የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረጉ 36 ግጥሚያዎች ላይ የታዩ አንኳር አንኳር ጉዳዮች!

በአዲስ አበባ ስታዲየም 36 ግጥሚያዎች፡-

የፌዴሬሽኑን ደንብ የጣሰው ኮሚሽነር
– ተሳዳቢዎቹ ደጋፊዎች
– የአርቢትሮቹ ደካማ አቋም
– የወልቂጤዎቹ ሮሮ
– የግብ ቀበኞቹ

መግቢያ

በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የመጀመሪያው 6 ሣምንት 36 ግጥሚያዎች ተጠናቆ ጥር 8/2013 በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ለሚደረገው ጨዋታ ቦታውን አስረክቧል፡፡ ከጅማ በኋላ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ድሬደዋ ከተማና ሀዋሳ ከተማ የቀሪ የሊጉ መርሀ ግብር የሚካሄድቸው አስተናጋጅ ከተሞች ናቸው የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ 36 ግጥሚያዎች ላይ ተከስተዋል ያላቸውን አንኳር ጉዳዮች እንዲህ ዳሷቸዋል፡፡

የመጨረሻው ጨዋታ ባለታሪክ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማናጅመንት ቦታ ላይ ያሉ አመራሮች በ2013 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ የጨዋታ ኮሚሽነር መሆን እንደማይችሉ ውሣኔ አስተላልፎ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል /ሀትሪክ ይህን ዜና መስራቷል ይታወቃል/ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ የኮሚሽነር ዝርዝሮችን ለሊግ ካምፓኒው የውድድርና ስነ-ሥርዓት ኮሚቴ አስረክቦ ሊስቱ ውስጥ ባሉ ባለ ሙያዎች ውድድሮች ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ምክትል ዋና ፀሐፊና የቴክኒክ ልማት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ ግን ሕጉን ወደ ጎን በማለት ወልቂጤ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና ያደረጉት ጨዋታ ላይ በኮሚሽነርነት መስራታቸው በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታን ፈጥሯል፤ የውድድርና ስነ-ሥርዓት ኮሚቴ በበኩሉ ለሀትሪክ በሰጠው ምላሽ ግን 30 ኮሚሽነሮች ከፌዴሬሽኑ ደርሶናል ሰባቱ ያለሟሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የነበረው አቶ ሰለሞን ቀሪ የህክምና ማስረጃቸውን በማቅረባቸው ልንጠቀምባቸው ችለናል ከዚያ ውጪ አቶ ሰለሞን ስለመከልከላቸው የደረሰን ምንም አይነት ደብደቤ የለም ሲል ተናግሯል፡፡ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ በበኩላቸው “የተባለውን ነገር አልሰማሁም ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ውድድርን በበላይነት የሚመሩ ኃላፊዎች በኮሚሽነርነት መስራት አይችሉም መባሉን ሰምቻለሁ ሊግ ካምፓኒ ውስጥ ምንም አይነት ኃላፊነት ስለሌለኝ ክልከላው አይመለከተኝም በሙያዬ የማገልገል መብቴም የተጠበቀ ነው ኮሚሽነር በመሆኔ የሚፈጠር ችግር አለ ብዬም አላምንም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሀትሪክ ከታማኝ የፌዴሬሽን ምንጯ ባገኘችው መረጃ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኋላ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

ተሳዳቢዎቹ ደጋፊዎች

ውድድሩ በዝግ ነው ወይስ ለተመልካች ክፍት ተደርጎ የተካሄደው ቢባሉ በዝግ ነው ማለትዎ አይቀርም የኮቪድ 19 ፕሮቶክልን በጣሰ መልኩ የተካሄዱ ግጥሚያዎች መኖራቸው በራሱ አነጋጋሪ ቢሆንም ውድድሩ በዝግ ተካሄዷል መባሉ እርግጥ ነው፡፡ አስር አስር ደጋፊዎች ይግቡ ተብሎ አንዱ ጋር በእጥፍ ሌላው ጋር ከአስርም በታች ደጋፊ ስታዲየም ገብቶ ሲመለከት የታየበት አጋጣሚ ብዙ ነበር፡፡ የአንዳንድ ክለቦች ደጋፊዎች ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም የሚናገሩት አስፀያፊ የሆነ ስድብ ለስታዲየሙ እፍረት ሆኖ የሰነበተበት ግጥሚያም ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሰበታ ከተማ ከጅማ አባጅፋር ጋር 1ለ1 ሲለያይ የሰበታ ደጋፊዎች ሙሉ 90 ደቂቃ አሰልጣኙን አብርሃም መብራቱንና ተጨዋቾቹን በስም እየጠሩ ሲዘልፉ የታዩበት የፀጥታ ኃይሎች ዝምታም ትኩረት የሳበበት አይነት ግጥሚያ አልታየም ቡድናቸውን ሊያበረታቱ ነው ተብሎ ተመርጠው የገቡት ደጋፊዎች የክለባቸውን ሞራል ረግጠው ለተጋጣሚ ክለብ ኃይል በመሆን የሰበታ ደጋፊዎችን የተለየ ያደርጋቸዋል፡፡ በቀጣይ በጅማ ከተማ የሚካሄደው ጨዋታ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይከሰትበት አዘጋጁ አካል፣ ክለቦችና የፀጥታው ኃይል ሊያስቡበት ይገባል፡፡

ግቦቹ

በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ፕሮግራም የወጣለት የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም 36 ጨዋታዎች ተካሄዶበት ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ተጠናቋል፡፡ በ6ቱ ሣምንት ግጥሚያዎች 36 ጨዋታዎች ተደርገው 107 ግቦች ከመረብ አርፈዋል፡፡ ከ6ቱ ሳምንት መሀል በ1ኛ እና 2ኛ እና በ4ኛ ሳምንት በነፍስ ወከፍ አስራ አምስት ግቦች ተቆጥረዋል፡፡ በ6ኛው ሣምንት 17፣ በ5ኛ ሳምንት 19፣ በ3ኛ ሳምንት 24 ግቦች ተቆጥረዋል፡፡ በ6ቱ ሳምንት ከተቆጠሩ ግቦች 0ለ0 3 ጊዜ፣ 1ለ0 6 ጊዜ፣ 2ለ2 2 ጊዜ፣ 4ለ1 5 ጊዜ፣ 2ለ1 3 ጊዜ፣ 3ለ1 6 ጊዜ፣ 3ለ2 3 ጊዜ፣ 2ለ0 3 ጊዜ፣ 4ለ2 1 ጊዜ፣ 1ለ1 3 ጊዜ የሆነ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

ግብ አስቆጣሪዎቹ

በ6ቱ ሳምንት ለተቆጠሩ 113 ግቦች መሀል በኮከብ ግብ አግቢነት እየተፎካከሩ ያሉት የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርና የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም እኩል ስምንት ስምንት ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል ሀብታሙ ታደሰ ከኢትዮጵያ ቡና ጌታነህ ከበደ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል አራት አራት ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ 6 ተጨዋቾች በየግላቸው ሶስት ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሌሎች 6 ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ ሁለት ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ 16ቱ ተጨዋቾች በጋራ 54 ግብ ሲያስቆጥሩ 59 ተጨዋቾች በየግላቸው አንድ አንድ ግቦችን ተጋጣሚ መረብ ላይ አሳርፈዋል፡፡

ዳኞቹና ያልተመለሰው ጥያቄ

የዳኞቹ ተቃውሞና ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኝ የአዲስ አበባ ስታዲየም ቆይታ ተጠናቋል፡፡ የሙያ አባልና የወሎ አባል የሚከፈላቸው ዳኞቹ በጁፒተር ሆቴል አንዲሰባሰቡ ከተደረገ በኋላ የውሎ አባላቸው ቀርቶ ሲያጫውቱ ብቻ 3ሺ ብር እንዲከፈላቸው መደረጉ ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል፤ ወጥተን ሣንሰራ በሆቴል ተቀምጠን የውሎ አበል መከላከላችን ተገቢ አይደለም የሚሉት ዳኞቹ በወር ውስጥ የሚያገኙት ምደባና የሚከፈላቸው ክፍያ ማነሱ ሁኔታውን ከባድ እንዳደረገቸውና ውሣኔው ብዙ ነገሮችን ከግመት ያላስገባ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ የመሀል ዳኞችና ረዳት ዳኞች በጁፒተር ሆቴል ተቀምጠው በጨዋታ ብቻ እንዲከፈላቸው መደረጉ ሊግ ካምፓኒው ላይ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ ሊግ ካምፓኒው ግን ለሀትሪክ እንደገለፀው የሚጨመር ብር ካለ ጉዳዩ የክለቦቹ ነው፡፡ ክለቦቹ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቦላቸው ጭማሪውን ካላፀደቁ የሊግ ካምፓኒው የውድድርና ስነ ሥርዓት ኮሚቴ ምን ማድረግ አይችልም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም 36 ጨዋታዎችን የዳኙ ዳኞች ቆይታ ያበቃ ሲሆን ጥር 8 በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚቀጥለው 7ተኛ ሳምንት ጨዋታን ጨምሮ እስከ አስራ አንደኛው ሳምንት ድረስ ያሉት ግጥሚያዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ሊጠይቁ በሚችሉ ሌሎች አርቢትሮች የሚዳኝ ይሆናል፡፡

በርካታ ጨዋታ ያጫወቱት ዳኞች

በጁፒተር ሆቴል 26 ዳኞች ተሰባስበው 36ቱን ጨዋታዎች የመሩ ሲሆን በሊጉ የመጀመሪያዎቹ 36 ጨዋታዎች 13 የመሀል ዳኞች ግጥሚያዎችን መርተዋል፡፡ ከእነዚህም መሀል ኢተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማና ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሠ አራት አራት ጊዜ በመሀል ዳኝነት መርተው ብዙ ጨዋታ የዳኙ ሆነዋል፡፡ ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ፣ ፌዴራል አርቢትር ብርሃኑ መኩሪያ፣ ፌዴራል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ፣ ፌዴራል አርቢትር ኤፍሬም ደበሌ፣ ፌዴራል አርቢትር ዳንኤል ግርማይና ፌዴራል አርቢትር ኢያሱ ፈንቴ ሶስት ሶስት ጊዜ፣ ፌዴሬል አርቢትር ኢብራሂም አጋዥ፣ ፌዴራል አርቢትር ከረን እንግዳ፣ ፌዴራል አርቢትር ወልዴ ንዳው፣ ፌዴራል አርቢትር ምስጋናው መላኩና ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ኃ/ስላሴ ሁለት ሁለት ጊዜ መርተዋል፡፡ በጨዋታዎቹ ሌሎች 13 የመስመር ዳኞች በየጨዋታዎቹ ላይ ተመድበው ግጥሚያዎቹን መርተዋል፡፡

የአርቢትሮቹ ብቃት መለካት

ከ36ቱ ግጥሚያዎች መሃል አብዛኛቹ በዲ.ኤስ.ቲቪ መታየቱ የዳኝነት ችግሮችን በጉልህ ያሳየ ሆኗል፤ ተደጋጋሚ ስህተቶቹ የዲ.ኤስ.ቲቪ ኮሜንታተሮችን ለቀልድ የጋበዘ ሲሆን ሊገቡ የነበሩ ኳሶች ሲቆሙ ኦፍሳይድ ያልሆኑ ኳሶች በተደጋጋሚ ሲያዙ መታየቱ ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩት የውጤት ማበላሸቶች ከዳኞች አቅም ጋር ሊያያዝ ይገባ እንደነበርም ታምኖበታል፡፡ የክልል ክለቦች ደጋፊዎችና የክለቦቹ አመራሮች ባህሪ ተፈርቶ ውጤቶች ይቀየሩ ነበር የሚለው ምክንያት እንዳለ ሆኞ የዳኝነት አቅም ማነሰም እንደነበረበት የሚያሳይ ሆኗል፡፡ ከ36ቱ ጨዋታዎች የጎላ የዳኝነት ስህተት ያልተገኘበት ጨዋታ በጣት የሚቆጠር መሆኑን ክለቦቹ በሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ታይቷል፡፡ የተጨዋቾቹ ዳኛ መክበብ አሁንም አለመቅረቱ የታዘብንበት ጨዋታዎች በርካታ ናቸው፡፡ ዳኞቹ በቀሪዎቹ ከተሞች በሚኖራቸው ጨዋታዎች ላይ አቅማቸውን አጎልብተው ጨዋታዎችን በብቃት እንዲመሩ ተጠይቀዋል፡፡ አርቢትሮቹ በውሳኔም ሆነ በሕግ አተገባበር ዝግጁነት ኖሯቸው ተጋጣሚዎቹ ውጤታቸውን ራሳቸው እንዲወስኑ ካላደረጉ በስተቀር የክለቦች ቅሬታ መቅረቡ አይቀሬ ነው፡፡ በቀሪ የዕረፍት ጊዜ የውድድርና ስነ ሥርዓት ኮሚቴ እንዲሁም የዳኞች ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን በጅማ ከተማ የሚካሄደውን ጨዋታ በሚመሩ ዳኞች አቅም ላይ ሊመክሩበትና ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይከሰቱ ጥረት እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡

የወልቂጤዎቹ ቅሬታ

የወልቂጤ ከተማ ተደጋጋሚ የፍትህ ጥያቄ በማቅረብ ከሊጉ ክለቦች ቅድሚያ ይወስዳል፤ ሁለት ሊገቡ የሚችሉ ኳሶች ባስቆማቸው ረዳት ዳኛ ላይ ቀሬታ አቅርበው በቀጣይ ጨዋታ ላይ ዳኛው የእነሱን ጨዋታ እንዲመራ መመደቡ ክለቡን ቅር አሰኝቷል፡፡ ይህም በፍትህ አካላት ውሣኔ ላይ እምነት እንዳይኖር ያደረጋል ተብሎም ይሰጋል፤ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ቀን ጨዋታ ላይ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 1ለ1 ሲለያዩ በነበረውም ዳኝነት ቅሬታ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በንፅፅር የመሀል ዳኞች የተሻለ ቢሆኑም የመስመር ዳኞቹ ግን ብዙ ይቀራቸዋል ስልጠናም ቢያገኙ ይሻላል የዲ.ኤስ.ቲቪ ኮሜንታተሮችም እየታዘቡ መሆኑ እንደ ሀገር መታረም ያለበት ይመስላል ሲሉ የክለቡ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ተደጋጋሚ የዳኞች ውጤት ለዋጭ ስህተቶች ደግሞ ዋጋ እያስከፈሉ በመሆኑ ዳኞችን ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸውና እምነት ባጣባቸው የሰፖርቱ ቤተሰብ ዳግም ለመታመን ጠንካራ ሙያዊ መሻሻል እንደሚጠበቅባቸው የብዙዎች እምነት ሆኗል፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport