በይስሐቅ በላይ
🗝የፋሲሉ ባህርዳር ከተማ ቡድን ወጥነት የለውም ብለው አስተያየት የሚሰጡት በራሳቸው ዱካ ውስጥ ሆነው ቢሆንም አሴተያየቱን አከብራለሁ
🗝ለእኔ የውድድሩ ምርጡ ተጫዋች አቡበከር ናስር ነው
🗝ሀትሪክ የተሠራበትን ኳስ መከልከል ታሪክን የመንጠቅ ያህል ነው
ብዙውን ጊዜ በሙሉ የሱፍ ልብስ ሽክ ብሎ ጨዋታ ሲመራ አይታይም፤ ሸሚዝ በጂንስ አሊያም ቱታና ስኔከር ተጫምቶ ቡዱኑን ሲመራ የሚታየው የጣና ሞገዶቹ ወጣቱ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ዘንድሮ ግን አዲስ ሙሽራ መስሎ ከወትሮ ለየት ባለ መልኩ በሙሉ ሱፍ ብቅ ብሏል።ምንአልባት ፋሲል የአለባበስ ስታይሉን የቀየረው ጨዋታው በDSTV መተላለፉን ተከትሎ ሽክ ብሎ ለመታየት ነው የሚል ሃሳብ በብዙዎች አእምሮ ብቅ ማለቱ የመጠየቅ ጉጉቴን አናረውና የእጅ ስልኬን በማንሳትና በቀጥታ በመደወል ፋሲል ያለ ወትሮህ ሱፍ ልብስ አበዛህ በሠላም ነው?ወይስ የተለየ ምክንያት አለህ? የሚል ጥያቄ በስልኬ ሞገድ ወርውሬለት ግርምት ያለው ምላሹን በሳቅ አጅቦ ሰጥቶኛል።ይሄ ብቻ አይደለም ከፋሲል ተካልኝ ጋር በነበረን ቆይታ ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ስለመውጣታቸውና ስለዲሲፒሊን ችግር፣የቡዱኑ አቋም ይዋዥቃል አንዴ ያሽንፋል በቀጣይ ደግሞ ይሸነፋል በሚል ከኃላው ስለሚደርስበት ሀሜትና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር አውርተዋል፤ቆይታችሁን አውሱን።
ሀትሪክ:-ከዚህ በፊት በሙሉ ሱፍ ጨዋታ ስትመራ አትታይም በሠላም ነው?
ፋሲል:-(በጣም ሳቅ) አንተም እንደታዘብከው ብዙ ጊዜ ወደ ሜዳ የምመጣው በቲሽርት አሊያም ቱታ ለብሼ ነው በሙሉ ሱፍ መጥቼ አላውቅም፤ሳምንቱን ሙሉ በቱታና በስኔከር ስለማሳልፍ የጨዋታ ቀን ለምን የአለባበስ ስታይሌን አልቀይረውም አልኩና ሱፍ መልበስ ጀመርኩ(ሳቅ)ምክንያቱም ለላይፍም ሁሌም አንድ አይነት የአለባበስ ስታይል መከተል አንድ አይነት ስሜትን ብቻ ነው የሚሰጠው ሊያሰለችም ይችላል፤ሌላው አለባበስ የራስ የመተማመን ስሜትህን፣ በሰዎች ዘንድ ያለህ አቀባበል ይጨምራል፣ጥሩ መንፈስ እንዲኖርህም ያደርጋል፤እኔም ከላይ ባልኩህና በጥሩ መንፈስ ወደ ሜዳ መምጣትን ስለፈለኩ ስታይሌን ቀይሬአለሁ(በጣም ሳቅ)።
ሀትሪክ:-ብዙዎች ፋሲል ስታይሉን የቀየረው ጨዋታው በdstv ስለሚታይ ሽክ ብሎ ለመታየት ነው ብለው ሲያሙህ ሰምቻለሁ?
ፋሲል:-(በጣም ሳቅ) ዕውነት ለመናገር በdstv ስለሚታይ ብዬ አይደለም ዋናው ምክንያቴ ከላይ እንዳልኩህ ነው፤ለdstv ብዬም ቢሆን ልክ ነኝ ምክንያቱም ውድድሩ በሀገራችንና በመላው አለም የሚታይ በመሆኑ የሚመለከቱንን ማክበርና ፕሮቶኮሌን ጠብቄ ፀዳ ብዬ ፊታቸው መቅረብ አለብኝ(አሁንም ሳቅ)።በሱፍ ስመጣ ይሄ የመጀመሪያዬ አይደለም በdstv ስላልተላለፈ ወይም ትኩረት አልተሰጠውም እንጂ ከአዳማ ጋር ስንጫወትም በሱፍ ነበር የመጣሁት።

ሀትሪክ:-ከዚህ በሃላም በሱፍ ብቻ ነው የምናይህ ማለት ነው?
ፋሲል:-ለጊዜው ተመችቶኛል፤ሠውም ወዶልኛል ግን ሠውን በሱፍ ብቻ እንዳላሰለቸው አልፎ አልፎ በሸሚዝ ወይም በቱታ ብቅ ልል እችላለሁ።
ሀትሪክ:-በሊጉ ከ24 ጨዋታ በላይ ነው የምታደርገው አውቀሃል?ከዚህ አንፃር ቁም ሳጥንህ ውስጥ ምን ያህል ሱፍ አለህ?
ፋሲል:-(ያላባራ ሳቅ)ምነው ልትገዛልኝ አስበህ ነው?ብለህ ብለህ ልብስ ቆጠራ ውስጥ ገባህ?(አሁንም ሳቅ)…
ሀትሪክ:- …በክፋት ሳይሆን ከጨዋታው ብዛት አንፃር እንዳትቸገር አስቤልህ ነው…ምነው አጠፋሁ እንዴ?…
ፋሲል:- …(የግርምት ሳቅ እየሳቀ)…ብዙም አትቸገር የሞላኝ የተትረፈረፈኝ ነኝ ባልልህም ያለኝ ይበቃኛል…
ሀትሪክ:-አ.አ ላይ በተካሄደው የሊጉ ጨዋታ በ10 ነጥብ 4ተኛ ሆነህ ነው ያጠናከከው፤ስኬታማ ነኝ ትላለህ?

ፋሲል:-አሁን ስለስኬት የምታወራበት አይደለም፤የውድድሩ 70 እና 80 ፐርሰንት እየቀረ ስለስኬት ማውራት ጤነኛነትም አይሆንም፤ራሴን የምለካው የመጨረሻ ባልሆነውና በሚዋዥቀው ደረጃ አይደለም፤በሠራነውና ተጫዋቾቼ ሜዳ ላይ እየመለሱት ባለው ነገር ነው፤በሶስት ነጥብ ተበልጦ 4ተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥና ለመሪነት መቅረብ በጣም መልካም ነገር ቢሆንም ስለ ስኬት ለማውራት ገና ጠዋት ነው ባይነኝ።በአጠቃላይ ግን እንደ ትልቅ ስኬት ሳይሆን ጥሩ ቦታ ላይ ያለን ግን የምንፈልገው ስኬት ጋር ለመድረስ ብዙ እንደሚቀረን ነው ለእኔ የሚሠማኝ
ሀትሪክ:-በተለይ ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ጎል ካገባችሁ በሃላ ተጫዋቾቹ ወደ አንተጋ ሮጠው መጥተው አቅፈውህ ደስታቸውን ሲገልፁ ነበር፤ለምን አቀፉህ በዚህ መልኩ ደስታቸውን ለምን ገለፁ ብልህ ትመልስልኛለህ?
ፋሲል:-…ሆ…(በጣም ሳቅ)…ሌላ ነገር ይመስልብሃል…ደግሞም ይሄን ጥያቄ ለእኔ ሳይሆን ላቀፉኝ ተጫዋቾች አቅርብና እነሱ ምክንያታቸውን ይንገሩህ፤የግል ግምትህን ካልከኝ ግን ጎል ስላገቡ ደስ ስላላቸው ብቻ ነው ልልህ የምችለው፤ከዚህ ውጪ ተጫዋቾች የራሳቸው ስራ አላቸው እኔም እንደ አሰልጣኝ የራሴ ስራ አለኝ፤ቀጋራ የሚያገናኘን ነገር ደግሞ አለ…የቡዱኑን ውጤት ማሻሻል፣እንዲያሸንፉ መርዳት፣ደጋፊው የሚደሰትበት ታሪክ መስራት በጋራ የሚያቆመን ነው፤ከዚህ ስሜቶችም በመነሳት ሊሆን ይችላል።
ሀትሪክ:-ምን አልባት ከፋሲል ከነማ ጋር ለነበረው የደርቢ ጨዋታ የተለየ ጉጉት ስለነበረህ ይሆን?
ፋሲል:-በፍፁም…!…የሚገርምህ ነገር ለፋሰሐል ጨዋታ ብለን በተለይ የተነጋገርነው ወይም ያደረግነው ዝግጅት የለም፤ሁልግዜም ስህተታቸውን እንዲያርሙ ጥንካሬያቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ እመክር ነበር ያኔም ያደረኩት ይሄንን ነው እንጂ ለፋሲል ብዬ ያደረኩት የተለየ ነገር የለም፤ለሁሉም ቡድን የምናደርገውን ነው ያደረኩት እንጂ ከፋሲል ጋር ነው የምንጫወተው ብዬ ከመደበኛው በተለየ ተጨማሪ ትሬይኒንግ አላሰራሁም።
ሀትሪክ:-የፋሲልን ጨዋታ ካነሳን ካልቀረ በአንድ ጨዋታ ሁለት ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጥብሃል፤ይሄ የቡድንህን የዲሲፒሊን ችግር አያሳይም?ፋሲል ኳስ ላይ እንጂ ዲሲፒሊን ላይ አልሰራም ብሎስ አያስወቅስህም?
ፋሲል:-የማይገናኝ ነገር ነው የምታገናኘው፤በነገራችን ላይ ሰለ እሱ ጨዋታና ቀይ ካርድ ካነሳን መናገር የማልፈልገውን ብዙ ነገር ልንነጋገር እንችላለን፤በተለይ የመጀመሪያው የወሰኑ ቀይ ካርድ በፍፁም አያሰጥም፤ስሜታዊ እንዳልሆን በሚል ፊልሙን ደጋግሜ አይቼዋለሁ በፍፁም አያሰጥም፤በዚህ ስህተት ቡድናችን ተጎድቷል፤የጨዋታ ዕቅዳችን እንዲበላሽና ተጫዋቾቼ ስሜታዊ እንዲሆኑ አድርጎብኛል፤የምንይሉ ላይ ጥያቄ የለኝም ያሰጠዋል፤እደግመዋለሁ የመጀመሪያው ቀይ ካርድ ግን በፍፁም አልተዋጠልኝም፤በዚህ መልኩ የታየን ቀይ ካርድ መነሻ በማድረግ ቡድኑ በዲሲፒሊን ችግር የታመሰ ያህል አድርጎ መቁጠር አግባብ ነው አልልም፤እግር ኳስ በስሜታዊነት የተሞላ ነው፤በአለም ዋንጫ ፍፃሜ ላይ የእግር ኳስ ንጉሶች የምንላቸው እንኳን ሲሳቱ እያየን ነው፤በአሰልጣኝነቴ ከማምንባቸውና ቅድሚያ ከምሰጥባቸው ጉዳዮች አንዱ ዲሲፒሊን ነው፤የሜዳ ላይ፣የካምፕ፣የሜዳ ውጪ የላይፍ ዲሲፒሊንን በተመለከተ ከተጫዋቾቼ ጋር ስለምመካከር በዚህ ደረጃ ለወሸሳ ያበቃናል ብዬ አላስብም።
ሀትሪክ:-አሁን ከፋሲል ከነማ ጋር ከነበረው ጨዋታ አልወጣም፤ከጨዋታው ደርቢነት ውጪ አንተን ቅ.ጊዮርጊስ B እና ዋናው ቡድን እያለህ ያሰለጠነህ፣ሁለታችሁም የቅ.ጊዮርጊስን ማልያ ለብሳችሁ በመጫወታችሁ የአንተና የስዩም ከበደ ፍልሚያ የተለየ ስሜት አልፈጠረብህም?
ፋሲል:-ምንም የተለየ ስሜት አልፈጠረብኝም፤ከስዩም ጋር ስንገናኝ የመጀመሪያችን ሳይሆን ሁለተኛችን ነው፤ያልከው ሁሉ ዕውነት ነው በጊዮርጊስ Bም በዋናው ቡድንም አሰልጥኖኛል ሁለታችንም የጊዮርጊስን ማልያ ለብሰን ተጫውተን አሳልፈናል ባህርዳርና ፋሲል ጎረቤታሞች ናቸው ቢሆንም ግን የተለየ አይነት ስሜት እንደተሰማኝ አላስታውስም፤ሁሌም ቡድኔን ለመምራት እንደምመጣው ነው የዚያም ቀን የመጣሁት።

ጥያቄ:-ቡድንህ ወጥ መገለጫ የለውም አንዴ ያሸንፋል ጥሩ ነው ሲባል ደግሞ ይሸነፋል ብለው በሚያሙህ ሰዎች ትበሳጫለህ?
ፋሲል:-ምን ያበሳጨኛል?በነገራችን ላይ እኔ የኮሜንት አፍቃሪ ስለሆንኩ እንደዚህ አይነት አስተያየት አያበሳጨኝም፤ሰዎች በራሳቸው ዱካ ውስጥ ቆመው የሚሰጡት አስተያየት ነው፤ይሄንን ጠንቅቄ ስለማውቅ ሠው የሚሰጠውን አስተያየት መራራም ይሁን ጣፋጭ አከብራለሁ፤የማደርገው ምንድነው ከአስተያየቱ ውስጥ የሚጠቅመኝን መውሰድና የማይጠቅመኝን መጣል ብቻ ነው፤ቡድኑ ወጥነት የለውም የሚለው ከማን ጋር ተነፃፅረን ነው ለሚለው የሁሉንም ቡድኖች ውጤትና አቋም መፈተሽ ነው፤ማን በተከታታይ ወጥነት ባለው መልኩ አሸንፏል?ማንስ ከዚህ በተቃራኒ ነበር?የሚለው ከተፈተሸ መልሱ አስተያየት ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፤ይሄን ስልህ ግን ከችግሮች የፀዳን ነን ማለቴ አይደለም።
ጥያቄ:-ግብጠባቂህ ሀሪሰን ሄሱ በተደጋጋሚ ስህተት እየፈፀመ ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍል ታይቷል በተለይ ከፋሲል ጋር ፤ከዚህ በመነሳት በተጠያቂነት ትወነጅለዋለህ?
ፋሲል:-ጎል በገባ ቁጥር ተጫዋችን ተጠያቂ አላደርግም፤እንደ አሰልጣኝ መሻሻል ያለበትን ከስህተት መማር ያለባቸውን አስተምራለሁ፤ለቡድኑ መስጠት ያለበትን መስጠት ያልቻለ ካለ በአሰልጣኝና በተጫዋች ስሜት ውስጥ ሆነን እንነጋገራለን፤ከዚህ ውጪ ተጫዋችን በተናጠል ተጠያቂ አላደርግም፤የትኛውም ተጫዋች ስህተት ሰርቶ ሽንፈት ቢመጣ የተሸነፍነው እንደ ቡድን ነው ስለዚህ እንደ አሰልጣኝ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ፤ሽንፈት ሲመጣ በተጫዋች የማሳስብና የማላክክ አይነት አሰልጣኝ ነኝ ብዬም አላስብም።

ሀትሪክ:-አ.አ ላይ ከተደረገው ጨዋታ አንፃር ከቡድንህ የተለየ የምትለው ተጫዋች?
ፋሲል:-እንዲህ ለማለት ገና ነኝ፤ምክንያቱም ያደረግነው ከአምስት የማይበልጥ ጨዋታ ነው፤ምክንያቱም ከተጫዋቾቼ ከዚህ በላይ ስለሚጠብቅና እንደሚሰጡኝ ስለማውቅ።
ሀትሪክ:-ከአጠቃላይ ከውድድሩ የተለየ ጎልቶ የታየ የምትለው ተጫዋችስ?
ፋሲል:-ምንም ጥያቄ የለውም አቡበከር ናስር ነዋ…!…ከዚህ በፊትም ነግሬሀለሁ አቡበከር ናስር በጣም ትልቅ ተጫዋች ነው…በጣምም ነው የማደንቀው በጣምም ነው የምወደው…በውድድሩ በማስበው ልክ ለየት ብሎ ያገኘሁት እሱን ነው።
ሀትሪክ:-ሰለአቡበከር ካነሳህ በደርቢ ጨዋታ ሶስት ጎል አስቆጥሮ ሀትሪክ የሰራበትን ኳስ ለማስታወሻነት አትወስድም መባሉ መነጋገሪያ ሆኗል፤በዚህ ላይ የአንተ ስሜት ምንድነው የሚለው የመጨረሻ ጥያቄዬ ብናደርገውስ?
ፋሲል:-ይሄ በፍጥነት መታረም ያለበት ነው፤በዚህች ትንሸ ነገር ትልቁን ታሪካቸውንም መንጠቅም ነው፤ሀትሪክ የሰሩበት ኳስ ለእነዚህ ተጫዋቾች ታሪካቸው ነው፤ወደፊት ለቤተሰቦቻቸው፣ለልጆቻቸው ታሪካቸውን ለማስተላለፍ እንደዚህ አይነት ታሪክ የተሰራባቸው ኳሶች ሊኖሯቸው ይገባል፤ሊጋችን በdstv መተላለፍ ጀምራል ከፍ ብሏል እንደዚህ አይነት ነገሮች ግን ያሳንሱታል፤ሀትሪክ የተሠራበትን አንድ ኳስ ለተጫዋቾች መስጠት ጉዳት ያመጣል የፌዴሬሽኑንም ካዝና ያናጋል ብዬ አላስብም፤በዚህ ደረጃ የፌዴሬሽኑም ሆነ የሊግ ካምፓኒው ስምም መነሳት አለቀት ብዬም አላስብም፤እንደዚህ አይነት ነገር በእንግሊዝ፣በስፔን፣በጣሊያንና በጀርመን ሊጎች ያለና የተለመደ ነው፤እንግዲህ ሞዴሎቻችን እነሱ አይደሉ ይሄንንም ከእነሱ መኮረጅ እንዴት ያቅተናል?እኔ ሀትሪክ የተሠራበት ኳስ መከልከል የለበትም ከሚሉት ጎራ ነኝ።
አስተያየት ይስጡ