሃገር ኳስ ጋርዲዮላ አርቴታን የጠራው ኳስ እንዳቆመ ነው ምክንያቱም ለዚህ እንቅስቃሴ የሚረዳኝ እሱ ነው ብሎ ነው ያመጣው..ያንን ለመግለጽ ነው ያንን የተጠቀምኩበት…..በርግጥ ለካሳዬ አራጌ ምክትል መሆኔ አያጠያይቅም.. ለአጨዋወቱ ይሆናል ስለሚባል…. የእግር ኳሱ ቤተሰብም እንደሚረዳው ተስፋ አደርጋለሁ… በኛ ሀገር ምክትልነት ቡድኑ ሊመርጥ ይችላል ምክትልህ ይሄ ነው ሲባል ዝም የሚልም አለ ትክክለኛው ግን የትም ቦታ ስትወዳደር ምክትልነት የዋናው አሰልጣኝ ፍላጎት ነው መሆን ያለበት ካሳዬ ያደረገው ግር ያሰኘውም ለዚህ ነው

ሀትሪክ:- ጥሬ ስጋ ይወዳል አሉኝ…..እውነት ነው?
ዘላለም:- አዎ…በጣም ነው የምወደው…በተለይ “መዝገበ ስጋ ቤት” ምርጫዬ ነው ከምግብነቱ ውጪ ደስ ብሎኝ ነው የምበላው..እዚያ ስበላ ነው ዘና የምለው..ሰው ከጋበዝኩም እዚያ ነው/ሳቅ/
ሀትሪክ:- ጨረስኩ…የመጨረሻ የምስጋና ቃል ካለህ…?
ዘላለም:- ለዚህ ያበቃኝ እግዚአብሄር የቅድሚያውን ምስጋና ይወስዳል.. ከዚያ በመቀጠል አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ፣ ማቲያስ ጸዳሉ/ጌድዮን/፣ ሳሙኤል ብዙነህ፣ አብደላ መሐመድ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉትን በሙሉ እንዲሁም የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች በአጠቃላይ አመስግናለሁ..
በርቲ ጥሩ ስራ ነው