መነሻ ገጽ ሀዲያ ሆሳዕና “ጠንካራ ነን፤ ስንከላከልም ስናጠቃም እንደ ቡድን ስለምንጫወት ዘንድሮ አንድ ነገርን ከእኛ ጠብቁ” አማኑኤል ጎበና /ሀዲያ ሆሳዕና/
ሀዲያ ሆሳዕናቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

“ጠንካራ ነን፤ ስንከላከልም ስናጠቃም እንደ ቡድን ስለምንጫወት ዘንድሮ አንድ ነገርን ከእኛ ጠብቁ” አማኑኤል ጎበና /ሀዲያ ሆሳዕና/

አጋራ
አጋራ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለአርባምንጭ ለወልዋሎ እና ለአዳማ ተጫውቶ ከማሳለፉ በፊት የቅ/ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ተጨዋች ነበር። በቤት ኪንጉ ደግሞ እስካሁን ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ውድድሩን እየመሩ ላሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመሀል ሜዳው ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየት ቡድኑን በመጥቀም ላይ ካሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል፤ የአርባምንጩ ተወላጅ አማኑኤል ጎበና። ይህ የውድድር ዓመት ለቡድናቸው መልካም የሚባል ውጤት የሚያመጡበትና እንደ ግል ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየትም ክለቡን እስከ መጨረሻው የውድድር ዘመን ላይ ለመጥቀም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መዘጋጀቱንም ተጨዋቹ ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
አማኑኤል ጎበና ከሀትሪክ ስፖርት ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ የነበረው አጠቃላይ ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል። ተከታተሉት።

ስለ ጥምቀት በዓል

“ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዬች እንኳን ለጌታችን መድኋኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ከእነ ቤተሰባችሁ በሰላም አደረሳችሁ። በዓሉም የሰላም እና የፍቅርም ይሁንላችሁ”።
ስለ ሀዲያ ሆሳዕና ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ጅማሬዎች
“ዘንድሮ ደስ በሚል እና ጥሩ በሆነ መልኩ ነው የሊጉን ውድድር የጀመርነው። እስካሁን ካደረግናቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥም አራቱን በማሸነፍ እና በአንዱ አቻ በመለያየት ባለመሸነፍ ሪከርድ ሊጉን በመምራት ላይም ስለሆንን ይሄን ወደፊት በሚኖሩን ጨዋታዎች ላይም ልናስቀጥለው ዝግጁ ነን”።

ስለ ቡድናቸው ጠንካራ ጎን

“የእኛ ጥንካሬ እንደ ቡድን መጫወታችን ነው። በህብረት እናጠቃለን በህብረት እንከላከላለን፤ በየጨዋታው ያለን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ተነሳሽነታችንና የመጫወት ፍላጎታችንም ከፍተኛ ነው። ጥሩም ቡድን አለን። ከዛ ውጪ ልምድ ያላቸውን ጥሩ ተጨዋቾችንም ስላሰባሰብን ውድድራችንን በጥሩ ሁኔታ እያስኬድን ነው”።

ክፍተት ጎናቸው ምን እንደሆነ

“የእግር ኳስን ስትጫወት አይደለም በእኛ ሀገር የሊግ ደረጃ በውጪዎቹም ጭምር ነው አንድ ቡድን ግጥሚያዎችን ሲያደርግ አሸነፈም ተሸነፈም ክፍተቶች እንዳሉበት የሚታወቀውና እኛም ጋር ይሄን ችግር ምንም እንኳን በጎላ መልኩ ባናየውም ስናጠቃም ሆነ ስንከላከል ግን ያሉብንን ችግሮች እየቀረፍን ለመሄድ ዝግጁ ነን”።

በቤት ኪንጉ ፈታኝ ስለነበረባቸው ጨዋታ

“ከአምስቱ ጨዋታዎቻችን መካከል ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረግነው ነበር ለእኛ ፈታኝና ጠንካራ የነበረብን። ይሄን ጨዋታ ለማሸነፍም የመጨረሻው ደቂቃ ክፍለ ጊዜ ሁሉ አስፈልጎናልም”።

የሀዲያ ሆሳዕና የእዚህ ዓመት እልሙ እና የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማን እንደሚያነሳ

“ቡድናችን በአሁን ሰዓት ላይ የያዘውን ያለመሸነፍ ሪከርድ ለማስቀጠል ጠንክሮ እየሰራ ነው። ለዋንጫው ተፎካካሪነት በመጫወት ላይም ነው የሚገኘው። ሁሉም ቡድኖችም ጠንካራ ሆነው የቀረቡበት ዓመት ስለሆነም የእዚህ ዓመትን የሊግ ዋንጫ ሁሉም ቡድን የማንሳት ዕድል ስላለው ይህን ማሳካት የሚችለው ግን እስከ ውድድሩ ዓመት መጨረሻ ላይ ጠንካራ ሆኖ የሚጓዘው እና ጥሩ አቅም ያለው ቡድን ነው”።


በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ስለሚገኝ የተለየ ተጨዋች

“በቁጥር ደረጃ አንድ እና ሁለት ሳይሆኑ ብዙ ተጨዋቾች በውድድር ዓመቱ ጅማሬ ጥሩ ጊዜን እያሳለፉ እንዳሉ ተመልክቻለሁ፤ ይሄ ሊቀጥል ከቻለም ለእግር ኳሳችን ለውጥ መልካም ነገር ነው የሚሆነው”።

ለሀዲያ ሆሳዕና እያበረከተ ስላለው አስተዋፅኦ

“እስካሁን በተሰለፍኩባቸው ጨዋታዎች የሚጠበቅብኝን ጥቅም ባለኝ አቅም ለቡድኔ እየሰጠው ነው። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይም የእኔ ዋንኛ እልሜና ግቤም ከእዚሁ ቡድን ጋር እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ዋንጫ እስከማንሳት በሚዘልቅ ደረጃ ምርጥ የውጤት እና የስኬት ጊዜን ማሳለፍም ጭምር ነውና በቀጣዩ ጨዋታዎችም ጠንክሬ ነው ለውድድሮቹ የምቀርበው”።
ከፋሲል ከነማ ጋር ስለሚያደርጉት ጨዋታ እና ስላደረጉት ዝግጅት
“በጅማ ዩንቨርስቲ ከፋሲል ከነማ ጋር ላለብን ጨዋታ ቡድናችን ሲዘጋጅ የነበረው ለሌሎች ቡድኖች እንደሚዘጋጀው ነው። ይሄን ጨዋታ በተመለከተም እነሱ ካላቸው ጥንካሬ እና ከያዙት ጥሩ ቡድን አንፃርም እኛም በጥሩ አቋም ላይ ስለምንገኝ በቁርጠኝነት ልንፋለማቸው እና ልናሸንፋቸው ዝግጁ ነን”።

ሀዲያ ሆሳዕናን አጠር ባለ መልኩ ግለፅ ብትባል

“ይሄ ቡድን ዓምና የሊጉ ውድድር በኮቪድ የተነሳ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ላለመውረድ የተጫወተ ነበር። ዓምና የነበረውም አምና አልፏል። ዘንድሮ ደግሞ የከዚህ በፊቱ የቡድኑ ችግር እንዳይደገም እና መልሶም እንዳይፈጠር በተጨዋቾች ደረጃም ሆነ በአሰልጣኝ ቀጠራ ላይ በአመራሮቹ በኩል ጥሩ ስራ ስለተሰራ እና እንደ አዲስ የተዋቀረ ጥሩ ቡድንንም ክለቡ ይዞ ስለመጣ በውድድር ዓመቱ ላይ ጠንካራ የውድድሩ ተሳታፊ በመሆን መልካም የሚባል ውጤትን ለማምጣት የተዘጋጀ ቡድን መሆኑን ነው ለመናገር የምፈልገው”።

 

ባሳለፋቸው የእግር ኳስ ህይወቱ ደስተኛ ስለ መሆኑና ስለ መከፋቱ?

“በአብዛኛው የኳስ ህይወቴ በየተጫወትኩባቸው ክለቦች ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴን አሳይ ስለነበር ደስተኛ ሆኜ ነው ያሳለፍኩት። ለእዛም ፈጣሪዬ ብዙ ነገሮችን ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። በእግር ኳሱ ተከፍቻለው ብዬ የማስበው ደግሞ አንድ ጊዜ ነው። ይሄም የአርባምንጭ ከተማ ቡድን ከፕሪምየር ሊጉ በወረደ ሰዓት። ይሄ ቡድን ለእኔ ጥሩ እውቅናን ያስገኘልኝ ነበር። ከሊጉ መውረዱ አስከፍቶኛል።

ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነት ሲመጣ አድንቆ ስላደገው እና ተምሳሌት ስላደረገው ተጨዋች

“ደጉ ደበበ ነዋ! እሱ የእኛ ክልል ተወላጅ ስለነበርና በችሎታውም በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ጥሩ ሲጫወት ስለተመለከትኩት አድንቄው ነው ያደግኩት እና እሱ ነው ተምሳሌቴ”።

የእግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮ

“ከኳስ ተጨዋችነት ውጪ ሌላ ምን ልሆን እችል ነበር? ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ ነው መጫወት የጀመርኩት። በ2003 አካባቢም ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ውስጥ መጥቼ ለሶስት ዓመታት ያህል ቆየሁኝ። ከ2006 ዓ/ም ጀምሮ ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ በወልዋሎ እና በአዳማ ከተማ ቡድኖች ውስጥ ተጫውቼ በማሳለፍ የመጣሁ ተጨዋች ስለሆንኩኝ ከበፊት አንስቶ በሌላ ሙያ ውስጥ ስለመሰማራትም አስቤ አላውቅም እና ስለ እግር ኳስ እና እግር ኳስ ተጨዋች ስለመሆን ብቻም ነበር አስብ የነበርኩት”

ቤት ኪንጉ በዲ ኤስ ቲቪ ስለመተላለፉ

“የጨዋታዎቹ መተላለፍ ካለፉት የውድድር ጊዜያቶች እና ዘመናቶች አንፃር ዓለም እየተመለከተንም ስለሆነ ለእኛ ተጨዋቾች ጥሩ ነገሮችን ይዞልን መጥቷል እና እነዚህን እድሎች ራሳችንን ለመሸጥ እንድንችል ልንጠቀምባቸው ይገባል።

ስናጠቃልል

“ሀዲያ ሆሳዕናን አስመልክቶ ብዙ ብያለሁ። ራሴን በተመለከተ በኳሱ ከእዚህ በላይ ደረጃ መገኘትን እፈልጋለሁ። ለዛ ደግሞ ጠንክሬ እሰራለሁ። ይህን ካልኩ ለእስካሁኑ የኳስ ህይወቴ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የረዳኝን ፈጣሪዬን በመጀመሪያ ከዛ በመቀጠል ደግሞ በብዙ ነገሮች ሲረዱኝ የነበሩትን ቤተሰቦቼንና በኳስ ህይወቴ በማሰልጠን ረገድ በችሎታዬ ላይ ለውጦችን እንዳመጣ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች አመሰግናችኋለሁ”።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...